Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የቱሪዝም ገጽታ ግንባታና ያልተፈለቀቀው ጥጥ

በደበበ ስሜነህ

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የግል ብቻ ሳይሆን በጥናት ላይ የተመሠረቱ የመወያያ ምልከታዎቼን ማስፈር እወዳለሁ፡፡ እርግጥ ርዕሰ ጉዳዩን ለመምዘዝ ያነሳሳኝ ሁነት፣ ሰሞኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ‹‹ቱሪዝምና ገጽታ ግንባታ›› የሚል ውይይት በተለይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲመክር ማየቴ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ጅምር መድረክ መልካም ቢሆንም፣ አገራችን ያሉዋትን ገና ያልተነገራላቸው በርካታ ቱባ የቱሪዝም ሀብቶች ያህል ያለመጠቀም እጅጉን የሚያስቆጭ ነው፡፡ አሁን ባለው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠቃለያ ከዘርፉ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር  በላይ ገቢ ማለፍ ካለመቻሉም በላይ፣ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥርም አንድ ሚሊዮን በዓመት እንኳን አለመድረሱን ነው መረጃዎች የሚያስረዱት፡፡ በአገራችን የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ባህል ባለመጎልበቱ ምክንያት ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ 10 በመቶ ዕድገት እንኳን አለመምጣቱን አንድ ጥናት ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ዜጎች እንዲያውም ወደ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች የሚያደርጉት ጉዞ ይበልጣል፡፡  

ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው (ጭስ አልባ የሚለው ቀርቷል) መቀጨጭ አሁን ያለውን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና መንግሥት ብቻ መውቀስ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በዋናነት ለዘመናት ከኖርንበት የድህነት፣ የረሃብ፣ የጦርነትና የኋላቀርነት ጨለማ ዘመን ጋር ይይያዛል፡፡ ያለንን የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የቀደመ ሥልጣኔ ወርቅ ጥጥ ሳይፈለቀቅ ለዘመናት እንዲበሰብስ ያደረገው ያ ዘመን ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡

ሁለተኛው ከሕዝቡ ግንዛቤና ከኢኮኖሚ መድቀቅ ጋር የሚያያዘው ሀብትን የጋራ አድርጎ የመጎብኘት ልምድ ማነስ ነው፡፡ ዘጠና ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት ያውም በፍጥነት እያደገች ያለች አገር ነች እየተባለ፣ በአገር ውስጥ የጉብኝት ባህልን እንደ መሠረታዊ ጉዳይ የሚመለከተው ሕዝብ ከሁለት በመቶ በታች ነው መባሉ ዘርፉ ምን ያህል እንደ ወደቀ ያሳያል፡፡ (እዚህ ላይ ግሎባል ቱሪዝም ኢንዴክስ የተባለ ዌብ ሳይት በጥናቱ የአፍሪካ አማካይ ስድስት በመቶ ሲያደርሰው፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ አልጄሪያ፣ ወዘተ ያሉት አገሮች ከ10 እስከ 20 በመቶ ዜጎቻቸው በየዓመቱ የጉብኝት መርሐ ግብር ያወጣሉ፡፡ በአውሮፓና አሜሪካም እስከ 60 እና 70 በመቶ ይደርሳል)

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ብሎ ያቋቋመው አካል አለ፡፡ ምን እየሠራና የትኛውን ዕርምጃ ወስዶ የመጣ ለውጥ እንዳለ ባይታወቅም፣ በየስድስት ወራት ይሰበሰባል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከ330 የማያንሱ ሕጋዊ አስጎብኝ ድርጅቶችን ሰብስቦና አደራጅቶ የሚመራው ሥራ እንዳለም ይታወቃል፡፡ ክልሎችና ፌደራል መንግሥት በአገሪቱ ያሉ ቅርሶችን በመለየት፣ በመመዝገብ (አንዳንዶቹንም በዩኔስኮ ደረጃ ለማሳወቅ) የሚደረግ ጥረትም አለ፡፡ ከእነዚህ ተግባራት በላይ የአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ‹‹ከነካ ነካና ቀባ ቀባ›› አካሄድ ፈንቅሎ ወጥቶ፣ አገርና ሕዝብ እንዲጠቅም በተጨባጭ የአገሪቱን ገጽታ ከፍታ ላይ ለማድረስ ችግሮችና መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች መንቀስ እፈልጋለሁ፡፡

እዚህ ላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እያደገ ስለሆነ ‹‹ምን እያልክ ነው!?›› የምትሉ ተቆጪዎች ካላችሁ አዎ በማደግ ላይ ነው እላችኋለሁ፡፡ ነገር ግን አገራችን ያላትን መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህልና ሀብት ይቅርና ሩብን ያህል እንኳን የሌላቸው ጎረቤት አገሮች ቱሪዝምን ምን ደረጃ ላይ እንዳደረሱት ማጤን ተገቢ ነው፡፡ እነ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ ቢሊዮን ዶላሮች የሚዝቁበት የኢኮኖሚያዊ ገበያቸውን 30 በመቶ ድረስ የሚሸፍን ግዙፍ ዘርፍ ቱሪዝም ነው፡፡ እነ ህንድ፣ ቻይናና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የተመለከተ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታዩ ጥቂት የነጭ ጎብኝዎች ተጋርዶ ለውጥ መጥቷል ቢል ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ለውጥ አንፃራዊ መሆኑን ባልዘነጋም ‹‹በጥቂቱ ከመኮፈስ›› ወጥቶ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መትጋት ይገባል ስል ምክሬን ልለግስ እወዳለሁ፡፡

የአገራችን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና ልዩ ገጽታ አልተዋወቀም

የአገርን ገጽታ ለማስተዋወቅ የሚረዳው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ገና ከብሔር ብሔረሰብ አጥር አልወጣም፡፡ በመንግሥት እጅ ተይዘው የሚገኙ መገናኛ ብዙኃንም ቢሆን በአገር ውስጥ ፖለቲካ ተጠምደው ‹‹በልማታዊ›› መንገድ በመሥራት ወጣ ብለው ኢትዮጵያ የምትባል ቀደምትና ታላቅ አገር መኖሯን መስበክ አልጀመሩም፡፡ የአገሪቱ ፖርታል ዌብ ሳይት እንኳን ተንገዳግዶ በእግሩ እየቆመ ያለው በቅርቡ ነው፡፡ ውድም ቢሆኑ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለቸው የቴሌቪዥን ቻናሎች ለአንድ ሰከንድ እንኳን ራሳችንን ማስተዋወቅ አልቻልንም፡፡ በዚህ በኩል ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ይበልጡናል፡፡

ይቅርታ ይደረግልኝና አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይስ መግባባት አለ ወይ? የትኛውን ተስማምንበት ነው የምናስተዋውቀው? ለአብነት ብንጠቃቅስ ‹‹አደዋ! የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች ድል ሆኖ ሳለ ምን ያህል ተናግረንለታል? ቦታውንስ እንዴት ጠብቀን አስተዋውቀናል? እኛ ራሳችን አደዋንና ታሪኩን እናውቀዋለን? አሁን አሁን ዓመታዊ በዓሉም ደብዝዞ እየተከበረ ምንሊክን የሚጠላ›› የአደዋ ድል ሊያንቋሽሽ የሚያምረው ኃይል እየተፈጠረ አይደለም እንዴ? መንግሥትስ ቢሆን ስለአድዋ፣ ዶጋሊ፣ ማይጨው፣ ጉንደትና ጉና፣ ወዘተ ጀግኖች ማውራት መቼ ይቀናዋል? ይልቁንም የእርስ በርስ ጦርነቱ ታሪክ አይደለም እንዴ አገር ምድሩን ይዞት ያለው?

በዚህ አገር ያለው ታሪክ ብቻ ሳይሆን እየደበዘዘ ያለው የቅርስ ትውውቅና ጥበቃውም ቢሆን መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች የሦስት ሺሕና የአራት ሺሕ ዓመታት ቅርሶቻቸውን ባማረ ሕንፃ በጥበቃ (በታንክ ሳይቀር የሚጠብቁ) ይዘው ሳለ፣ እኛ እጃችን ላይ እየፈረሱ ያሉ ሐውልቶች፣ ዋሻዎች፣ ገዳማትና መስጊዶች ስንት ናቸው? ቅርሳ ቅርሱ፣ የነገሥታት አልባሳት፣ ጌጣ ጌጡና ሽልማቱ ሁሉ ቁጥሩ ታውቆ ተመዝግቦ ስለመያዙ ማን በድፍረት ሊናገር ይችላል?

እዚህም ላይ የተሳሳተው አካሄድ የተንሻፈፈ ፖለቲካዊ ምልከታ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ክልሎች በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አካባቢ ያሉ ቅርሶችን እንደ ሕዝብ ቆጥሩ የመጠበቅ ፍላጎት አይታይም፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ ምልክቶች እንዳሉ የሚያሳየው በቀደምት ታሪክ የሚታወቁ ቦታዎች፣ ጎዳናዎችና ቅርሶች ከ20 ዓመታት ወዲህ በፍጥነት ለመቀየር እየተሠራ መሆኑ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ንብረት እኮ የአገር ሀብት ነው፡፡ ግብፅ ውስጥ የመጀመሪያው የኦሮቶዶክስ ገዳምና ማርያም የተሰደደችበት ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ቅርሳቸው ነው፡፡ የቱሪስት መዳራሻቸው በመሆኑም እንደ ትልቅ ቁሳዊ ሀብት ቆጥረው በጥንቃቄ የሚያስተዋውቁት ነው፡፡ ከእስልምና መስፋፋት ጋርም ሆነ አሁን እየፈላ ያለው አሸባሪ ጥቃት እንዳይደርስበት (የገቢ ምንጭ ነውና) በኩራት ይዘውታል፡፡ ሶሪያም ቢሆን አይኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን እያወደመው ያለው ሀብት ከፍተኛ ጥፋት ቢደርስበትም፣ በእስላማዊቷ አገር የክርስትና ሀብቶች ቢሆኑም የአገር ቅርስ ሆነው ነው እየተጠበቁ ያሉት፡፡

በእኛ አገር ግን የብሔር ፖለቲካ ገዳም ውስጥ ገብቷል፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች ኦርቶዶክስ የለም የሚለው ማን ነው? ካልጠፋ ቦታ የኖረውን የታሪክ ሀብት አፍርሶ ሌላ ‹‹ሀብት›› ለመተካት መፈላለግን ምን አመጣው? ማንንም ሊያሳስብ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ሰሞኑን አስጎብኚ ድርጅቶች በገጽታ ግንባታ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ይኼን አላነሱትም፡፡ አገሪቱ እንዴት ያላትን ክፉም ሆነ ደግ ታሪክ ጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፍና ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ አለባት የሚለው ሐሳብም አላስጨነቃቸውም፡፡ ይልቁንም ተግባሩ የሚናቅ ባይሆንም፣ የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ እንዴት ማስተዋወቅና ማስተናገድ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ (ሀብቱ እየጠፋ ከሄደ ግን የሚመጣውም እንደሚቀር መዘንጋት የለበትም)

ተወያዮቹ የአገራችን የቱሪዝም መለያ (ብራንድ!) ሊኖር ይገባል ሲሉ የገለጹት አፅንኦታዊ ምክር ተገቢ ነው፡፡ ግን በቱሪዝም መስህብ ቅርሶቻችን ላይ ሁላችንም የተግባባንበት ፍልስፍና ምንድነው? ብሎ መነሳት ይገባል፡፡ የኦርቶዶክስ ዋነኛ የሃይማኖቱ ቅርሶች የዕምነቱ ተከታዮች ብቻ ያውም የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተደርጎ ከተሰላ፣ እንደ አገር ሀብት ሊታይ አይችልም፡፡ ከወላይታ ወይም ከቦረናና ከጅጅጋ አክሱም ድረስ ሄዶ ገዳማቱን ሊመለከት አይሻም እንኳን ሊያስተዋውቀው የሚባለው ከንቱ ወሬ አይሠራም፡፡

በታሪካችንም ላይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተከበረው ‹‹የአርበኞች ቀን›› በአዲስ አበባ ከተማ ፋሽቱ የጣሊያን መንግሥት ከ30 ሺሕ በላይ ዜጎችን በአንድ ቀን የጨፈጨፈበት የመታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ለጉዳዩ መንግሥት የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ በስድስት ኪሎ አደባባይ ከተሰበሰበው የአገሬው ሰው የውጭ አገር ዜጎች የበዙ ይመስለኛል፡፡ የተገኙት እንግዳም በአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ገና ለጋ ካድሬ ናቸው፡፡ (አስቡት ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ከከንቲባና ምክትል ከንቲባም ወርዶ የግብር ይውጣ ሲሆን) ይኼ ነገር ሆን ተብሎ ባይሆን በፍፁም ሊደረግ አይገባም፡፡

አሁን ካለው የጣሊያን መንግሥት ጋር በጎ ግንኙነት ለመፍጠር ነው ቢባል እንኳን ተቀባይነት የማይኖረው፣ ጀርመናዊያን የራሳቸው ሂትለር ለጨፈጨፋቸው ንፁኃን የሌላ አገር ዜጎች መታሰቢያ እንኳን በድምቀት ማክበራቸው ነው፡፡ በአሜሪካ የጥቁሮች ቀን፣ የነፃነት ዕለት፣ የተጋድሎ ሳምንት፣ ወዘተ እያሉ የሚዘክሩት ከታሪካቸው ማህደር ላለመውጣት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በእኛ አገር በወቅቱ የተጠቃው የእገሌ ብሔር፣ የዚያ ሃይማኖት፣ የዚህኛው አቅጣጫ ሕዝብ ነው እያልን የዚች አገር ታሪክ የ20 ዓመታት ካስመሰልነው ሁሉም ነገር ይቀራል፡፡

ይኼን ሐሳብ ለመደምደም የአገራችን የቱሪዝም መለያ (ብራንድ) በጋራ መግባባት ለመፅደቅ በቅድሚያ ፍልስፍናችን ይታወቅ፡፡ በታሪካችን እንግባባ፡፡ አንዱ አክሱምን ጠርቶ የሦስት ሺሕ ዘመን ሲል ሌላው 100 ዓመት ይላል፡፡ (በነገራችን ላይ እዚህ ላይ ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ይወዛገባሉ) የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የጎሳ ቅርፅ ማለቱን ትተን አገራችን መስህብ መሆን አለባት፡፡ ሀብትን ሁሉ እንደ አገር ቅርስ እንውሰድ፡፡ ይኼን አድርጎ ለኢንዱስትሪውን አስፈላጊውን ዕውቀት፣ ሀብትና አመራር በመስጠት ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገር ይቻላል፡፡

የአገር ውስጥ ጉብኝት ላይ አልተሠራም

ከእኛ አገር የዕድገት ደረጃና የነፍስ ወከፍ ገቢ አንፃር የሚወዳደሩ አገሮች ሕዝቦች የአገር ውስጥ የጉብኝት ባህል የተሻለ የሚባል መሆኑን አይተናል፡፡ የእኛ ግን ዝቅተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የሚደግምም አይመስልም፡፡ ለዚህ እንደ ችግር የሚመስሉኝ ነጥቦች አሉ፡፡

አንደኛው ቀደም ሲል በስፋት እንዳነሳሁት በታሪኩና በቅርሱ የተግባባና መኩራት የጀመረ ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት፡፡ በማንነቱና በቀደመው ትውልድ በጎ ሥራ የማይቀና ትውልድ ‹‹ቅርስ›› ቢሉት ሊያዳምጥ አይሻም፣ ሊጓጓም አይችልም፡፡

ሁለተኛው የጉብኝት ልምድን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማጠናከር ነው፡፡ በክበባት፣ በማኅበራትና በልዩ ልዩ አደረጃጀት መነሳሳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ጅምሮች ቢኖሩም ገና ለጋ ናቸው፡፡ የመንግሥትም ሆኑ የግል መሥሪያ ቤቶችም ሠራተኞቻቸውን በመደገፍ ቅርሶችና መስህቦችን የማስጎብኘት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲካዊ ፍላጎቱ ከፍ ያለ ስለሆነ በቅርቡ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ደደቢትና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላሉት ሁነቶች ከፍተኛ በጀት እየተያዘ ሕዝብ ይንቀሳቀሳል፡፡ የቱሪዝም መስህቦቻችንስ?

ሦስተኛው የሆቴሎችንና የጉዞ ወኪሎችን የማስፋፋትና የማጠናከር ጉዳይ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በተመረጡ ጊዜዎች የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች መነቃቃት መስዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የመንግሥት፣ የሚመለከታቸው አካላትና መገናኛ ብዙኃንም ማንቃትና ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ግን ቀዳሚው ነገር በቅርሶችና በሀብቶች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ማስቀደም ነው፡፡

የአገር ጉብኝት ዝንባሌ ለማሳደግ የሌሎች አገሮች ተሞክሮንም መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በግሌ እዚህ ላይ የተለያዩ አገሮች ሁኔታ ሲፈተሽ የግድ በሺሕ ዓመታት ታሪክና ቅርስ ላይ ብቻ አይንጠላጠሉም፡፡ የቅርብ ጊዜ ግጭቶች ወይም የልማት ውጤቶችም ሆነ መታየት ያለባቸውን ሥፍራዎችን መስህብ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ተራራና ሸንተረሮች፣ ትልልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ወዘተ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በአዲስ አበባችን የዓባይ ወንዝ ድልድይን ሳያውቅ ስለሜሴፖታሚያ ወንዝ፣ ስለፓስፊክ ውቅያኖስ ወይም ስለጋዛ ሰርጥ በብዛት የሚናገሩ ይደመጣሉ፡፡

በአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማበብ ላይ ሌላው መሠራት ያለበት ጉዳይ ባለፈው ሳምንት እንደታየው ባለድርሻ አካላት ላይ መሥራት ነው፡፡ ከአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከጉዞ ወኪሎችና ከሾፌሮች ጀምሮ በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ግልጽነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ፣ የዋጋ አጠያየቅ፣ የአገሪቱን ትክክለኛ ገጽታን ማስገንዘብ፣ በጊዜያዊ ፖለቲካዊ ትርፍና ስሜታዊነት ገጽታን ላለማበላሸት የሚጣልባቸው አገራዊ ኃላፊነት ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አደረጃጀቶቻቸውን እንደ ዋነኛ መሣሪያ መጠቀም ይገባል፡፡

በተለይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች ረገድ ብዙ ሥራ ያስፈልገናል፡፡ ሆቴሎች ምግብና መኝታ ብቻ ሳይሆን ደኅንነት፣ ትራንስፖርት፣ መረጃና ሕክምና እንዲሁም መዝናኛን የሚያሟሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በእኛ አገር የሆቴሎች ቁጥር ቢጨምርም ፓርኪንግ የሌላቸውና አረንጓዴ ቦታ አልባ ‹‹አፓርታማ›› የሚመስሉ ብዙ ናቸው፡፡ ከውኃና ከተራራ ጋር እንዲሁም ጭልጥ ባለ ጫካና በረሃ ሆቴሎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የግል ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ እንደ መከላከያ፣ ፖሊስና ራሱ ባህልና ቱሪዝም በሆቴል ኢንዱስትሪው ገብተው መልሰው ቀስ በቀስ እጃቸውን ቢያወጡ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

በአጠቃላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በአገራችን ያለውን የወርቅ ጥጥ ፈትል ሊፈለቅቅ ግድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁርጠኛ የመንግሥት አቋምና ተነሳሽነት ሊኖር የግድ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

     

     

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles