Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት ጉዞ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያለምንም ሥራ በየቤቱ ጓዳ ተቆልፎበት የተቀመጠ ገንዘብ እንደሞተ ይቆጠራል ይላሉ፡፡ ወደ ባንክ ያልመጣ ገንዘብ አገልግሎት እንዳልሰጠ የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ የአገርን ኢኮኖሚ ሊጐዳ የሚችልበት አጋጣሚ ስላለ፣ በተፈለገው ፍጥነት ማደግና መለወጥ ለሚፈልግ ኢኮኖሚ እንቅፋት እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

ገንዘብ ያለሥራ ቤት ውስጥ መቀመጥ እንደሌለበት የሚሞግቱት የባንክ ባለሙያዎች፣ በምንም መንገድ ቢሆን ወደ ባንክ ሥርዓት ውስጥ መግባት እንዳለበት አበክረው ይገልጻሉ፡፡ በሌላኛው ጽንፍ ግን ገንዘብ ባንክ መቀመጡ ከሃይማኖት ባሻገር በተሰለፉ ምሁራን ዘንድም ሲብጠለጠል ይታያል፡፡ ባንኮች በሰው ገንዘብ የሚነግዱ፣ ባዶ ወንበር፣ ጠረጴዛ ይዘው፣ ቤት ተከራይተው በአስቀማጭ ገንዘብ ወለድ የሚሰበስቡ እየተባሉ ሰፊና ጽንፍ የወጣ ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡

ይህም ቢባል ግን በእምነታቸው ምክንያት አልያም በሌላ መነሻ ከባንክ አገልግሎት የራቁ ዜጐች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከእምነት ጋር በተያያዘ ከባንክ የሚገኝን ወለድ ነክ አገልግሎት ስለማይፈልጉ ወደ ባንክ የማይመጣ በርካታ ገንዘብ በእጃቸው እንዲኖር ተገደዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሥራ ፈትቶ የተቀመጠ ከፍተኛ ገንዘብ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ ምክንያት ወደ ባንኮች መምጣት ጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተለየ ራሱን ችሎ እንዲሠራ የሚለው ሐሳብ በገዥው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዘንድ ግን እስካሁን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ወለድ አልባ ባንክ ለማቋቋም ጥያቄ ማቅረባቸውና መንቀሳቀሳቸው ይታወሳል፡፡ ገዥው ማንኛውም ባንክ ከመደበኛ አገልግሎቱ ጐን ለጐን መሥራት እንደሚችል በመፍቀዱ ግን ከባንክ አገልግሎት ርቀው የነበሩ ዜጐች የባንክ ደጆችን እንዲረግጡ ዕድል እየሰጣቸው ነው ተብሏል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ መመርያ ካወጣ ሁለት ዓመት ሊቆጠር ነው፡፡ በአብዛኛው ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ትስስር ያለውን ይህን አገልግሎት ግን ማንኛውም ተገልጋይ የሚጠቀምበት ሲሆን በዓለም ላይ የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡

ይህ አገልግሎት እንዲጀመር ከተፈቀደ ወዲህ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ካሉት ጥቂት ባንኮች ውስጥ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ተጠቃሽ ነው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ከሆነ፣ ከተቋቋመባቸው ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ውስጥ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አንዱ በመሆኑ በቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት ተችሏል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ካሉት 132 ቅርንጫፎች ውስጥ ከ120 በላይ በሚሆኑት የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት በባንኩ መሰጠት ሲጀመር ራሱን የቻለ አንድ ቅርንጫፍ እንደመክፈት ያህል ነው የሚሉት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ፣ አገልግሎቱ ከተለመደውና ባህላዊ ከሚባለው የባንክ አገልግሎት በተለየ የሚሠራበት ነው፡፡ አሠራሩም ለብቻው ተነጥሎ የራሱ ሥርዓት፣ የራሱ የመረጃ ቋት ያለው ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ አገልግሎት የሚመደቡ ሠራተኞችም መደበኛውን የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡት የተለዩ ናቸው፡፡ በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በኩል የሚሰበሰበው ገንዘብም ለብቻው የሚቀመጥ ነው፡፡ መደበኛውንና ወለድ አልባ አገልግሎቱን አጣምሮ በአንድ ቅርንጫፍ ውስጥ ቢሠራበትም፣ ሁለቱ አገልግሎቶች ግን በተለያየ መስኮት የሚስተናገዱ ናቸው፡፡

ወለድ አልባው አገልግሎት ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም እስከ ዛሬ የመደበኛውን የባንክ አገልግሎት የማይጠቀሙ፣ ወለድ የማይፈልጉ ዜጐች በቤት ያስቀመጡትን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲያመጡ የማድረጉ ሥራ ግን ከባድ እንደነበር የባንኩ ፕሬዚዳንት ይገልጻሉ፡፡

ይህም ሆኖ ባንካቸው በአንድ ዓመት ውስጥ በወለድ አልባው የሚገለገሉ ደንበኞቹን ቁጥር ከ45 ሺሕ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ ደንበኞች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበ ከፍተኛው መጠን እንደሆነም ይገመታል፡፡  

በወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል ባንኩ ብድር መፍቀድ ጀምሯል፡፡ እስካሁን በወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት በብዛት ‹‹ኢስላሚክ ባንክ›› እየተባለ በሚጠራው አሠራር፣ ብድር ከጠየቁ ተበዳሪዎች ውስጥ ከ40 በላይ ለሚሆኑት ከ420 ሚሊዮን ብር በላይ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በአሠራሩ መሠረት ግን ብድሩ በተፈቀደ ማግስት የሚለቀቅ አይደለም፡፡ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጥ ባለመሆኑም ብድሩ ለተፈቀደለት ዓላማ በቀጥታ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት ዕቃ ለማስመጣት ብድር የተፈቀደለት ተበዳሪ፣ ዕቃውን የሚያስመጣው ከባንኩ ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ 

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ሙረሃባ በሚባለው የባንክ አገልግሎት ዓይነት ብቻ ነው ባንኩ ብድር የሰጠው፡፡ በኢስላሚክ ባንክ አሠራር ውስጥ ዘጠኝ የሚደርሱ የፋይናንስ አገልግሎቶች ቢኖሩም፣ እስካሁን ገንዘብ እንዲለቀቅ የተፈቀደው በሙረሃባ ብቻ ነው፡፡ ሙሻረካ የሚባለውን አገልግሎት ለመጀመር ባንኩ እንዳልቻለ የአቶ አቢ ገለጻ ያስረዳል፡፡

ሙሻረካ በኢስላሚክ ባንክ አሠራር መሠረት ባንኩና ተበዳሪው ወይም የተበዳሪው ሸሪክ በጋራ ኩባንያ ፈጥረው የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመሥራት የሚበደሩበት አሠራር ነው፡፡

ይህንን አሠራር ለመጀመር ያልተቻለው ለዚህ የፋይናንስ አገልግሎት ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ ስለሚገድብ ነው፡፡ እንደ አቶ አቢ ገለጻ በሙሻረካ አሠራር ባንኩና ተበዳሪው በጋራ በሚፈጥሩት ኩባንያ መሠረት የባንኩ ድርሻ ከ20 በመቶ መብለጥ የለበትም፡፡ የተበዳሪው ደግሞ 80 በመቶ ይሁን የሚለው የመመርያው አካል ብዙዎችን ያስደሰተ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለሙሻረካ የተቀመጠውን የባለቤትነት ድርሻ የሚያመለክተው መጠን መስተካከል እንዳለበት ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡንና ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አቶ አቢ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የብድር ዓይነት የሚሰጠው ብድር ለባንኩ የተሻለ ትርፍ ሊያስገኝ እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡ ብድሩ ሲለቀቅ አዋጭነቱ ታይቶ በመሆኑ እስካሁን በተፈቀደው 420 ሚሊዮን ብርና በገንዘቡ አማካይነት በሚሠራው ሥራ ባንኩ የሚያገኘው ገቢ ከመደበኛው የባንክ ብድር ከሚገኘው ትርፍ የተሻለ እንጂ ያነሰ እንደማይሆን አቶ አቢ ይሞግታሉ፡፡

‹‹ዋናው ነገር በቂ ፈንድና በቂ ተበዳሪ ማግኘት ነው፤›› የሚሉት አቶ አቢ፣ ‹‹አሁን ከሰበሰብነው 600 ሚሊዮን ብር ወደ 420 ሚሊዮን ብር ማበደራችን ትክክለኛ አሠራር ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከትርፍ አንፃር ጥቅም ቢኖረውም የባንኩ አነሳስ ግን ትርፍ ለማግኘት ብቻ አይደለም በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹ዋናው ነገር ኅብረተሰቡን ማቀፍ ነው፡፡ ይህንን ያደረግንበትም ምክንያት የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ጥቅም ስላለው ነው፤›› ያሉት አቶ አቢ፣ ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን፣ ባንካቸውና ሌሎች ባንኮች በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እየሰበሰቡ ያሉትን ገንዘብም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

 ወለድ የማይፈልጉ ብዙዎች ገንዘባቸውን ቤታቸው የማስቀመጥ ልምድ እንደነበራቸው፣ አሁን ግን ይህ ገንዘብ ወደ ባንክ መጥቶ በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት መሠረት ለሌሎች በማበደር ገንዘቡ ኢኮኖሚ ውስጥ በመግባት በመደበኛው ዘርፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹መንግሥትም የሚያገኘው ገቢ ይኖራል፡፡ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ይህንን ማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጐላ ይሆናል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ የሞተና በየቤቱ ተቆልፎበት የተቀመጠን ገንዘብ አውጥቶ ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ማስገባት እየተቻለ ነው፤›› በማለት ባንካቸው ከሚያገኘው ትርፍ በላይ አገራዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታው የጐላ መሆኑን አቶ አቢ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ሊኖረው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ የጠቀሱት አቶ አቢ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ሊሰባሰብበት እንደሚችል በአንድ ዓመት ውስጥ የታየውን ተሞክሮ በመንተራስ ተስፋ እንደሚጣልበት ጠቁመዋል፡፡

እንደምሳሌ ያቀረቡትም ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አሁን ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ባንኩ ሥራ በጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት እንኳ ከመደበኛው አገልግሎት ይህንን ያህል ተቀማጭ ገንዘብ ያለማሰባሰቡን በመጥቀስ ነው፡፡

በመሆኑም በአዲሱ አገልግሎት ከፍተኛ ሊባል የሚችል ገንዘብ በማሰባሰብ ገንዘቡ እንዲሠራ፣ ገንዘብ አጥተው መሥራት ያልቻሉ ዜጐችም ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ያስቻለ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አስቀማጮች ወለድ የማይከፈላቸው ቢሆንም በምትኩ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አሠራር ግን አለ፡፡ አቶ አቢ እንደሚሉት፣ አስቀማጮች ብዙ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ወለድ አልባ አስቀማጮች ትልቁ ጥቅም ገንዘባቸው ለመጥፎ ተግባር እንደማይውልባቸው መረጋገጡ ነው፡፡ ገንዘባቸው ወለድ የሚያስገኝ ሥራ ላይ እንዳይውል ማድረግ ግድ ነው፡፡ አስቀማጮቹ የሚፈልጉትም ይህን ስለሆነ፣ በርካታ አስቀማጮችም ይህንን ዕድል ከሃይማኖታቸው አኳያ እንደ ትልቅ ጥቅም እንደሚያዩትም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መንገድ የተሰበሰበው ገንዘብ እያደገ ሲመጣና አቅም ሲኖረው፣ አስቀማጮች ትርፍ የሚጋሩበት አሠራር እንዳለም አቶ አቢ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለአስቀማጮቹ ትርፍ ልንሰጣቸው የምንችለው እነርሱ ባስቀመጡት ገንዘብ ላይ ብድር ተሰጥቶ የተሠራው ሥራ ትርፍ ማምጣት ሲጀምር ትርፉን ወደማካፈል እንመጣለን፤›› ይላሉ፡፡አስቀማጮች ትርፍ የሚያገኙበትን አዲስ የአስቀማጮች አገልግሎትም በቅርቡ ባንኩ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ እስካሁን እያስቀመጡ ላሉት ደንበኞች ትርፍ የሚያስገኝ ስላልሆነ አዲስ አገልግሎት ሲጀምር ግን ትርፍ ወደሚያስገኘው የወለድ አልባ ተቀማጭ አገልግሎት ሒሳባቸውን ሊያዞሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ትርፍ የሚያስገኘው የተቀማጭ ሒሳብ ግን የራሱ አሠራር ይኖረዋል፡፡ እንደ አቶ አቢ ገለጻ ከሆነ፣ ትርፍ የሚያስገኘው የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎትን ለማግኘት ራሱን የቻለ ውል ስላለው በዚያ ውል መሠረት መስማማትን ይጠይቃል፡፡

አስቀማጮች ትርፍ ለመውሰድ ሲዘጋጁ አብሮ የሚወስዱት ተጋላጭነት ወይም አደጋ አለ፡፡ ይህም በሸሪአው አስገዳጅነት የተቀመጠ እንደሆነ የገለጹት አቶ አቢ፣ የትርፍ መጋራቱ ሒደት ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተለየ መንገድ የሚካሄድ ነው ብለዋል፡፡ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ለተቀማጭ ገንዘብ አምስት በመቶ ወለድ ሲከፈል፣ በወለድ አልባው ነገር ግን ትርፍ በሚያስገኘው የተቀማጭ ሒሳብ መሠረት ትርፍ ለማግኘት በሚደረገው ስምምነት ሊገኝ የሚችለው ትርፍ ከአምስት በመቶ በላይ ሊሆን ወይም ከዚያም ያነሰ አላያም ከነጭራሹ ምንም ትርፍ ላይገኝበት ስለሚችል ነው ተጋላጭነት ያለበት የተባለው፡፡

ስለዚህ ትርፍ ለማስገኘት የተቀመጠው ገንዘብ አክሳሪ ከሆነ ኪሣራውን አስቀማጩም እንዲጋራ ይደረጋል፡፡ ይህ ግን እንደ አማራጭ የሚቀርብ ነው፡፡ አሠራሩ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም አደጋ ያለበት ስለሆነ፣ አስቀማጮች ይህንን አውቀው እንዲገቡበት መረጃው በአግባቡ ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ሃይማኖታዊ ገጽታው የጐላ ነው የሚለው አስተያየት የብዙዎች ቢሆንም አቶ አቢ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ‹‹ሃይማኖቱ የግለሰቡ እንጂ የባንኩ አይደለም›› የሚሉት አቶ አቢ፣ ባንኩ የሃይማኖት ሥራ አይሠራም ብለዋል፡፡

ማንኛውም ድርጅት አገልግሎት ሲሰጥ፣ አገልግሎት ተቀባዮቹን በማሰብ ነው፡፡ ‹‹የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ሲጀመር የራሱ ተገልጋዮች ያሉት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አገልግሎት እንደ አንድ አማራጭ የቀረበ እንጂ ሃይማኖታዊ ሊያሰኝ አይችልም፡፡››

በሁለቱም የባንክ አገልግሎቶች የተለያየ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሰዎች ይጠቀማሉ ያሉት አቶ አቢ፣ ‹‹በወለድ አልባው የባንክ አገልግሎት ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ይጠቀማል፡፡ በመደበኛው የባንክ አገልግሎትም የሁለቱም ሃይማኖቶች ተከታዮች እየተጠቀሙ በመሆኑ አገልግሎቱ የሁሉም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ባንኩ ይህንን አገልግሎት ለማስፋትና ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች