Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ዝምታን ማን ይስበር?

  ሰላም! ሰላም! ውዷ ማንጠግቦሽ “ሞል አማረኝ” ብትለኝ እሷን ይዤ አሉ የተባሉ የከተማችን ሕንፃዎችን ሳስጎበኛት ሰነበትኩ። በዚያውም ከሠፈር እሮሮና ዕይታ ወጣ ብላ የሰውን ሳይሆን የከተማውን ለውጥ ታያለች ብዬ ነበር። አንከራታኝ ስታበቃ፣ “እኔ ሽርሽር አማረኝ አልወጣኝም፣ ‘ሞል’ መሥራት አማረኝ ነው ያልኩህ፤” አትለኝ መሰላችሁ? “ደፋር!” ብዬ ጓዳዬ እንደለመድኩት ሕዝብ ፊት ስጮህ ለራሴ ደነገጥኩ። አንዳንዱ ‘ሙሰኛ የሚያስደነግጥ ጩኸት አትጩህና እህቶቻችን ላይ ደንፋ’ በሚል አስተያየት አፈር ድሜ ያስግጠኛል። እንዳወጣጥዋ ቤቷ አስገብቼ ወደምሄድበት ሳቀና ይኼን ጉድ ባሻዬ ይስሙት ብዬ ቤታቸው ጎራ አልኩ። ባሻዬ ማንጠግቦሽ ያማራትን ሲሰሙ ከት ብለው ስቀው፣ “አንተም እንደ ፀረ ዴሞክራቶች ምኞት ልትከለክል አማረህ?” አሉኝ። በደካማ ጎናቸው ልግባ ብዬ “ባሻዬ መጽሐፉስ የሚለው ‘አትመኝ’ መስሎኝ?” ስላቸው፣ “እንደተጻፈው ቢሆን ኖሮማ በምድራዊውም በሰማዩም ሕግና ሕገ መንግሥት እንነታረክ ነበር?” ብለው አመለጡኝ። ባሻዬ አጉል ‘ሙድ’ እንደያዙብኝ ገብቶኝ ለልጃቸው ብነግረው የእሱ ባሰ። ምን ይለኛል፣ “ኳስ ተጫዋች ሆነህ ጠረቡኝ እያልክ ካኮረፍክ መጀመሪያም አርፈህ ገበጣ መጫወት ነበረብህ፤” አይለኝ መሰላችሁ?

  ስለዚህ በእሱ አባባል ዕድልና ‘ቻፓ’ የሌለን ሰዎች በምኞት ጠረባ ስናልቅ ዝም ነው ማለት ነው ያለብን? እስኪ ንገሩኝ በፈጠራችሁ? መቼ ወደን ሆነ ሕንፃ ሠርተን የከተማ ውበት ልንጨምር (ሰው መቼም ካልበላና ነገር የማታውቅ ሌሊት ካላሳለፈ አያምርበትም) ቀርቶ የጓሮ አትክልት ማልማት ያቃተን? እኔ ልሙት! ታዲያ ነገሩን ምንም ሳላንዛዛ በአጭሩ ቀጨሁና የሆዴን በሆዴ ይዤ ሳብላላ ሰነበትኩ። የማንጠግቦሽ ልበ ተራራ መሆን ምንጩ ምን ይሆን? እያልኩ በልቶ እንዳልበላ ሆንኩ። “ምግብማ ሞልቷል አምላክ መቼ ነሳኝ፣ የምኞት ጣጣ ነው እኔን ያከሳኝ፤” እያልኩ መሆኑ ነው። በራሴ ዛቢያ መሽከርከር አማረኝ፡፡

  መቼም ስለምኞት አንስቼላችሁ እንዲሁ ማለፍ ይከብደኛል። ያው በእኛ ጊዜ፣ “ማሙሽ ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብሎ ወላጆቻችንን አፍሮ ከነቋቁቻችን ከነፎረፎራችን አቅፎ የማይጠይቀን አልነበረም። የአሁኖቹ እንኳን ‘ስማርት’ ናቸው። ያውስ እንኳን ሰው ስልኩ ‘ስማርት’ በሆነበት ጊዜ? ምን ነካችሁ። አንዱ ለምሳሌ “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ስለው ኮራ ጀነን ብሎ “አሜሪካዊ!” ብሎኛል። “እንዴ! አሜሪካዊ መሆን እኮ መክሊትን ማግኘት ማለት አይደለም፤” ብለው ገር መስሎኝ፣ “የለም አትዮጵያዊነት ነዋ!” ብሎ የወጣልኝ ሞኝ አድርጎኝ አረፈው። የዘንድሮን ነገር እንዲሁ በሆድ ይፍጀው ካላለፍነው አቃጥሎ ሊጨርሰን ነው። ስለቀደመው ምንም ያለማወቅ የልጅነት ጊዜ እንቀጥል። እናም እንደነገርኳችሁ በየሄድንበት ሰው ሆነን ተፈጥረን ሰው አድርገው ላይሠሩን የምኞትኛና የሆዳችን ባሪያ ሆነን ለምንቀረው፣ “ወደፊት ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?” ስንባል የምንመልሳቸው መልሶች ከምናችንም ጋር የማይዛመዱ ነበሩ።

  አንድ ወዳጄ፣ “ይችን አገር ፈጣሪ እንደሚወዳት ያወቅኩት እንደ ምኞታችን ስላላደረገን ነው፤” አለኝ። “እንዴት?” ስለው፣ “እስኪ አስበው ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወገናችን እኮ ክፉና ደግ ሳይለይ እንደቀባጠረው ቢሆን የሽቦ ‘ቦይንግ’ አብራሪና ራሱን በራሱ መርፌ ወጊ ሆኖ ቀርቶ ነበር። ‘ፓይለትና ዶክተር’ ካልን መመለሻ ነበረን እንዴ?” ሲል ፈገግ አሰኝቶኛል። በማከልም፣ “ለነገሩ ምንም ማድረግ አትችልም። ቤትህ ለመጣ እንግዳ ከሁለቱ ውጪ እሆናለሁ ብለህ ወይ ፓይለት ወይ ሐኪም ካላልክ ማታ ‘ማንን ልታሰድብ ነው’ በሚል በቀኝና በግራ የሚወርድብህ የኩርኩም መድፍ አይጣል ነው፤” ቢለኝ የአንድ አብሮ አደጋችን ገጠመኝ ትዝ አለኝ። የድሮ የሚሉት መዓት መጥቶ በትዝታ እንለቅ ግን?

  ጓደኛችን ምን አደረገ መሰላችሁ? የእናቱ ቅርብ ዘመድ ከውጭ ይመጣል። መሬት ላይ የወደቀ ‘ዩፎ’ እንደምናይ እንግዳውን ከበን ባህር የተሻገረ ዘመድ ባለው በጓደኛችን ቀንተናል፡፡ የልጅነት ቁጭታችን ይሆን ‘ኢሚግሬሽኑን’ የሚያጨናንቀው? አይታወቅም እኮ! በኋላ እንግዳው በልቶ ጠጥቶ ከቤት ሲሸኝ ጓደኛችንን ከመሀል ነጥሎ ጠራና “ማስቲካ ከመስጠቴ በፊት ወደፊት ምን መሆን እንደምትፈልግ ንገረኝ፤” አለው። ከእኛ ከእኩዮቹ ጋር ተቧድኖ ሌባና ፖሊስ እንደ መጫወት መስሎት ሲቅለበለብ “ፖሊስ!” አለ። እናት አጠሩ። “ምን? አንተ! እኔ ብቻዬን እየተንገላታሁ የማሳድግህ ተምረህ ‘ፖሊስ’ እንድትሆን ነው?” ሲሉት እንግዳው ፊት ስለቆመ ብቻ በቁጣ የተቀየረለት ኩርኩም ማታ በተኛበት እንዳይመጣ አጉል ብልጥ ሊሆን፣ “እሺ ሌባ!” ብሎ እንግዳውንም እናቱንም በሳቅ ገደላቸው። ሳይገባን አብረን ሳቅን። አይ ልጅነት!

  እንግዲህ የልጅነት ነገር ተረቱ ብዙ ነው። ድሮ ድሮ ‘ልጅነቴ ልጅነቴ ማርና ወተቴ’ን ስንዘምር ብዙዎቻችንን በማርና ወተት ፈንታ ሽሮና ቂጣ ያሰለቸን ነበርን። የምንዘምረውም የሥነ ጥበብ አስተማሪያችን ማርክ እንዳይቀንሱብን በመፍራት ነው። ምን ዋጋ አለው? ለካ እውነትም ልጅነት ማርና ወተት ኑሯል ያልነው ዛሬ በጉልምስና የኑሮን ንረት፣ የክፋትን ረቂቅ ሬትነት ስናይና ስናጣጥም ሆነ። መቼስ ሰው አፈሩ ካላለፈና ካልተፈታ የዚህ ዓለም ፀጋና መርገም አይገባውም አይደል? “ደግሞ እኮ ክፋቱ ምንም ላንፈይድ ውለን አድረን ነገር የሚገባን መሆናች ነው፤” አለኝ የበሻዬ ልጅ። ይኼን የማርና የወተት ‘ቲዎሪ’ ሳጫውተው ‘ነገር’ ያላት ነገር የቀናነት ቀኖናዬ ውስጥ በመሰንቀሯ ደስ አላለኝም። ስለዚህ “የምን ነገር ነው የምታወራው?” ብዬ ዓይን ዓይኑን ሳየው፣ “በፖለቲከኞች ሴራና ተንኮል ስለሚባክነው የትውልዶች ዕድሜ፣ ከሰፊው ሕዝብ ጥቅም በፊት ስለራሳቸው ስምና ታሪክ  በሚባዝኑ ጥቂት ጀብደኞች ምክንያት እያደር ስለከረሩ የኑሮ አጀንዳዎች ነው የማወራው። በቀላሉ የሚስተካከሉ የኑሮ ስንክሳሮች ጠብቀው ጠብቀው እንኳን ማርና ወተት ውኃና እንጀራም ትግል ሆነ አደል እንዴ?” አለኝ። ወዴት ወዴት እንደተንሸራተተ ገብቶኛል። ጥቂት ሳዳምጠው መጠለያ፣ ኔትወርክና መብራት የሚል ጨመረበት። “ይኼን ግለትህንና ቁጭትህን እኔ ላይ ብቻ ከምታባክነው ወይ ምርጫ መወዳደር ነው፣ ወይ ጋዜጣ ላይ መጻፍ ነው፣ አልያም ደግሞ ፌስቡክ ላይ መለጠፍ ነው፤” ብለው ትኩር ብሎ አይቶኝ ሲያበቃ፣ “ለማን ብዬ?” ብሎ ጥሎኝ ሄደ። እኔም ጠቀም ያለ ኮሚሽኝ የማገኝበት ሥራ ስለነበር ወደዚያው ከነፍኩ። ይኼ በሰው እጅ ሲያዩት የሚያስቀና ሲይዙት የሚያደናግር ከበሮ እኮ እንዴት እንደሚያስተዛዝበን? የምሬን ነው!

  እስኪ ወደ አሻሻጥኩት ከባድ መኪና ገጠመኝ ልውሰዳችሁ ደግሞ። በድለላ ሥራ ጥርስ ስትነቅሉ ትልቁ ወሮታችሁ በከባድ ሚዝን ከሚጫወቱ የኑሮ ተፋላሚዎች ጋር መዋል ነው። ቀላል ሚዛኑማ ጥርስ ሳታበቅሉም ነው የምትውሉበት። ታዲያ ያን ‘ሪሞርኬ’ የሚገዛ ደንበኛዬ መኪናውን ቶሎ አስፈትሾ ቀልቡን ሰብስቦ ሊዋዋልልኝ አልቻለም። በቅርብ ሠርቶ ስላጠናቀቀው ቤት በየአቅጣጫው እየተደወለለት ያወራል። በመርከብ አስጭኖ ከአውሮፓና ከቻይና ስለሚያስመጣቸው የቤት ዕቃዎች ይቀዳል። በዕቃ ግዢ ለሚያግዙትና ከዚያው ሆነው ለሚያማክሩት ሰዎች በስልክ ሲመልስ አንድም ርካሽ ዕቃ እንደማይፈልግ “የሰው መሳቂያ አታድርጉኝ፤” በሚል መኩራራት ይገበዛል። “ያዝኩ ሲሉ መያዝ አለሁ ሲሉ መቅረት በሰው እንኳ አይቶ አልተማረም እንዴ ይኼ ሰው?” ብሎ የሪሞርኬው ባለቤት ቢታዘበው ጓደኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “ምን ይደረግ ገንዘብ ዕውቀትን የትና የት መርቶት እያየህ ለምን በእሱ ትፈርዳለህ?” ይለዋል። መልሶ ደግሞ ከፊል ወደኔ ዘወር ብሎ፣ “እንደ እኛ ላለው ደካማ ደግሞ መኖሪያ ቤት ፀሐዩ መንግሥታችን በዕጣ ሊያንበሸብሸን ነው። ከሁሉ የገረመኝ ግን የዘንድሮ የገዢው ፓርቲ የቅስቀሳ ስልት ከጉንጭ አልፋ ዲስኩር በቤት ዕደላና በሌሎች የልማት ሥራዎች  ሥልት መታጠፉ ነው፤” አለኝ። ይኼኔ ጓደኛው ተቀብሎ፣ “ታዲያ በአንዲት መርፌ ላይ ስንት ሺሕ መላዕክት መቆም ይችላሉ?’ ከሚል ውኃ የማይቋጥር ክርክር ለእኛስ ቢሆን ይኼ አይሻለንም?” አለውና ፈገግ አለ። እየበሉ ማልቀስን እንዴት እንደተካንነበት ታያላችሁ?

  በሉ እስኪ እንሰነባበት። ዝጌን ዘግቼ ሳበቃ ውኃ ጥም ሊገለኝ ደረሰ። የባሻዬን ልጅ ደወልኩለትና የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ስንገናኝ ግሮሰሪያችን ከወትሮዋ በተለየ ሁናቴ የዋጋ ጭማሪ አድርጋ ታዳሚዎቿን ታስተናግዳለች። የግሮሰሪያችን ባለቤት መቼም ይኼ ሕዝብ በሃይማኖቱና በሚስቱ ነው የሚገኘው ብሎ (እምዬ ምንሊክ ሊያተርፉበት ሳይሆን ሊያተርፉት በማርያምና በሚስቱ እንደመጡበት አልገባውም) ከመጽሐፈ መክበብ ያገኘው መሆኑን በትልቁ ጠቅሶ፣ “ራሱን የማይወድ ሌላውን አይወድም፤” የሚል ጥቅስ ለጥፏል። ለዚህም የተጋነነ ጭማሪ ስላደረገ በዝምታ የሚታለፍ መስሎታል። ገና አንድ መለኪያ ሳይቀምስ የዋጋ ጭማሪው ያሰከረው የዘወትር ደንበኛው ጥጉን ይዞ “የት ሄደን እንብላ?’ ስንል ዝም የተባልነው አንሶ ‘የት ሄደን እንጠጣ’ በሚልም ከመንግሥት ጋር ልታቀያይመን ነው? ተው የቄሳርን ለቄሳር የእኛን ለእኛ!” ይለዋል። “አወይ ዘመን! አወይ መጨካከን። እላያችን ላይ የትርፍ ‘ዌት’ እያነሱብን ገላጋይ አጥተን እኮ ‘ዌት’ የለሾችን ሆነን ጎበዝ! ሲያዩን አንከብድ ሲቆጥሩን አንሞላ፤” ይላል ሌላው።

  ገና ከአሁኑ በዚህ ሁናቴ እንደለመደው ተመላልሶ እየጠጣ ፀንቶ ኑሮውን የመርሳቱ ዓላማው አደጋ ላይ እንደወደቀ የተረዳው ደግሞ፣ “እሱ ምን ያድርግ? እስከዛሬ የተጎዳው አይበቃም? ስንት ጓደኞቹ ሕንፃ እየሠሩ በክለብ ተቧድነው ክለብ ሲከፍቱ፣ እሱ እስከ ዕለተ ሞቱ ግሮሰሪ ላይ መቅረት አለበት?” ይላል። ከዚህ ሁሉ በላይ በቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ ይገኛሉ ተብለን፣ ዝም ይላሉ ተብለን ለመጃጃል መታሰባችን ያንገበገበው፣ “ራሱን ቢወድ ነዋ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሲጓዝ አንገቱን የደፋው? ሕገ መንግሥት አደረግከው የፈጣሪን ቃል እንዳሻህ ለራስህ መጠቀሚያ እያደረግክ የምትለጥፈው? አንሳ ወዲያ!” ሲል አምባጓሮ ያስነሳል። እኔና የባሻዬ ልጅ ስንተያይ “ወይ ዘንድሮ!” አልኩት። እሱም መለሰና “ከራስ በላይ ለራስ! ሆነ እኮ ጊዜው!” አለኝ፡፡ የእሱ አባባል በቅጡ ባይገባኝም፣ ዘመኑ የፀና ራስ ወዳድነትና ሌላውን ጠልፎ የመጣል አባዜ የበዛበት መሆኑ ሲታወሰኝ ቅሬታ ተሰማኝ፡፡ ቅር ሲለን ቅሬታችንን ማን ነው የሚሰማልን? ብለን ብንጠይቅ ቅሬታ የሚያባብስ እንጂ የሚፈታ የለም የሚል መልስ ስለሚገኝ ዝምታ በዝቷል፡፡ ዝምታን ማን ይስበር? መልካም ሰንበት!  

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት