Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ፈተና የፈጠረው አዲስ መንገድ

የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር በአገሪቱ ውስጥ ካሉት የበጎ አድራጎት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ አቶ ስንታየሁ አበጀ በተባሉ በጎ ፈቃደኛ የተመሠረተ ሲሆን፤ ተቋሙ ከምሥረታው ጀምሮ በሠራቸው ሥራዎች ዙሪያ የተቋሙን መሥራች ሺቢያምፅ ደምሰው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር መቼና እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ስንታየሁ፡- ማኅበሩ ዕውቅና አግኝቶ የተመሠረተው በ1990 ዓ.ም. ነው፡፡ ተቋሙን ለመመሥረትም ምክንያት የሆነኝ በሕይወቴ የገጠመኝ ፈተና ነው፡፡ ተወልጄ ያደጉት ሰሜን ጎንደር ነው፡፡ በ1980ዎቹ በወጣትነቴ አዲስ አበባ መጥቼ አልባሳትን እየሰፋሁ ነበር የምተዳደረው፡፡ ከበፊትም የተለያዩ የጤና ችግር ስላለብኝ በ1989 ዓ.ም. ሕመሜ በርትቶብኝ ለሦስት ወር የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ፤ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ለራሴ አንድ ቃል ገባሁ፡፡ ከሕመሜ ከተፈወስኩኝ ጧሪ ቀባሪ ያጡትን አረጋውያን፣ ሕሙማንና አካል ጉዳተኞችን በቀሪው የሕይወት ዘመኔ ለማገልገል ወሰንኩ፤ ዳንኩኝ፡፡ ከዛም ቃሌን በተግባር ለመለወጥ መንቀሳቀስ ጀመርኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሥራው ሲገቡ ምን ያህል ካፒታል ነበሮት? ምን ምን ድጋፎችን ነበር የሚያደርጉት?

አቶ ስንታየሁ፡- ለሦስት ወር የአልጋ ቁራኛ ከመሆኔ በፊት ወደ 8,000 ብር አጠራቅሜ ነበር፡፡ ብሩን የማስቀምጠው ወለል ላይ ከማነጥፈው ፍራሽ ሥር ነበር፡፡ ከሦስት ወር በኋላ ከሕመሜ ድኜ ፍራሹን ሳነሳው ከሁለት ብር ውጪ ያስቀመጥኩት ብር ሁሉ ሻግቶ ከጥቅም ውጭ ሆኖ አገኘሁት፡፡ የተረፈችውንም ሁለት ብር የውኃ መቅጃ ጄሪካን ገዛሁባት፡፡ እንግዲህ በሁለት ብር ካፒታል ነው የተነሳሁት፤ ወደ ሥራው ስገባ በምኖርበት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የመቃብር ባለቤቶችን ቤት በማስፈቀድ አረጋውያኑን፣ ሕሙማኑን፣ አካል ጉዳተኛውን ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ ከዛም በገዛኋት ጄሪካን ውኃ በአካባቢው ካለ ወንዝ በማመላለስ ገላቸውን፣ ልብሳቸውን በማጠብ፣ የሚውሉበትን የሚያድሩበትን ቤት በማፅዳት፤ ከሕዝብ የተሰበሰበውን ምግብ በማቅረብና በመመገብ ሕይወታቸው ሲያልፍ ለማዘጋጃ ቤት በማሳወቅ ነበር ሥራውን የጀመርኩት፡፡ በዚህ ሁኔታ ሥራውን እያከናወንኩ ሳለሁ ንጉሤ፣ ሀብታሙና ካሳሁን ከበደ ከሚባሉ ወጣቶች ጋር ተዋወቅን፡፡ ወጣቶቹ ቤተሰቦቻቸውን አስተባብረው ከማኅበሩ ምሥረታ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዕርዳታ የምታውሉትንስ ወጪዎች እንዴት ነው የምታገኙት?

አቶ ስንታየሁ፡- ማኅበሩ ሙሉ በሙሉ የሚረዳው በሕዝብ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ድጋፎችን እንዲያደርግ ብሮሸሮችን አዘጋጅተን በመበተን፤ እንዲሁም የተቋሙን ሥራዎች በዶክመንተሪ መልክ በማሳየት ነው ገቢ የምናገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ያሰባችሁትን ያህል ሠርታችኋል?

አቶ ስንታየሁ፡- አልሠራንም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት 17 ዓመታት የመሥሪያ ቦታ ችግር ነበረብን፤ የፋይናንስ አቅም ውስንነት፣ በዚህም ምክንያት ምግባቸውን፣ አልባሳታቸውን እንዲሁም የሕክምና ወጪያቸውን የሚሸፍን ገንዘብ አልነበረንም፡፡ ከኅብረተሰቡም የሚገኘው ድጋፍ ጥቂት ነበር፡፡ አሁን ግን ከሕዝቡ የሚደረግልንም ድጋፍ እየተጠናከረ ነው፡፡ ይህም የሚበረታታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት 17 ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የሠራችሁትን ሥራ ቢገልፁልን?

አቶ ስንታየሁ፡- ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያን፣ ሕሙማን፣ አካል ጉዳተኞች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ከ230 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ብዙዎቹ ድነው በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ ደግሞ በማኅበሩ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ሲመሠረት ምን ያህል ነዳያን ነበሩት? አሁንስ?

አቶ ስንታየሁ፡- ማኅበሩን ስንመሠርት 25 የሚሆኑ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ቁጥራቸው 100 ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቁጥራቸው አናሳ የሆነበት ምክንያት አለው?

አቶ ስንታየሁ፡- ዋነኛው ምክንያት የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ ሥራችንን የምናከናውነው በአራት ቦታዎች ነው፡፡ ሁለት የቀበሌ ቤት፤ ሁለት ደግሞ የግለሰብ ቤት ተከራይተን ነው፡፡ ቤቶቹ በጣም ጠባቦች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የነዳያኑን ቁጥር ከማብዛት ይልቅ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ስለምናምን ነው፡፡ ማኅበራችን በሥሩ ያቀፋቸው የተለያዩ ችግሮች ያለባቸው ወገኖች እንደመሆናቸው መጠን የሚያስፈልጋቸውም የዛኑ ያህል ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃልና አንድም በዚህ ምክንያት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሕዝቡስ ድጋፍ እንዴት ይገለፃል?

አቶ ስንታየሁ፡- ኅብረተሰቡ ከፋይናንስ ጀምሮ የቁሳቁስ እንዲሁም በጉልበትና ባላቸው ዕውቀትና ክህሎት ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ በሕዝብ የሚተዳደር እንደመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ አይታይም፡፡ ለነዳያኑ በየጊዜው ድጋፍ ሊያደርጉ የሚመጡት ብዙዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ የባለሀብቱ ተሳትፎ በጣም አናሳ ነው፡፡ መጥተው እንዲጎበኙን ስንጋብዛቸው እንኳን ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ አይመጡም፡፡ ይህ መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ጧሪ ቀባሪ ያጡትን ወገኖች መንከባከብ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሚደረግላቸውስ ሕክምና ምን ይመስላል?

አቶ ስንታየሁ፡- በሁለት ዓይነት መንገድ የሕክምና ዕርዳታ ያገኛሉ፡፡ አንደኛው የሕክምና ድጋፍ ደብዳቤ ከቀበሌያችን በማጻፍ ወደ መንግሥት የጤና ተቋማት በመውሰድ የምናሳክምበት ሒደት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበራችን ድረስ በመምጣት ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በተለይ ስማቸውን የማልጠቅሳቸው ጥቂት ዶክተሮችና ነርሶች በየሳምንቱ እየመጡ የነዳያኑን የጤና ሁኔታ የሚከታተሉልን፣ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን የመድኃኒት ወጪ ሳይቀር የሚሸፍኑልን ባለሙያዎች አሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ውስጥ ካሉ መሰል የመረዳጃ ተቋማት ጋር በትብብር የምታከናውኗቸው ሥራዎች አሉ?

አቶ ስንታየሁ፡- ብዙም የተጠናከረ ባይሆንም አለ፡፡ ሰባት ተቋማት አንድ ላይ በመሆን የጋራ ጥምረት ቡድን አቋቁመናል፡፡ የጥምረቱ ዓላማም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጠሩት ችግሮች ላይ በመወያየት የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመለዋወጥና በተቋማቱ ላይ የሚፈጠሩትን ችግሮች የበለጠ ተሰሚነት እንድናገኝ ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ በልምድ ልውውጡ በኩል ለአብነት ያህል ሜቄዶንያ የአረጋውያን ማኅበር እኛ ዘንድ መጥተው ሁሉን ነገር ጎብኝተው ሄደው ነበር፡፡ እኛም ሄደን ማዕከላቸውን ጎብኝተን ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በማኅበሩ ውስጥ ምን ያህል ተቀጣሪ ሠራተኞች አሉ?

አቶ ስንታየሁ፡- እየተከፈላቸው በቋሚነት ተቀጥረው የሚሠሩት 15 ናቸው፡፡ የሠራተኛው ቁጥር ካለው ከፍተኛ የሥራ ጫናና ፈታኝነት አንፃር አናሳ ነው፡፡ ይህንንም ያደረግነው ወጪን መቀነስ ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ ያለነው ሠራተኞች ነዳያኑን 24 ሰዓት እንከባከባቸዋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ በጎ ፈቃደኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየመጡ ያግዙናል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎች ፕሮግራም እያስያዙ ልብስ ማጠብና ሌሎችንም ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተቀጣሪዎቹን ቁጥር አናሳ አድርገነዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ ሥራ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ያሉ ነገሮች ምንድናቸው?

አቶ ስንታየሁ፡- ማኅበራችን ሲመሠረት ጀምሮ በርካታ ችግሮች ነበሩበት፤ ከዚህም ውስጥ የአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ክፍተት፤ ይህም ማለት ከኅብረተሰቡ የሚኙትን የፋይናንስም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ ለግል ጥቅማችን እንደምናውል በማሰብ በእኛ ላይ አመኔታ አለማሳደር፤ በዚህም የግንዛቤ ክፍተት ይመስለኛል ተቋሙ በተለይ አቅም ካላቸው ባለሀብቶች ድጋፍ የማያገኝበት ምክንያት፤ ይህ አመለካከት ግን ፍፁም የተሳሳተ ነው፡፡ ይህ አሁንም ያለ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን መሻሻሎች አሁን አሁን እያየን ነው፡፡ በሒደት ችግሩ ይቃለላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላው እጅግ አንገብጋቢ ችግር የሆነብን የውኃ እጦት ነው፡፡ እኛ ባለንበት አካባቢ የቧንቧ ውኃ የምናገኘው በ15 እና በ10 ቀን ውስጥ አንድ ጊዜ ነው፡፡ ያውም የምትመጣው ሌሊት ነው፡፡ ይህ በምንሠራው ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረብን ነው፡፡ በውኃ እጥረት ምክንያት ነዳያኑን በመንከባከብ ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረብን ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውኃ እጥረቱ እየገነባን ባለው ዘመናዊ ማዕከል ግንባታ ላይም ችግር እየፈጠረብን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የሕክምና ምርመራዎችን በግል የሕክምና ባለሙያዎች እንድናከናውን በሚጻፍልን ጊዜ የግል የሕክምና ተቋማት የሚጠይቁን የሕክምና ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም የሥራችን ሌላኛው ፈተና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ነዳያንን ከመንከባከብ ባለፈ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ካሉ?

አቶ ስንታየሁ፡- ማኅበሩ በተቋቋመበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮሜዳ አካባቢ በሚደረጉት የፅዳትና ውበት ሥራዎች ላይ አቅማችን በፈቀደው መጠን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው፡፡ በፅዳትና ውበት ሥራ ለተሰማሩ ሠራተኞች የፅዳት አልባሳት፣ የቆሻሻ መሰብሰቢያ መጥረጊያና ማጠራቀሚያ ገዝተን ለግሰናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት ለሚማሩ ምግብ በበቂ ሁኔታ ለሚያገኙ ተማሪዎች በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡበትን መንገድ አመቻችተን እየተመገቡ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ትርፍ አልባሳትን በምናገኝበት ጊዜ ለነዳያንም እንለግሳለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ተቋሙ ወደፊት ምን ሥራዎችን ለመሥራት አስቧል?

አቶ ስንታየሁ፡- በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥት 2924 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶን ዘመናዊ የነዳያን ማዕከል እየገነባን ነው፡፡ ግንባታው 80 በመቶ እየደረሰ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም አጠቃላይ ሥራዎችን የማጠናቀቅ ዕቅድ አለን፡፡ ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የቅበላ አቅማችንንም ያሳድገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ የራሱ የሆነ የሕክምና ማዕከል፣ የመዝናኛ ክበባት ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚያገለግል አዳራሽንም አካቶ የሚይዝ በመሆኑ በኅብረተሰቡና በነዳያኑ መካከል የበለጠ መቀራረብን ይፈጥራል፡፡ ማኅበሩም ቢሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር አቅምን ያገኛል ብለን እናስባለን፡፡ በተለይ ደግሞ አዳራሹ ለተለያዩ ስብሰባዎች፣ የሠርግ፣ የልደት፣ የምርቃት ዝግጅት በሚውልበት ወቅት ማኅበሩ ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ አርአያ ይሆናልም ብለን እንገምታለን፡፡ ለሌሎችም ጥሩ ተሞክሮ ለመሆን ነው በመንቀሳቀስ ላይ ያለነው፤ ነገር ግን አሁንም ካሰብነው ለመድረስ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ያስፈልገናልና ኅብረተሰቡ አሁንም በሚችለው ሁሉ ድጋፉን እንዲያጠናክርልን እንጠይቃለን፡፡  

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...