Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየዓድዋ ውሎ ከ119 ዓመት በፊት

የዓድዋ ውሎ ከ119 ዓመት በፊት

ቀን:

19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአንድ በኩል በአውሮፓውያን የግዛት መስፋፋት፣ በአፍሪካውያን ደግሞ የነሱ ቅኝ ተገዥ የመሆን ምኞት ዘመንም ነበር፡፡ ይኸው ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እንደነበረም ይታወቃል፡፡ የኢንዱስትሪው አብዮት ደግሞ ጥሬ ዕቃውን እንዲፈልጉና በአነስተኛ የጉልበት ዋጋ አውጥተው እንዲያመርቱ እንዲሁም ገበያ እንዲፈልጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡

በዚህ ረገድ መካከለኛው ምሥራቅና ሩቅ ምሥራቅ አስፈላጊ ቅኝ ግዛቶች መሆናቸው አስተማማኝ ቢሆንም አፍሪካ ግን ያኔ ‹‹ጨለማው ዓለም›› ተብላ ትታወቅ ስለነበር እምብዛም ትኩረት አልተሰጣትም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የአፍሪካንና የተቀረውን ዓለም የንግድ ግንኙነት በአብዛኛው በባሪያ ንግድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ባሮችም ከማዕከላዊ አገሮች ወደድንበር እየተገፋፉና እየተገፈተሩ ይመጡላቸው ስለነበር ወደ ውስጥ ዘልቀወው መግባት እምብዛም አላስፈለጋቸውም፡፡ ከዚያም አውሮፓውያን የባሪያ ንግድን በሕግ ስለከለከሉ በዚህ ረገድ የነበረው ግንኙነት ደረጃ በደረጃ እየተቋረጠ ሔደ፡፡

ይሁንና ከአፍሪካውያን ባሮች አንዳንድ መሠረታዊ ቁም ነገሮችን በመረዳትም ይሁን የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ወይም የቅኝ ግዛት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ገበያ ለማግኘት ሲሉ ‹‹አሳሾቻቸውን›› መላክ ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ጁሴፔ ሳፔቶ የተባሉትን ኢጣሊያዊ ሚሲዮናዊ ወደ አሰብ የላካቸው ሩባቲኒ የተባለ የንግድ ኩባንያ ነበር፡፡

- Advertisement -

በተለያዩ ስሞችና መልኮች የመጡ አፍሪካውያን አውሮፓውያኑን ያለ ጥርጣሬ በሙሉ ልብ ተቀብለዋቸዋል ማለትም አይደለም፡፡ የአውሮፓውያኑ ዓላማ ከሃይማኖት ትምህርት ከሰላማዊ ግንኙነት አልፎ ቅኝ ግዛት አናደርጋችሁም ሲሉም ጥያቄአቸውን በጸጋ አልተቀበሉትም፡፡ ሆኖም አፍሪካውያኑ የአውሮፓውያንን የቅኝ ገዥነት ፍላጎትን ባይፈልጉትም በነሱ እጅ መውደቃቸው አልቀረም፡፡ የቅኝ ግዛቱ በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅም፣ በደቡብም ቀጠለ፡፡ የስዊዝ ካናል መከፈት አትላንቲክ ውቅያኖስንና ሕንድ ውቅያኖስን በማቋረጥ ማለትም አፍሪካን በመዞር ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደሩቅ ምሥራቅ ይደረግ የበረውን ጉዞ በአያሌ ቀነሰው፡፡ በአንጻሩም የቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በእጅጉ ከፍ አደረገው፡፡ ቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በአካባቢው የሚገኙ አገሮች የባሕር ዳርቻዎችን አስፈላጊነት አጎላው፡፡ የባሕር ለባሕር ጉዞው ከኢኮኖሚ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ስለነበርም ደቡብና ሰሜን አፍሪካን ታላቋ ብሪታኒያ፣ ምዕራብንና ምሥራቅ አፍሪካን ፈረንሳይ ባቡር ሐዲድ ለማገናኘት ትልቅ ፍላጎት አሳደረባቸው፡፡ በእርግጥ በስተሰሜን በኩል ግብጽን በስተደቡብ በኩል ደቡብ አፍሪካን ይዛ የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ በስተ ምሥራቅ በኩል ጂቡቲን በስተምዕራብ በኩል ሴኔጋልን ይዛ የነበረችው ፈረንሳይ ፊት ለፊት ባሉት አቅጣጫዎች የባቡር ሐዲድ ለመዘርጋት ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ፡፡

ይህም ሆኖ በፈረንሳይና በእንግሊዝ መካከል የጥቅም ግጭት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ከደቡብ ወደ ሰሜን ወይም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አቋርጦ ለማለፍ ሐዲሱ በግድ አንድ ቦታ ላይ ማለፍ ነበረበት ያም ሥፍራ ያኔ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት በነበረችው ሱዳን በኩል መሆኑ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ጂቡቲ በፈረንሳይ ብትያዝም ኢትዮጵያ ነፃ አገር ስለነበረች ይህች ነፃ አገር አንድም በእንግሊዝ ካለበለዚያም እንግሊዝ በምትፈልጋት አገር ካልተያዘች ሁኔታው አመቺ አልነበረም፡፡ ይህም በበኩሉ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳይወዱ በግድ ውስብስብ እንዲሆን አደረገው፡፡ ናይልን (ዓባይን) ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን መቆጣጠር ያስፈልግ ነበርና የኢትዮጵያ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ በአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሥር መዋል የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆነ፡፡

የዛሬ መቶ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ታሪክን መለስ ብለን ስንመለከተው የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር ብሎ መጠየቅ ለዚህ ትውልድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታና የኢጣሊያ ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበረ ለማውሳት እንሞክራለን፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ

ስለወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲወሳ ከጥንት አክሱማውያን እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረችው ስመገናና ኢትዮጵያ ከሦስት መቶ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በእርስ በርስ ጦርነት ተዳክማ ለዘመነ መሳፍንት ተዳርጋ ከነበረችበት ጊዜ ተላቃ በመጀመሪያ በአፄ ቴዎድሮስ፣ ከሳቸውም ቀጥሎ በአፄ ተክለጊዮርጊስ፣ በአፄ ዮሐንስና በአፄ ምኒልክ ጥንታዊ አንድነቷን በከፊልም ቢሆን ማስከበር የጀመረችበት ጊዜ ነበር፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ በትረ መንግሥት ከቆመም ገና በአሥራዎቹ ዓመታት ውስጥ ነበር፡፡ የዓድዋ ጦርነት በአንድ ጊዜ ዱብ ያለ ሳይሆን ከነዚህ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪዎች አነሣስና አመራር እንዲሁም በተለይም ከመጀመሪያዎቹ ሦስቱ አወዳደቅ ጋርም እጅግ የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ ከሦስተኛው መሪ ማለትም ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጋር ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ይያያዛል፡፡

አራቱ የኢትዮጵያ አንድነት መሐንዲሶች በአንድነት በነበሩበት ዘመን ስንመለከታቸው አውሮፓውያን የቅኝ ግዛት አድማሳቸውን ለማስፋፋት የወሰኑበት ዘመን መሆኑን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩል አገራቸውን ከዘመነ መሳፍንት ለማውጣት በሌላ በኩል፤ ከውጭ ወራሪዎች ለማዳን ይደረግ በነበረው ፖለቲካዊ ሕይወት ያለፉ መሆናቸው፤ አንዱና በራሱ መንገድ እንደጀማሪ፤ ሌሎችን ደግሞ በራሳቸው መንገድ እንደቀጣይ እንድናያቸው ከማድረጉ በስተቀር አንድም ሁለትም ናቸው ወደሚል አዝማሚያ እንድናመራ ያደርገናል፡፡

በሌላ በኩልም ለብዙ ዓመታት በቅኝ ገዥዎች ስትረገጥ ከነበረችበት ዘመን ነፃ ከወጣች የ27 ዕድሜ የነበራት ኢጣሊያን እናገኛታለን፡፡ ይህች ሀገር በነማዚኒና ጋሪባልዲ ጀግንነት የተመላበትን ወታደራዊ አመራር እ.ኤ.አ በ1870 አንድነቷን አስከብራ ነበር፡፡ ይሁንና በዚያ ወቅት አንድነቷን ያስከበረችው፣ ከፍተኛ ኃይል አስተባብራ ስለነበርና በነፃነትና በአንድነት ዘመቻው የተሳተፉ ሕዝባዊ ሠራዊት አባላቷ የደም ካሣ እንዲከፈላቸውና መተዳደሪያ እንዲሰጣቸው ይፈልጉ ስለነበር ለዚያ ችግር መፍትሔ ማግኘት ነበረባት፡፡ የተገኘው አማራጭም ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በወቅቱ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ቅኝ ግዛት ማግኘትና በምታገኘው ቅኝ ግዛት ውስጥም የሠፈራ ፕሮግራም ማካሔድ ነበር፡፡ ሌላው እቅዷ ወደላቲን አሜሪካ ማሻገር ነበር፡፡ የላቲን አሜሪካውያንና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን ለጊዜው እንተወውና ወደ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ትኩረት ብቻ እንመልከት፡፡

ምንም እንኳን የኢጣሊያ መንግሥት ቅኝ አገዛዝ ፖሊስን እንደአማራጭ ቢወስድም በወቅቱ የኢጣሊያ መንግሥትን ፖሊሲ ይቀናቀኑ የነበሩ ኃይሎች ደግሞ ይህንን የመስፋፋት ፖሊሰ አጥብቀው ይቃወሙት እንደነበረም በዚህ አጋጣሚ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም የኢጣሊያ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ለማለዘብ በአንድ በኩል የጦርነት መሠናዶ እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ማጠናከርን እንደስልት ወሰደ፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱንም መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ጠቅላላ ሁኔታ የሚያጠኑ የኢጣሊያ መልክአ ምድራዊ ማኅበረሰብ አባላትንም ልካለች፡፡ እነዚህም መልክአ ምድራዊ ማኅበረሰብ አባላት በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ በነበሩት ምኒልክ ፈቃድ ልጥ ማረፊያ (አንኮበር) ላይ ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡ እነዚህም የቡድን አባላት ወደደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመጓዝ ተልዕኳቸውን አከናውነዋል፡፡ ‹‹ዓድዋና ምኒልክ›› በሚል ርዕስ በቤካነሞ የተዘጋጀው ጽሑፍ እንደሚገልጸውም አባ ማስያስ የተባለው የቫቲካን ካርዲናልም ከ1868-1879 ድረስ ካለው ጊዜ ሸዋ ውስጥ ተቀምጦ ንጉሥ ምኒልክን ይረዳ ነበር፡፡ ፔየትሮ አንቶኔሊ የተባለ ኢጣሊያዊ መስፍን ወደ ንጉሥ ምኒልክ ተልኳል፡፡ ይህም ሰው በንጉሥ ምኒልክና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል የወዳጅነት ስምምት እንዲደረግ ሁነኛ ሚና ተጫወተ፡፡ በዚሁ ስምምነት ውስጥ በተለይም አንቀጽ አሥራ ሦስትን ስንመለከተው ንጉሥ ምኒልክ ኢጣሊያውያንን እንደአገናኝ መኮንን ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ስለሚያወሳ አንዳንድ ምሁራን በ1897 ማለትም የውጫሌ ውል በተለይም አንቀጽ አሥራ ሰባት አስቀድሞ የተሸረበ ሴራ ነው የሚል ግንዛቤ እንዲያድርባቸው አድርጓቸዋል፡፡

ኢጣሊያውያን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደረጉ በስተሰሜን ደግሞ ከአፄ ዮሐንስ ጋር የወረራ ዘመቻቸውን ያካሒዱ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ድንበር ዘልቀው በመግባት በጉንደትና በጉራዕ ላይ ጦርነት ለማድረግ ከሚችሉበት ሁኔታ ላይ ደረሱ፡፡ እንግሊዞችም የግብጽን ጦርና የውጭ አገር ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ከሱዳን ለማስወጣት ከፍተኛ ውለታ የዋሉላቸው አፄ ዮሐንስን በመካድ ኢጣሊያ ምፅዋን እንድትይዝ አደፋፈሯት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የጦር መሣሪያ እንዳይደርሳቸው ከለከሉ፡፡ በዚህና በወቅቱ በነበሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመሠረትም ጣሊያኖች ወደመሐል 30 ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት ሰሐጢን ያዙ፡፡ ነገሩ ‹‹የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ሆነና ብሪታኒያውያን የኢጣሊያ መልእክተኛ ወይም አስታራቂ በመሆን እንዲገለገል ሰር ጌራልድ ፓርታል የተባለ ዲፕሎማት ላኩ፡፡ የሽምግልናው መሠረታዊ ዓላማ አፄ ዮሐንስ ከማይችሉ አውሮፓዊ ኃይል ከሚጋፉ ይልቅ ሰሐጢን፣ ዊዓንና ከረንን ለኢጣሊያውያን እንዲለቁላቸው ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስም ይህንን አጉል ሽምግልና አልቀበልም በማለት ሰላም በእርግጥ የሚፈለግ ከሆነ ‹‹ኢጣሊያኖች ራሳቸው አገር ላይ ሆነው ኢትዮጵያውያንም ግዛታቸው ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው›› እንደሆነ በግልጽ አቋማቸውን አሳወቁ፡፡ ሰሐጢንም ለማስለቀቅ 80,000 ጦር አሰልፈው ነበር፡፡ ነገር ግን የሱዳን ማኅዲስቶች በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ወረራ አድርገው መተማን ያዙ፡፡ አፄ ዮሐንስም ጎንደር ድረስ ዘልቆ የገባውን የማህዲስቶች ጦር ለመውጋት ፊታቸውን ወደዚያው በማዞር ዘመቱ፡፡ እዚያም ሲዋጉና ድሉ ቀንቷቸው ለማሸነፍ ሲቃረቡ ቆሰሉ፡፡ ሲቆስሉም ድሉ ወደ ሽንፈት ተለወጠና በቆሰሉ በሁለተኛው ቀን አረፉ፡፡

አፄ ዮሐንስ ከማረፋቸው በፊት ግን ኢጣሊያውያን ንጉሥ ምኒልክ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ሊደረግ በሚችል ጦርነት ገለልተኛ እንዲሆኑና ለዚህም ውለታቸው 5000 ጠመንጃ እንደሚሰጧቸው ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ምኒልክም ከኢትዮጵያ መሬት አንዳችም አፈር እስካልነኩ ድረስ ብቻ ገለልተኛ እንደሚሆኑ አስታውቀው ነበር፡፡ ኢጣሊያም የምኒልክን አመለካከት ባለመቀበል የጦር መሣሪያ ርዳታውን አዘገየችባቸው….

አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ እንደሞቱም ንጉሥ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ነገሡ፡፡ እንደነገሡም ኢጣሊያ ራስ መንገሻ ዮሐንስን ‹‹የአባትህን ወንበር እናስመልስልሀለን›› በማለት እጎኗ ለማሰለፍ ሞክራ ነበር፡፡ በእርግጥም ወቅቱ የሥልጣን ሽግግር ዘመን በመሆኑ ኢጣሊያ ከጎኗ የሚሰለፉ ሥልጣን ፈላጊ ባላባቶችን አግኝታ ስለነበር ጭምር ከመረብ ምላሽ የሆነውን ግዛት ለመያዝ በቃች፡፡

ከዚህም ሌላ አፄ ዮሐንስ እንደሞቱ በአገሪቱ ከፍተኛ ረሃብ ስለነበር የአፄ ምኒልክ መንግሥትን እጅግ ከፍተኛ ችግር ገጠመው፡፡ በዚህም ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች እንደሞቱ፣ ለከብቶቹ መሞት ምክንያትም በግብርና የሚተዳደረው ሕዝብ የሚያርስበት ከብት አጣ፡፡ አንድ አምስተኛ የሚሆነው ሕዝብም አለቀ፡፡

ኢጣሊያውያንም በአንድ በኩል ከእንግሊዝ ያገኙትን ዲፕሎማያዊ ድጋፍ በጎላ በኩል ደግሞ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በመጠቀም አብዛኛውን የኤርትራን ደጋማ ስፍራ በ1889 ላይ ያዙ፡፡ በ1890 ላይም ‹‹ኤርትራ›› ብለው የሚመሯትን ቅኝ ግዛት መሠረቱ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ የሚበግራቸው አንድም የኢትዮጵያ ኃይል አልነበረም፡፡ ወዲውም የውጫሌ ውል ተፈረመ፡፡ ይህ ውል ግን ኢጣሊያን የኢትዮጵያ የበላይ (ፕሮቴክትሬን) የሚያደርግ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ደረሰው፡፡ ይኸው ውል ይስተካከል ዘንድም ራስ መኰንን ወደ ኢጣሊያ ተልከው ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውጫሌ ውል እንዲስተካከል መልእክተኛውን ወደሮም ብትልክም የኤርትራ ቅኝ ገዥ አዛዥ የነበረው ጀኔራል አንቶኒዮ ባለዴሴራ ደግሞ ከመረብ ባሻገር ያለውን ግዛት ለመውረር ይዘጋጅ ነበር፡፡

ራስ መኰንን ውጫሌ ስምምነት በተለይም አንቀጽ አሥራ ሰባት ትክክል አለመሆኑን ለመግለጽ ወደ ኢጣሊያ በሔዱ በወራቸው ኢጣሊያውያን ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ኢትዮጵያ የምታደርገው የውጭ ግንኙነት በኢጣሊያ በኩል መሆን አለበት›› ሲል አስታወቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ድሮውንም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እንድትያዝ ግፊት ስታደርግ የነበረችው ብሪታኒያ አስቀድማ እውቂያን ሰጠች፡፡ የድንበር ውልም ተደራደረች፡፡ ምኒልክም እንዲህ ያለውን ውል እንደማይቀበሉት ለዓለም አስታወቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ጦርነቱ የማይቀር ሆነና በ1887 ላይ ዓድዋን ከዚያም አዲግራትን በመያዝ ወደ መቀሌ ገሠገሡ፡፡ አምባላጌንም ተቆጣሩ፡፡ እንደተቆጣጠሩም ትግራይ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት መሆኑን አወጁ፡፡ ይህንን የተረዱት ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም. ላይ የክተት አዋጅ አወጁ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጦርም የመጀመሪያውን ጦርነት በአምባላጌ ላይ አደረገ፡፡ በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጀግንነት በተሞላበት ሁኔታ የተዋጉ ሲሆን የኢጣሊያ ጦርም ተደመሰሰ፡፡ ከአምባላጌ በኋላም የኢትዮጵያ ጦር ችግር የገጠመው እንዳየሱስ፣ ዕዳጋ ሐሙስና በአዲግራት በነበረው ምሽግ ነው፡፡

በዚህ ጦርነት ወቅት እንደራስ ስብሐት አረጋዊና ደጃዝማች ተፈራ ሐጎስ ያሉት የአጋሜ ባላባቶች ‹‹መሞት ካለብን ለእናት አገራችን ስንዋጋ እንሞታለን›› ብለው የኢጣሊያን ጦር በመክዳት ከወገኖቻቸው ጋር ሆነው እንደተዋጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በኢጣሊያ የመገናኛ መስመሮች ላይ ጥቃት አድርሰዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ጀኔራል ባራቲየር ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ገጠሞ ሊያሸንፍ እንደማይችል በመረዳቱ የሰላም ድርድር ለማድረግ ፈልጎ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ኢጣሊያ ውጫሌ ውል ያፈረሰችውን የ‹‹በላይ ጠባቂ ነኝ›› ባይነቷ ልታቆም ባለመቻሏ ከዚህም በላይ በያዘችው ስፍራ ሁሉ ባንዲራዋን በመስቀሏ ውይይቱ ከጅምሩ አንሥቶ የደከመ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒም ጦርነቱ እንዲቀጥል የቴሌግራም መልእክት አስተላለፈለት፡፡ ይኸው ቴሌግራም በተላለፈ በአራተኛው ቀን የዓድዋ ጦርነት ተካሔደ፡፡

የዓድዋ ጦርነትና የጦር አሰላለፍ

ዶክተር ዓለሜ እሸቱ ‹‹የአድዋ ጦርነት›› በሚል ርዕስ በ1970 ባሳተሙት መጽሐፍ እንደቀረበው፣ አፄ ምኒልክ የጦርነቱን ክተት አውጀው ከአዲስ አበባ የተነሡት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኅዳር 28  ቀን ላይ አምባላጌ ላይ ታህሳስ መቀሌ ላይ በተደረገው ዘመቻ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የፍልሚያው ስፍራ ዓድዋ ላይ የነበረ ሲሆን የካቲት 23 ቀን ያዘመቱት ጦር ቁጥር ግን በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተሰላው በተለያየ ቁጥር ነው፡፡

ዓድዋ ጦርነት ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች ከተማረከ በኋላ ነፃነቱን አግኝቶ ኢጣሊያ የተመለሰው የጄኔራል አልቤሮቶኒ ግምት ኢትዮጵያ ከ111,000 እስከ 122,000 ያህል ወታደሮች ያሰለፈች ሲሆን ከዚህም ውስጥ፡- ራስ መኮንን (ሐረር) ከ15,000 – 16,000 ጠመንጃዎች፣ ራስ ሚካኤል (ወሎ) ከ14,000 – 15,000 ጠመንጃ፣ ራስ ተክለሃይማኖት (ጎጃም) 5,000 – 6,000 ጠመንጃ፣ ራስ ወሌ 6,000 – 7,000 ጠመንጃ፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ — ከ3,000 – 4,000 ጠመንጃ፣ ራስ አሉላ ከ3,000 – 4,000፣ የአፄ ምኒልክ ከ33,000—38,000 ጠመንጃ፣ እቴጌ ጣይቱ ከ5,000 – 6,000 ጠመንጃ አሰልፋለች፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያን ሊጎበኝ የመጣው ሩሲያዊው የካውንት ሊኦንትየፍ ግምት ከ85,000 እግረኞች፣ 22,600 ፈረሰኞች፣ 42 መድፈኞች ተሰልፈዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት 20,000 ያህል የኢጣሊያ ጦር የተከማቸው ሳውሪያ (ኢንቲጮ) ላይ ሲሆን፣ ይህም ከዓድዋ በስተምሥራቅ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡ በአራት ጄኔራሎች የተከፈለ ነበር፡፡ እርሱም፡- ጄኔራል ዳቦርሜዳ… የቀኝ ብርጌድ 3500 ወታደሮችና – 18 መድፎች፣ ጄኔራል አልቤርቶኒ …የግራ ብርጌድ – 8300 ወታደሮችና 12 መድፎች፣ ጄኔራል አሪሞንዲ … የመሐል ብርጌድ – 2900 ጠመንጃዎችና 12 መድፎች፣ ጄኔራል ኤሌና … ተጠባባቂ (ሪዘርቭ) ብርጌድ 3350 ወታደሮች በመድፎች ነበሩት፡፡

አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓድዋ ላይ የካቲት 7 ቀን ኢጣሊያኖች ደግሞ ኢንቲጮው ላይ የካቲት 6 ቀን ካሰፈሩ በኋላ የሁለቱ ወገን ሠራዊት ተፋጠው እስከ የካቲት 23 ቀን ድረስ ቆይተዋል፡፡ እስከዚያ ዕለትም ሁለቱም የተፋጠጡ ወገኖች ሌላውን ሲሰልለው ሰንብቷል፡፡ በመጨረሻም ኢጣሊያኖች በደረሳቸው መረጃ መሠረት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሠራዊት ገሚሱ ቀለብ ፍለጋ ወደሽሬና ወደተንቤን እንዲሁም ተከዜን ተሸግሮ ወደጸለምት ተበትኗል፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አክሱም ጽዮን እሑድ የሚውለውን የጊዮርጊስ በዓል ለማስቀደስ ሔደዋል›› የሚል በመሆኑ በየካቲት 23 ቀን እሑድ የጊዮርጊስ ዕለት በአጥቂነት የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ወሰነ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ገብረሥላሴ እንደሚለውም (ገጽ 262) ቀለብ ፍለጋ አክሱም ጽዮን ከሔዱት እሑድ ለጦርነቱ የተመለሱት ከሦስት እጅ ሁለት እጅ ነበሩ፡፡

የዓድዋ ጦርነት በጆርጅ ኤፍ በርክሌይ እይታ

ጆርጅ ኤፍ በርክሌይ የተባለ ጸሐፊ ‹‹የዓድዋ ዘመቻና የምኒልክ አነሣሥ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፉ በዳኛው ወልደሥላሴ ተተርጉሞ እንደምናነበው፡፡ … አፄ ምኒልክ ሆኑ የኢጣሊያው የጦር መሪ ባራቲየሪ ቀድመው ለማጥቃት ሳይዳዳቸው የጠላት ስንቅ እንዲያልቅ እየተመኙ ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ሳይጀምሩት ስንቃቸውን ወደመጨረሱ ተቃርበው ነበረ፡፡

ድል በመምታት መበቀልን የፈለገው የሮማ ሕዝብ ውሎ ባደረ ቁጥር ተስፋ እየቆረጠ በመሔዱ የባራቲየሪም ክብርና ዝና ወደቀ፡፡ የካቲት 15 ቀን በምሥጢር ባራቲየሪ ተሸሮ ጄኔራል ባልዲሴራ የጦሩ አዛዥ እንዲሆን ተሾመ፡፡

ይሁንና ይኸው የጦር መሪ የካቲት 21 ቀን በማይ ገገበታ በኩል ወደማይ ማረት ለማፈግፈግ ወስኖ መንገድ ከጀመረ በኋላ በዚሁ ምሽግ አራቱን ጄኔራሎች ሰብስቦ ያለው ምግብ እስከ የካቲት 23 ወይም የካቲት 24 ቀን ድረስ ብቻ የሚያቆያቸው መሆኑን ካስረዳ በኋላ ወደሰንአፌ ለመሸሽ ወይም አስፈላጊው ጥናትና ዝግጅት እንዲያደርጉ አማከራቸው፡፡ (በዚህ ጊዜ) ጄኔራል ዳቦርሜዳ፣ የጄኔራል ባራቲየሪን ንግግር ከሰማ በኋላ መሸሹ የማይደረግ ነው ብሎ ስሜቱን ገልጾ ምክንያቱን ማስረዳት ጀመረ፡፡ አንደኛ የኢጣሊያ ሕዝብ ከምናሳፍር 3,000 ወታደር ቢሞትብን ይመረጣል፡፡ ሁለተኛ የወታደሩ ሞራል በጣም ይወድቃል፡፡ ሦስተኛ ጠላቶቻችን ከኛ ፈጥነው ለመጓዝ ስለሚችሉ አሁንም በመሸሽ ላይ ሳለን ደርሰው ለራሳቸው ከሚያመቻቸውና ከመረጡት ቦታ ላይ አደጋ ሊጥሉብን ይችላሉ፡፡ ይህ ከሚሆን ወጥተን ማጥቃቱ ይሻላል ሲል አሳሰበ፡፡

ጄኔራል አልቤርቶኒም የጄኔራል ዳቦርሚዳን አሳብ ደግፎ ‹‹የጠላት ጦር ምግብ ለመሰብሰብ የተበታተነ ከመሆኑም በላይ ብዙውም ወደአገሩ በመመለስ ላይ ነው፤›› በማለት የአበሻው ጦር ሰፈር በሁለት መሪዎች የተከፈለ ከመሆኑም በላይ ከ14,000 ወይም ከ15,000 ጦር በላይ እንደማይኖረው ገለጸ፡፡

በሁኔታው አፄ ምኒልክም በጣም ተጨንቀዋል፡፡ የቀራቸው ሦስት ወይም ለአራት ቀን የሚሆን ስንቅ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ከምሽጉ ወጥቶ ማጥቃት እንዲጀምር ብርቱ የሆነ ጸሎታቸው ነበር፡፡ ይህንንም ዕድል ለማግኘት ለባራቲየሪ እንዲደርስ የሚያስወሩት ፕሮፖጋንዳ  ‹‹በአፄ ምኒልክ የጦር ሰፈር ችግርና ረሃብ ጸንቶ ሠራዊቱ እየሸሸ በመሔድ ላይ መሆኑና ዙሪያውም የሚገኘው ሕዝብ ተነሥቷል›› የሚል ነበር፡፡

አጼ ምኒልክ እንደተመኙትም የካቲት 22 ቀን ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጄኔራል ባራቴሪ ወጥቶ ለማጥቃት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ፡፡

የባራቴሪ ዓላማ በሦስት አቅጣጫ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ የጠላት ጦር ሳያውቅ በተራራው ገመገም ስር ለመመሸግና የመከላከያ ቦታ ለመያዝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የጠላት ጦር ቢያጠቃ መልካም፣ ካልሆነም የአበሻን ጦር ፍርሃት እንዲያድርበት በዙሪያው ለሚገኘው ሕዝብ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣሊያ ጦር ተንቀሳቅሶ የነዚህን ተራራዎች ገመገም በሚይዝበት ጊዜ የአበሻው ጦር በርግጎ ወደኋላ ይመለሳል የሚል እምነትና ተስፋ ነበረው፡፡ ይህም ከሆነ ዓድዋን በሰላም (ያለችግር) ለመያዝ እንደሚችልም ገምቶ ነበር፡፡ የጦሩ አሰላለፍም፡፡

ሀ. በቀኝ በኩል በጀነራል ዳቦርሜዳ የሚመራው የበላህን ተራራ አምባ፣ የበላህን ጎጥና በዙሪያው ያለውን ቦታ፣

ለ. በመካከል በጀነራል ኦሪሞንዴ የሚመራው የበላህን ተራራ

ሐ. በግራ በኩል ‹‹በጀነራል አልቤርቶኒ የሚመራው ኪዳነ ምሕረት ብለው የጠሯትና (ለዚች ተራራ የተሰጠው ስም በትክክል አልነበረም) ራይ የተባሉትን ተራራዎች እንዲዝ፣

መ. በጄኔራል ኤልና የሚመራው ተጠባባቂው ጦር ጦር ረቢ አርየኒ በተባለው ቦታ ሆኖ እንዲጠባበቅ፣

የቀኑ ትእዛዝም ‹‹የካቲት 22 ቀን 1888 ቁጥር 87 ዛሬ ማታ ጦሩ በሦስት አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚከተለው ሁኔታ ይቀንሳል፡፡

… የቀኙ ክፍል ጄኔራል ዳቦርሚዳ 2ኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ የሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ሻለቃ ጦር የ2ኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ የ5ኛ፣ የ6ኛ፣ የ7ኛ ከባድ መሣሪያ ጓድ፡፡

…ግራው መስመር በጄኔራል አልቤርቶኒ (የሚመራ ሆኖ) አራት የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር የአንደኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ ከ1ኛ ፣ ከ2ኛ፣ ከ3ኛ፣ ከ4ኛ ከባድ መሣሪያ ክፍል ጋር፡፡

ተጠባባቂ ጄኔራል ኤሌና፣ 3ማ እግረኛ ብርጌድ፣ 3ኛ የአገሬው ተወላጅ ያለቃ ጠር ሁለት የመትረየስና የከባድ መሣሪያ ጓድና አንድ ኮፖኒ መሐንዲሶች፡፡

…ጄኔራል ዳቦርሚዳ፣ በአርሞንዲና በአልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ሲታዘዝ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ተጠባባቂው ጦር የመካከለኛውን መሥመር ተከትሎ ይንቀሰቀሳል፡፡

…የቀኙ ረድፍ በዛሃላ ጎጥ አድርጎ ጎልደም ጎጥን አልፎ ወደረቢ አርእየኒ ጎጥ ይጓዛል፡፡ የመካከለኛው ተጠባባቂ ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንድብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንደብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ደግሞ ከሶሎዳ በአዲ ቸራይራ በኩል ወደኪዳነምሕረት ይጓጓል፡፡…›› የሚል ነበር፡፡ (በዚህም ዓይነት ኢጣሊያኖች ብዛቱ 100,000 የሚሆን የጦር መሣሪያ ጦርና ጋሻ የያዘውን የአበሻን ሠራዊት ለመግጠም 17,700 ወታደርና 56 መድፍ ጠምደው ተሰናድተዋል፡፡

በዶክተር ዓለሜ እሸቴ መጽሐፍ መሠረት አፄ ምኒልክ ኢጣሊያኖችን ኢንቲጮ ድረስ ሔደው ለመውጋት ያልፈለጉበት ምክንያት ቦታው ለአጥቂ ጦር የማያመች እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ጀኔራል አልቤርቶኒ የታዘዘለትን ትክክለኛ ጦር ሠፈር በመፈለግ ከሌሎቹ የኢጣሊያ ብርጌዶች ተነጥሎ ኪዳነምሕረት ኮረብታ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲደርስ፣ በሜጀሪ ቱሪቶ ይመራ የነበረው የብርጌዱ ግንባር ቀድሞ ጦር ቀደም ብሎ በመድረሱ በዚህ ቀን በጥበቃ ተራ ላይ ከነበረው ከራስ መንገሻ ዮሐንስ እንዲሁም ጥቂት ቆይቶም ከዋግሹም ጓንጉል፣ ከደጃች ገሠሠና ከበጅሮንድ ባልቻ ሠራዊት ጋር ውጊያ እንደጀመረ ኮንቲሮዘኒ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ መዝግቦታል፡፡

ይኸው ኮንቲሮዚ የተባለው ጸሐፊ ዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ያስቀድሱ የነበሩት አጼ ምኒልክ፣ የኢጣሊያ ወታደር በዚህ ቀን ጦር ለማድረግ መወሰኑን በተረዱ ጊዜ ሠራዊታቸውን በያለበት ቀስቅሰው ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ሆነው ከዓድዋ ተነሥተው በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አባ ገሪማ ኮረብታ ላይ ሰፍረው ነበር፡፡ የአልቤርቶኒ ብርጌድ ኪዳነምሕረት እንደሰፈረና ግንባር ቀደሙም ጦር አልፎ መምጣቱን እንደሰሙ በነፊታውራሪ ገበየሁ፣ በነደጃዝማች በሻህ አቡ፣ የሚመራውን የራሳቸው ጦር ፊት ለፊት፣ የእቴጌ ጣይቱንና የጎጃሙን ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር በስተግራና በስተቀኝ እንዲዘምቱ አዘው ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ጦርነቱ ተጀመረ፡፡

…ከዚያ በኋላ ነጋሪት መቺው ‹‹ውጋ! ውጋ!›› እያለ፡- እየተበረታታ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በግራና በቀኝ በሁሉም አቅጣጫ ከቦ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ አብረው በሚያዙት ላዳት (አባ ገሪማ አጠገብ) 3 ኪሎ ሜትር ከጠላት ሠፈር ርቆ ይገኝ የነበረውን የኢትዮጵያ ከባድ መሣሪያ (መድፍ) እየተደገፈ፤ በጄኔራል አልቤርቶኒ ይመራ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ደመሰሰው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ተኩል ሲሆን ጄኔራል አልቤርቶኒ የተረፉ የኢጣሊያ ወታደሮች መድፈኞች ወደኋላ እንዲሸሹ አዞ ነበር፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሠራዊት ማየል ጄኔራል አልቤረቶኒ ከብዙ መቶ ኢጣሊያኖች ጋር ተማረከ፡፡ … ጦርነቱም ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ ሲሆን አበቃ፡፡

ወደ ሰላም ምሥረታ

ከዓድዋ ጦርነት በኋላም የኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ መሐንዲስ እየተባለ ይጠራ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ከሥልጣኑ ለቀቀ፡፡ ያም ሆነ ይህ ጄኔራል ባራቲየሪም ኢትዮጵያን ድል ለማድረግ ባለመቻሉ በጦር አመራር ብቃት ማነስ ምክንያት በሕግ ተጠያቂ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ግን ዓለም አቀፍ ክብርንና ሞገስን አገኘች፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የተመረጠው አንቶኒዮ ስታራባም ክሪስፒ ያራምደው የነበረውን የመስፋፋት ፖሊሲን እንደማያራምድ በማስታወቅ ሁለቱን አገሮች የሚያስማማ መንገድ መከተል መረጠ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፓፕ) ሊዮ 13ኛን በማሳመን አፄ ምኒልክ ለያዟቸው የኢጣሊያ ምርኮኞች ምሕረት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ በግንቦት 1888 ዓ.ም. ላይ እንዲጽፉ አደረገ፡፡ አፄ ምኒልክም በምሕረቱ በመስማማት የመልቀቁ ሁኔታ ኢጣሊያ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ባላት ፍላጎት ላይ የሚወሰን መሆኑን አሳወቁ፡፡

አብዛኛው ጊዜ ‹‹የአዲስ አበባ ውል›› እየተባለ የሚታወቀውና በውሉ ርዕስ እንደሰፈረው ለዘላለም የሚዘልቅ የሰላም የወዳጅነት ተብሎ የሚታወቀውን ስምምነት ጥቅምት 15 ቀን 1889 ዓ.ም. ተፈረመ፡፡ በዚህ ውል ኢጣሊያ ውጫሌ ውል እንዲሰረዝና ፍጹም ነፃ አገር መሆኗን አወቀች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...