የዘውዲቱ ሆስፒታል የዴያሊስስ ሕክምና ማዕከል፣ ዴያሊስስ ወይም የኩላሊት እጥበት ከመደረጉ በፊት ሕክምናው የተዋጣ እንዲሆን የሚያስችል የቅድመ ዴያሊስስ ሕክምና መስጠት ጀመረ፡፡ ሕክምናው የሚሰጠው የቆየ የዴያሊስስ ችግር ላለባቸው ሕሙማን ሲሆን፣ ሕክምናው የሚከናወነው የአርተሪ እና ቬን ፌስቱላ ኦፕሬሽን በማድረግ ወይም የደም ቅዳና ደም መልስ ስሮችን በቀዶ ሕክምና በማገናኘት ነው፡፡
ዶክተር ተስፋዬ ይልማ የማዕከሉ የኩላሊት ሕክምና ስፔሻሊስት እንደሚሉት፣ ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የተውጣጡና በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ስምንት የሕክምና ስፔሻሊስቶችና ባለሙያዎች የሕክምና አገልግሎቱን በነፃ እየሰጡ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮና በኩላሊት እጥበት ማኅበር አማካይነት ከመጡት ስፔሻሊስቶችና ባለሙያዎች መካከል አብዛኞቹ በማዕከሉ ሥራ የጀመሩት ከአንድ ሳምንት በፊት ሲሆን ዋናው ስፔሻሊስት እና ረዳቶቻቸው ደግሞ ከየካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሕክምናውን እያከናወኑ ነው፡፡
ስፔሻሊስቶቹና ባለሙያዎቹ በጠቆሙት ዲዛይን መሠረት የሕክምና መስጫ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን፣ ባለሙያዎቹ ደግሞ መሣሪያዎችን ከአገራቸው ይዘው መምጣታቸውንና አገልግሎቱ መጀመሩን ዶክተር ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
ስፔሻሊስቶቹና ባለሙያዎቹ እስከ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በአገልግሎት ላይ የሚቆዩ ሲሆን፣ ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይዘው ካመጧቸው የሕክምና መሣሪያዎች መካከል ግማሹን ያህል ለማዕከሉ የሚያበረክቱ ይሆናል፡፡
በቆይታቸው ወቅት የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማከናወን እንዲቻል ከተለያዩ የሕክምና ተቋማት የተውጣጡ ሐኪሞች አብረዋቸው እንዲሠሩ የተደረገ ሲሆን፣ ሙያው ጥልቅ ሥልጠና የሚፈልግ በመሆኑ ተጨማሪ ትምህርት እንዲሰጡ በተጠየቁት መሠረት በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ላይ ተመልሰው እንደሚመጡ ታውቋል፡፡
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የዴያሊስስ ሕክምና በሆስፒታሉ በሚገኘው ማዕከል መሰጠት የሚጀምር ሲሆን፣ ለዚህም 20 የዴያሊስስ ማሽኖችን ሊይዙ የሚችሉ ሶሥት ክፍሎች በቋሚነት ተዘጋጅተዋል፡፡ የተለየ ዓይነት የዴያሊስስ ሕክምና የሚሰጥባቸው ክፍሎችም ይኖራሉ፡፡
አቶ ዮሴፍ አብዱልሃማድ የኩላሊት እጥበት ማኅበር ፕሬዚዳንት በዘውዲቱ ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ የተቋቋመው የዴያሊስስ ሕክምና ማዕከልን ከ800 ሺሕ ብር በሚበልጥ ወጪ ያሰራው ማኅበሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድ ሕመምተኛ ማዕከሉ የሚሰጠውን ሕክምና ለማግኘት አንድ ሺሕ ብር ብቻ እንደሚከፍል፣ ወደ ግል ሕክምና ተቋም ቢሄድ ግን እስከ 15 ሺሕ ብር ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡