የስንዴ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከአምራቾቹ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አልተቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ስንዴ፣ የስንዴ ዱቄትና ሌሎች የተቀነባበሩ የብርዕና አገዳ እህሎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በገቢ ንግድ እየቀረቡ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች መካከል ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ቢሆንም ከአንድ ሦስተኛ የበለጠው የአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሸፈነውም በገቢ ንግድ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች የገጠማቸውን የስንዴ ጥሬ ዕቃ እጥረት አስመልክቶ፣ የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄዱት የጋራ መድረክ ላይ የተገኙት የምግብ መጠጥና ፋርማስዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የብርዕና የአገዳ እህሎች ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ አቶ ዘርጋው ፈለቀ እንደሚሉት፣ 3.6 ሚሊዮን ቶን ከሆነው አጠቃላዩ ዓመታዊ አማካይ የስንዴ ምርት ውስጥ 73 በመቶ ያህሉ ወይም ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆነው እዛው በተመረተበት አካባቢ ለፍጆታና ለዘር፣ 27 በመቶ ወይም 0.98 ሚሊዮን ቶን ደግሞ ለገበያ ይቀርባል፡፡
ለገበያ ከሚቀርበውም መካከል ለዱቄት አምራቾች የሚደርሰው አራት በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተመራማሪው ጠቁመው፣ ከእህል ንግድ የሚሰራጨውም የአቅማቸውን ከ20 እስከ 30 በመቶ ብቻ እንደሆነና በዚህም ሁሉም አምራቾች ተጠቃሚ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስንዴ የተሸፈነው መሬት 1.606 ሚሊዮን ሔክታር ሲሆን፣ ይህም በ2005 በጀት ዓመት ከተሸፈነው 1.627 ሚሊዮን ሔክታር ጋር ሲነጻጸር በ1.35 በመቶ ያንሳል፡፡ ይሁንና በ2006 በጀት ዓመት የስንዴ ምርታማነት በሔክታር 24.5 ኩንታል ሲሆን፣ ይህም በ2005 በጀት ዓመት በሔክታር ከተገኘው 21.4 ኩንታል ጋር ሲነጻጸር በ15.88 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡
በዚህም ምክንያት በ2006 ዓ.ም. የተመረተ ጠቅላላ የስንዴ ምርት መጠን 3.92 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ ይህም ከ2005 ዓ.ም. ከተገኘው 3.43 ሚሊዮን ቶን ጋር ሲነጻጸር በ14.28 በመቶ ይበልጣል፡፡ ስለሆነም የሕዝብ ብዛት ጫና ከሚፈጥረው መሬት ጥበት አንፃር የሚታረስ መሬት በማስፋት ምርት የመጨመር ዘዴ አሁን ባለንበት ሁኔታና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሆን አይደለም ብለዋል፡፡
የተሻሻሉ ግብዓቶችንና ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎችን በመከተል ምርታማነትን የማሳደግ ዘዴ የተሻለ ተመራጭ እንደሚሆን፣ ይህንን አጠናክሮ በመቀጠልና በምርምርና ሥርጸት በመደገፍ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ከሰነድ አቅራቢው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተመራማሪው የኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማኅበር በ1999 ዓ.ም. ያካሄደውን ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት፣ የማኅበሩ አባል ያልሆኑትን ጨምሮ የሚያስፈልጋቸው የስንዴ ምርት መጠን 2.2 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስ ተገምቶ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ያሉት የዱቄት አምራቾች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ እስከ 400 ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
አቶ በዳዳ ቤኛ የቁልምሳ ግብርና ምርምር የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ኤክስቴንሽን ተመራማሪ እንደሚሉት፣ ለዳቦ የሚውል የስንዴ ምርት በዋናነት ከዋጋ ጋር ተያይዞ
በዚህም የተነሳ ባለፈው ክረምት ባሌና አርሲ አካባቢዎች በቡቃያ ደረጃ የነበረውና ለዳቦ የሚውለው የስንዴ ሰብል ማበብ አካባቢ ሲደርስ በዋግ ተመትቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ምርት ያልተገኘበት ሁኔታ ነበር፡፡
ዋግን ይቋቋማሉ የተባሉ አሥር ዓይነት የስንዴ ዝርያዎች በምርምር እንደተገኙ፣ በእነዚህም ዝርያዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሌላ አዲስ ዓይነት ዋግ እንደተከሰተም ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ከአዲስ ዓይነት ዝርያዎች መካከል ‹‹ዲገሎ›› የተባለው ዝርያ ባሌ ላይ ለስምንት ዓመታት ያህል ዋግን ሲቋቋም ቆይቶ በ2004 ዓ.ም. በተከሰተው አዲስ ዋግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ አምና ደግሞ አርሲ ላይ ይኸው ዓይነት ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡
የዱሪም ስንዴ ምርታማነት ግን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በምርምር አካባቢ በሔክታር በአማካይ እስከ 45 ኩንታል የሚገኝበት ሁኔታ እንዳለ፣ ከዋግ በሽታም ነፃ እንደሆነና በዚህም የተነሳ የዱሪም ስንዴ ዝርያን ለአርሶ አደሩ በስፋት የሚገባበት ሁኔታ እየታሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ደመቀ ሰይፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ግብይት ኬዝ ቲም አስተባባሪ፣ ‹‹በተፈጠረው የስንዴ ጥሬ ዕቃ እጥረት ሳቢያ የዳቦ አምራቾች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘታቸው የከተማውን የዳቦ ችግር ለመቅረፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡
አቶ ንጉሤ ገብረማርያም በኢንስትቲዩት የገበያ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በፍላጐትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚቻለው ግብርና ራሱን ችሎ ትራንስፎርምና ኮሜርሻላይዝድ ሲደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በግብርና ሚኒስቴር ከአምና ጀምሮ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ትላልቅ እርሻ በማስፋፋት ተግባር ላይ የሚሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን የመሳብ ሥራ በሰፊው በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ የግል ባለሀብቶች ከአነስተኛው ገበሬ ቦታ በኮንትራት ወስደው በማምረት ገበሬውንም እኩል የቴክኖሎጂውና የገቢ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡