Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹በኢትዮጵያ የቦብ ማርሌ ሐውልት መኖሩ ለጥቁሮች አርማ ሆኖ ታሪኩን ያንፀባርቃል›› ድምፃዊ...

‹‹በኢትዮጵያ የቦብ ማርሌ ሐውልት መኖሩ ለጥቁሮች አርማ ሆኖ ታሪኩን ያንፀባርቃል›› ድምፃዊ ዘለቀ ገሠሠ

ቀን:

‹‹ዶንት ሌት ሚ ዳውን›› በብዙዎች የሚታወቅ ዘፈኑ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወረ ከመዝፈን አንስቶ በስደት ጂቡቲ ከዛም አሜሪካ ሲሄድ ዳሎል የተባለ ባንዱን ይዞ ሄዷል፡፡ ዘለቀ ገሠሠ ከዓመታት በፊት ኑሮውን ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲያደርግ ከሙዚቃው በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ይዞ መጥቷል፡፡ ከቦብ ማርሌ ቤተሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ዘለቀ፣ ከቦብ ልጅ ዚጊ ማርሌ ጋር በሜሎዲ ሜከርስ ባንድ ግራሚ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት የቦብ 60ኛ ዓመት ልደት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከበር የተጠነሰሰው የቦብ ሐውልት ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ይመረቃል፤ የዘለቀ አልበምም በዛው ሰሞን ይወጣል፡፡ ስለ ሐውልቱ፣ የዕርዳታ ሥራውና የሙዚቃ ሕይወቱ ከምሕረተሥላሴ መኰንን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቦብ ማርሌ መታሰቢያ ሐውልት የማቆም እንቅስቃሴ እንዴት ተጠነሰሰ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- የተጠነሰሰው የዛሬ አሥር ዓመት ለቦብ 60ኛ ዓመት በተዘጋጀው  በዓል ነበር፡፡ ኮንሰርቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ማስተዋወቂያ ነበር፡፡ እኔና ወንድሜ አዲስ ገሠሠ ለሰባት ዓመታት ለፍተን ነው ኮንሰርቱ የመጣው፡፡ መንግሥትም ካሰበው በላይ ነው የሆነው፡፡ 400 ጋዜጠኞችና ከዓለም አገሮች ያልመጣ ራስታ አልነበረም፡፡ በሙዚቃ ፌስቲቫል ኢትዮጵያ በዓለም ስሟ ሲነሳ የመጀመርያው ነበር፡፡ የቦብ ቤተሰቦች እንደመጡ በቦብ ስም ቋሚ ነገር ይገባዋል ተባለ፡፡ በያኔው ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ ሪታ ማርሌ ባለችበት ኢምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት ያለው አደባባይ ለሐውልቱ ተከላ ተወሰነ፡፡ ሐውልቱ በታዋቂው ቀራፂ ተስፋ ብዙነህ ቢሠራም አልቆመም ነበር፡፡  ሐውልቱ አራት ሜትር ቁመት አለው፡፡ ቦብ ‹‹አፍሪካ ዩናይት›› ብሎ የዘፈነው ለአፍሪካ አንድነት ነው፡፡  ሁሉንም የአፍሪካ ባንዲራዎች በአንድ ፖስተር አድርጎ እየዞረ ያስተዋወቀ የመጀመርያው ሰው ስለሆነ ይገባዋል፡፡  ዕቅዳችን ትልቅ በዓል አዘጋጅተን የዓለምን ሚዲያ ጠርተን ለማቆምና ለማስመረቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቦብ ሐውልት ቢኖር በምዕራቡ ዓለም ላሉ ጥቁሮች ዓርማ ሆኖ ታሪኩን ያንፀባርቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ምን ያህልስ ገንዘብ ወጣበት?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ሐውልቱ መልክ ይዞ ሲሠራ አምስት ዓመት ወስዷል፡፡ ወጪው በጣም ብዙ ነው፡፡ አደባባዩን ለመጠገን ብቻ ከ200,000 ብር በላይ አውጥተናል፡፡ የሐውልቱ ማቆሚያ፣ መብራትና የቀሩት ሲያልቁ ወደፊት አጠቃላይ ወጪውን እናሳውቃለን፡፡ ገንዘቡ ለአገር ስለሆነ አልተሰማንም፡፡ ምርቃቱ የዳግማይ ተንሣኤ (ሚያዝያ 11) ቀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርቃቱን የቦብ ልጆች እንደሚታደሙ ሰምተናል፤ እነማን ይገኛሉ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ባለቤቱ ሪታ ማርሌ ትመጣለች፡፡ ልጆቹ አልበም ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ዚጊ  ግራሚ አሸንፎ በኩባንያው አዲስ አልበም ስለሚያወጣ አይችልም፡፡ ስቲቨንና ዴሚያን  ቱር ላይ ናቸው፡፡ ጁልያንን አነጋግረነዋል ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ የበዓሉ ዋና ዓላማ  የኢትዮጵያ አርቲስቶች ለቦብ መታሰቢያ እንዲያደርጉ ነው፡፡ በፊት ልጆቹ በመጠኑ ታስቧል፤ አሁን ደግሞ እኛ እናስበዋለን፡፡ ወደ 12 ኢትዮጵያውያን ለዝግጅቱ የተመረጡ ሲሆን በቅርቡ እናሳውቃለን፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዲፕሎማቶች ተጋብዘዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኮንሰርቱ በተጨማሪ የተዘጋጀ መርሐ ግብር አለ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ዝግጅቱ ቅዳሜ ነው፤ ዓርብ ማታ የራስታ ድራሚንግ (ናይቢንግ) ይኖራል፡፡ ከሻሸመኔ ሸምገል ያሉትን አምጥተናቸው አደባባዩ ሥር በሻማ የታጀበ ዝግጅት ይኖራል፡፡ ስፖንሰር ከተገኘ ርችትም ይኖራል፡፡ ዝግጅቱ መንፈሳዊ ይዘት ያለው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ታሪክ እንደሚያስረዳውና ባለውም ነባራዊ ሁኔታ ራስ ተፈሪያኖች ከሻሸመኔ ጋር የተለየ ትስስር አላቸው፡፡ ለሐውልቱ መቀመጫ የመጀመርያ ምርጫችሁ አዲስ አበባ  ነበረ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- አዎ፤ ቦብ ምኞቱ ሻሸመኔ መቀበር ነበር፡፡ ስላልተሳካ በተወለደበት ጃማይካ፣ ናይን ማይል ተቀብሯል፡፡ ሪታ ሬሳው እዚህ እንዲቀበር ብትሞክርም የጃማይካ መንግሥት በፓርላማ ተቃውሟል፡፡ በዓመት ከዓለም ዙሪያ ከሚሊዮን በላይ ቱሪስት ስለሚጎበኘው ለጃማይካ ይጠቅማል፡፡ ቦብ ጃማይካ የሄድኩት በስደት እንጂ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ስለሚያምን እኛ በሐውልቱ እንጠቀማለን፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በምዕራብ ያላችሁ የአፍሪካ ልጆች ቦታ አላችሁ ብለው ሻሸመኔን ሰጥተዋል፡፡ በጣሊያን ጦርነት  ሐርለም ኒዮርክና ቺካጎ ለኢትዮጵያ እንዋጋለን ያሉ ብዙ ሺዎች ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያም የአፍሪካም መዲና በመሆኗ በደንብ የሚጎበኘው እዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ኢትዮጵያ የመጣ የግብፅ ቡድን አባላት አደባባዩ ላይ ፎቶ ተነስተው የግብፅ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል፡፡ ይህ ትልቅ የአንድነት መልክት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- የቦብ ሐውልት ጃማይካና ፍሎሪዳ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሠራቱ ምን ያመላክታል? ምንስ ጠቀሜታ ይኖረዋል?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ከዓድዋ ድል ወዲህ ኢትዮጵያ የጥቁሮች ዓርማ ናት፡፡ የጥቁሮች ንቅናቄ በሙሉ የተጀመረው ከአቢሲኒያን ባፕቲስት ቸርች ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1886 ምኒልክ ከአሜሪካ ጋር ንግድ ለመጀመር አራት ራሶች ይልካሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ነጭና ጥቁር ተለያይቶ ስለሚቀመጥ ራሶቹን ከኋላ ሲያስቀምጧቸው ቤተ ክርስቲያን እንሠራለን አሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ ወደ 50 ሚሊዮን ጥቁር አለ፡፡ በብዛት ደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ናይጄሪያ እንጂ ኢትዮጵያ አይመጡም፡፡ እነሱ በቱሪዝም ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ ሐውልቱ ታሪካዊ ግንኙነቱን ስለሚያመላክት ቱሪስቱን እንደሚስብ እናምናለን፡፡ አዲሱ ትውልድ በቀደመው ጊዜ የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት በማስታወስ ታሪክ ሊያጠና ይችላል፡፡ ሐውልቱ በአዲስ አበባ ከሚጎበኙ ቦታዎች (በቱር ጋይድ) ውስጥ እንደሚገባ ተነግሮናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶች በመክፈት ስለምትሠራቸው የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ንገረን?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ከ19 ዓመት በፊት ለዓድዋ 100ኛ ዓመት በዓል ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ስመጣ ነው የተጀመረው፡፡ ኢትዮጵያን ዞሬ ሳይ ብዙ ሕፃናት ትምህርት ቤት አይሄዱም ነበር፡፡ ከነዚጊ ጋር እሠራ ነበርና አሜሪካ ተመልሼ ስሄድ እኔ እሱና አዲስ ተነጋገርን፡፡ አንድ ሰው ትምህርት ከተሰጠው መንገዱን ይቀይሳል በሚል ትምህርት ላይ አተኮርን፡፡ የትምህርት ቤት እጥረትን ከዘ ሴቭ ችልድረንና ዩኒሴፍ ስናጣራ ትምህርት ቤት ለማግኘት ለሰዓታት በእግር የሚያስጉዙ አካካቢዎች ጠቆሙን፡፡ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ የቦርድ አባል ስለሆኑ ገንዘብ ለማሰባሰብ ብዙ አገር ሄደናል፡፡ ጀርመን፣ እስራኤል፣ ፈረንሣይ፣ ጃማይካ ዞረን ቺካጎ የምትኖር ዕርዳታ ሰጪ ተስማማች፡፡ መጀመርያ በፈረንጆች ሚሊኒየም ደቡብ ውስጥ አሥር ትምህርት ቤት ሠራን፡፡ የየአካባቢው ነዋሪዎች የገበሬ ማኅበር መሬት ይሰጣሉ፡፡ እንጨትና ድንጋይ እነሱ አቅርበው ደመወዝና ቁሳቁስ ለአምስት ዓመት እኛ እንችላለን፤ ከዛ ትምህርት ቤቶቹ ወደ መንግሥት ይዛዋወራሉ፡፡ ከጎንደር ጫሒትና ከአርሲ ነገሌ አዴንሾ ሞዴል ትምህርት ቤት መርጠን ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀት ለዕርዳታ ሰጪዎች እናሳያለን፡፡         አሥሩን ትምህርት ቤት ለዕርዳታ ሰጪዎች አሳይተን በተገኘው ዕርዳታ ሌላ አሥር ትምህርት ቤት በሰላሌና ቡታጅራ፣ አሥር ትምህርት ቤቶች በጎንደር ደንብያና ሰሜን ጎንደር ተሠራ፡፡ ከ30ው 16ቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲሆኑ፣ 14ቱ የውኃ ጉድጓድ 18ቱ የኮምፒውተር ክፍል አላቸው፡፡ የዛሬ አራት ዓመት 1,000 ላፕቶፕ መጥቶ ተከፋፍሏል፡፡ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር የነበረን ኮንትራታችን አልቆ በመንግሥት ሥር ገብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤቶቹን እንቅስቃሴ እየተከታተላችሁ ዕርዳታው ቀጣይነት ይኖረዋል?  ከዚህ በኋላስ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ይሠራሉ ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- አዎ እንከታተላለን፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ግን የዕርዳታው ድርጅት  ቆም ብሏል፡፡ የሐውልቱ ጉዳይም አለ፡፡ እንደ ውኃ ፓይፕ ያሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ፕሮፖዛል ያስግባሉ፡፡ የውኃ ፓይፕ ማስገባት ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ታዳጊ ሴቶች ጠዋትና ማታ ውኃ ለመቅዳት ከትምህርት ከሚዘገዩና አደጋ ውስጥ ከሚወድቁ ከትምህርት ቤቱ ውኃ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ዕርዳታው የሚቀጥል ነው፡፡ ኮምፒውተር ያላቸው ትምህርት ቤቶች በአንድ አንቴና እስከ አሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ያለ ኢንተርኔት እንዲያገኙና ሕይወታቸው እንዲለወጥ የማድረግ ሕልም አለ፡፡ ጥሩ ውጤት ያሳየ ፕሮጀክት በመሆኑ ያኮራናልና ይቀጥላል፡፡ ተጨማሪ ለመገንባት ብዙ ሥራና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ለጊዜው ያሉትን የማሻሻል፣ ላብራቶሪና የስፖርት ሜዳ የማዘጋጀት ሥራ ይቀጥላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅርብ ‹‹ሀገሬ›› የሚል ነጠላ ዜማና ‹‹ዶንት ሌት ሚ ዳውን›› ሪሚክስ ተደርጎ ተለቋል፡፡ አልበምም እየሠራህ ነው መቼ ይጠናቀቃል?

ዘለቀ ገሠሠ፡- አገሬ ስመለስ ኢንቨስትመንት እንጂ ሙዚቃ እሠራለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ የዕድሜም ጉዳይ እየመጣ ነው፡፡ ወጣቶች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ ውጭ ሳለሁ የቀመስኩትን ዕውቀት ለማካፈል ነው፡፡ ‹‹ዶንት ሌት ሚ ዳውን›› ሪሚክስ ለማድረግ ሲያምረኝና ቤቲ አድቨርታይዚንግ ሲጠይቁኝ ከሠራችሁት እኔ መኖር አለብኝ ብያቸው ጥሩ ሆኖ ተሠራ፡፡ ቤቲም ሲያምረኝም አልበም እየሠሩ ስለሆነ እነሱንም ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ‹‹ሀገሬ›› ከአዲሱ አልበሜ ነው፡፡ ኤልያስና ሁንአንተ በአንተ ሙዚቃ ስላደግን አብረን አንድ አልበም እንሥራ ብለው ተጀምሯል፡፡ አልበሙ ከፋሲካ በፊት ይለቀቃል፡፡ እዚህ አገር አዲስ አልበም ከበዓል ዶሮና ዕንቁላል ጋር ይሸጣል፡፡ በበዓል ደስታና ጥሩ መንፈስ ቢኖርም በዓል ተጠብቆ ብቻ ሙዚቃ መውጣት የለበትም፡፡ ኢንዱስትሪው መሻሻል አለበት፡፡ ወደፊት እንቀይረዋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- አልበምህ ምን ዓይነት ሙዚቃዎች ይኖሩታል? እንደ ‹‹ዶንት ሌት ሚ ዳውን›› የድሮ ዘፈኖችህን ያካትታል?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ብዙ ምስጢር ላወጣ ነው፡፡ ሁሉም አዳዲስ ዘፈኖች ናቸው፡፡ እንደ ድሮ  ዘፈኖቼ እያንዳንዱ መልክዕት አለው፡፡ ስለ ሕይወት፣ ፍቅር፣ ነፃነትና የአፍሪካን አንድነት የሚዳስሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስክ በኋላ የሙዚቃ ድባቡን እንዴት አገኘኸው?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ፈጠራው ላይ ጎበዝ አርቲስቶች ቢነሱም ቢዝነሱ ተዳክሟል፡፡ ብዙ አልበም ቢወጣም የሚገዛ የለም፡፡ ሙዚቃ ቤቶች ድሮ ይገዙ ነበር፤ አሁን ግን በኮፒ ራይት ምክንያት አይገዙም፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ሕጉ ወጥቷል፡፡ አንድ አርቲስት ራሱ አሳትሞ ፕሮዲውስ አድርጎ ለማውጣት ይከብዳል፡፡ ካልተስተካከለ አዳዲስ አርቲስቶች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ዘሪቱ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ ነፍሱን ይማረውና ኢዮብ፣ ሸዋንዳኝ ጥሩ አልበሞች እያወጡ ነው፡፡ ሙዚቃው ወደ ዓለም ገበያ ደርሷል፡፡ የደከመውን የቢዝነስ ጎን መስመር የማስያዝ ዕቅድ አለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባት አሁን ያለው የሙዚቃ አሠራር ያስኬዳል ብለህ ታምናለህ? ባህላዊው ሙዚቃ ይዘቱን ሳይለቅ ወይስ በዘመናዊ መልክ መቅረብ አለበት?

ዘለቀ ገሠሠ፡- እኛ አማርኛን በሬጌ ሠርተን ወደ ውጪ ስንወስደው ጥያቄ ነበር፡፡ የሬጌ ባንድ ከኢትዮጵያ ሲባል ግራ ቢጋቡም ‹‹አሽቃሩን›› ስንዘፍን አድንቀዋል፡፡ወደ ውጪ ዓለም ስንወስደው የኛን ባህላዊ ሙዚቃ እንዲወዱት የሚገባቸውን ብንጠቀም ስሜታቸውን ይገዛል፡፡ በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋና ቅኝት ቢሠራ ይርቃቸዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ በደንብ የሚሰማው ቋንቋውን በእንግሊዝኛ ወይም በሚያውቁት ሥልት እያደረጉ ነው፡፡ የዓለምን ገበያ ለማግኘት ደብለቅ አድርጎ መሥራት ይመረጣል፡፡ እትት በረደኝና ሺቨሪን ሚ በአማርኛም በእንግሊዝኛም የምዘፍነው ምቱን እየወደዱት እንዲገባቸውም ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሲሠራ ስለ ኢትዮጵያ ያውቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ልዩ ባለ አምስት ስኬል በመሆኑ ይህ በራሳቸው ዘዬ ሲሆን ይስባቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለህ የተቋቋመው ዳሎል ባንድ ወደ ጂቡቲ ስትሰደድ አሜሪካ ከገባህ በኋላም ዘልቋል፤ ጉዟችሁ ምን ይመስል ነበር?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ዳሎል አፍንጮ በር የዶሮ ቤት ነበር የተመሠረተው፡፡ ዳሎል ከዶሮ ቤት ተነስቶ ግራሚ አሸንፏል፡፡ እኔ ወንድሜ ሙሉጌታ ገሠሠና ሁለት ጓደኞቻችን በኃይለ ሥላሴ ጊዜ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወርን በነፃ እንዘፍን ነበር፡፡ ጊታር ስጀምር 14 ዓመቴ ነበር፡፡ ታላቄ መኰንን ገሠሠ በልዑል መኰንን ትምህርት ቤት (የአሁኑ አዲስ ከተማ) ጊታር ያስተምር ነበር፡፡ እሱ ቤት ውስጥ ከሙሉጌታ ጋር እለማመድ ነበር፡፡ ሙዚቃ ወደ ቤተሰባችን የገባው በእናቴ ነው፡፡ ሙዚቃ በጣም ትወድ ነበር፡፡ አብዮት ሲመጣ ትምህርት ቤት ተዘጋ፡፡ ቀይ ሽብር መጣ፡፡ ዕድገት በኅብረት ሄደን ስንመለስ በእግራችን ወደ ጂቡቲ ተሰደድን፡፡ ቀይ ሽብር በጣም ያስፈራ ነበር፡፡ ጓደኞቻችን እየተገደሉ መንገድ ላይ ሲጣሉ ለመሄድ ወሰንን፡፡ የምዕራባውያን ሙዚቃ ስለምንሠራ ከደርግ ጋር ችግር ነበር፡፡ ቅድመ ምርመራም ነበር፡፡ በወሎ ድርቅ ጊዜ ‹‹ወሎ ስታክ›› ብለን ኮንሰርት ስናዘጋጅ እያንዳንዳችን ቤት መጥተው ገምግመው የጄምስ ብራውን ዘፈን አይዘፈንም ብለው ከለከሉን፡፡ ደርግን ለማበሳጨት አህያ ላይ የሰላም ምልክት ሥለው ወደ ኮንሰርቱ የሚሄዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ወደ 10,000 ትኬት ተሽጦ ሲከለክሉን ተስፋ ቆረጥን፡፡ ጂቡቲ በእግር በ15 ቀን ገባን፡፡ ድንበር ላይ የተያዘ ሰው ወዲያው ይረሸናል፡፡ እኛም ተይዘን ሲመልሱን ኃይለኛ ዝናብ ይዘንብና መኪናው ማለፍ አቅቶት ስለተመለስን ተረፍን፡፡ ከፖሊስ ጣቢያ ጠፍተን ዲኬል ውስጥ አንድ ሶማሊያዊ ለሦስት ወር አስቀመጠን፡፡ ‹‹ዳሎል››፣ ‹‹ብራዘርስ›› ባንድ ተብሎ እየሠራ ታዋቂ ሆንን፡፡ ጂቡቲ በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ ስንጫወት ወደውን ነበርና ቪዛችንን ጨረስን፡፡

      ዳሎል የተደራጀው ቺካጎ ነው፡፡ ከጂቡቲ ስደት ያወጣን አዲስ ነበር፡፡ ፈርተው በእግራቸው ከዚህ ያልወጡት በአውሮፕላን መጥተው ተቀላቅለውን ዩኒቨርሲቲ ገብተናል፡፡ እ.ኤ.ኤ. 1979 በጥቁር ታሪክ ወር ኖርዝ ኢስት ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያው ኮንሰርት አሳየንና በመቀጠል ቴፕ ሠራን፡፡ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ስንሠራ ስቲቪ ወንደርን አግኝተነዋል፡፡ ከሬዲዮ ጣቢያዎቹ በአንዱ የምትሠራ ኢትዮጵያዊት ነች ያገናኘችን፡፡ በስቱዲዮ አምስት ዘፈን ቀድቶ ሰጥቶን በዓለም ዙሪያ ተዳርሷል፡፡ ያ ቴፕ ነው ሪታ ጋር ደርሶ ጃማይካ ያስገባን፡፡ ቦብ ጃማይካ በሄድን በዓመቱ ነው ያረፈው፡፡ የቦብ የመጀመርያ ልደት የተዘጋጀው መቃብሩ ጋ ነበር፡፡ ሪታ ለዝግጅቱ ልትጋብዘን ስትደውል ማመን አልቻልኩም ነበር፡፡ በጃማይካ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከዳር እስከ ዳር ይውለበለባል፤ ኢትዮጵያ ያለን ነበር የመሰለን፡፡ በስደት ስለወጣን የአገር ናፍቆትም አለ፡፡ አሁንም ኢትዮጵያውያን ጃማይካ ሲሄዱ ሕዝቡ የሚያሳየው ፍቅር የሚገርም ነው፡፡ የመንፈሳዊ አገራችን ሰዎች ብለው ፊታችንን ሁላ ይዳስሱናል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሬጌ ሙዚቃ ያዘነበልከው በቦብ ምክንያት ነው?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ኮሌጅ የምንማረው ብሉዝና ጃዝ ነበር፡፡ ሬጌ የትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ባይኖርም እኛ እናጠናው ነበር፡፡ የሚዘፍነው ስለ አፍሪካ ነፃነት፣ ፍቅርና ሰብአዊ መብት መሆኑ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ አፍሪካን የሚጠቅስ የሙዚቃ ዓይነት ሬጌ እንደመሆኑና እንደ አፍሪካዊነታችን ማንነታችን ስለሆነም ጭምር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ ሙዚቃዎችህ ያለፍክበትን ውጣ ውረድ የሚያንፀባርቁ ናቸው?

ዘለቀ ገሠሠ፡- አዎ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ላንድ ኦፍ ዘ ጀነሲስ›› ስለ ሉሲ ነው፡፡ የዓለም መሠረት ኢትዮጵያ ከሆነች ጦርነትና ችግር ለምን ተስፋፋ ይላል፡፡ በወቅቱ የብሔር ጦርነት ነበር፡፡ አልበሙ ላይ ‹‹ሸግዬ ኢን ዘ ናይት›› አለ፡፡ በሙዚቃው አንድነታችንን ለመግለጽ አንድ ዘፈን በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ዘፍኛለሁ፡፡  እኛ በኦሮሞ ባህል  ነው ያደግነው፡፡ ‹‹ሴል አሎንግ ዘ ሪቨር ናይል››ን እኔ ነኝ የጻፍኩት፡፡ ወደ ምዕራባውያን ከመሄድ ከእኛው ዕድር፣ ዕቁብና ማኅበራዊ ነገሮች መፍትሔ ይገኛል ይላል፡፡ ደርግ ይኼ ዘፈን እንዳይከፈት ከልክሎ ነበር፡፡ ሬጌን የመረጥነው የወቅቱን ሕይወት ስለሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ጥበብ የኅብረተሰቡ መስተዋት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቺካጎ ውስጥ ዋይልድ ሔር የሚባል ታዋቂ የሬጌ ክለብ ነበራችሁ፤ ክለቡ አሁንም አለ?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ኮሌጅ እያለን ዋይልድ ሔር የጣሊያናዊ ወጣት ነበር፡፡ ዳሎል ሐሙስና እሑድ እንጫወታለን፡፡ እሱ በታክስ ምክንያት ሲታሰር በጨረታ ገዛነው፡፡ ሐሳቡን ኋላ ሼርሆልደር ለሆነው ቢዝነስ ፕሮፌሰሬ ነበር ያማከርኩት፡፡ ጨረታውን ስናሸንፍ የቺካጎ ጋዜጦች የያኔውን ከንቲባ ‹‹ሬጋንስ ሬጌ ኮኔክሽን›› ብለው ጻፉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሬጌ ባንድ እየተባለ ሕዝቡ ሙዚቃችንን ይወደው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008  የአሜሪካ ኢኮኖሚ በመውደቁ ገቢው ስለቀነሰ እኔም ወደ አገሬ የመምጣት ዓላማ ስለነበረኝ ተሸጠ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ያቀድከው ኢንቨስትመንት ምን ነበረ? የተለያዩ የሙዚቃ ዘዬዎችን እንደየፍላጎት የሚያስተናግደው መዝናኛ ከምን ደርሷል?

ዘለቀ ገሠሠ፡- ዕቅዴ ሆቴል መሥራት ነበረ፡፡ ቦታው ጠባብ በመሆኑ ቀይሬአለሁ፡፡ አሁን በኢሊባቡር ማር ምርት ላይ አተኩሬአለሁ፡፡ ሪል ስቴት ቤቶች እየሠራሁ ነው፡፡ በሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ድርጅት የማቋቋም ዕቅድ አለኝ፡፡ የአዳዲስ ወጣቶችን ሥራ ፕሮዲውስ በማድረግ የማሳደግ ሥራ ይሠራል፡፡ ወጣት ሙዚቀኞችን ችሎታ 40 በመቶና ቢዝነስ 60 በመቶ እንዲሆን እየሞከርኩ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ የቺካጎ ሚዲያ ብር ለማግኘት እዚህ ይሻልህል ለምን ትሄዳለህ ብለውኝ ነበር፡፡ ሕይወት ብር ብቻ አይደለም ነው ያልኳቸው፡፡ በሕይወት ባህል አለ፡፡ ባህላችን ልዩነቱ ትልቅ ውበቱ ነው፡፡ የኢንተርቴይመንት ሴንተሩ የበለጠ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፡፡ መዝናኛው ዲዛይኑ ወጥቶ አልቆ ነበር ግን አይሠራም፡፡ አንደኛው ምክንያት ያነጋገርኩት የኢንቨስትመንት ባንክ ስለተጎዳ ከአሜሪካ ውጪ አይሠራም፡፡ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ ባስበውም ጥናት ሳደርግ ከባድ ሆኖ ስላገኘሁት አይሠራም፤ ይቆያል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚጊ ጋር በምትሠሩበት ወቅት ዓለምን ዞራችኋል፤ በርካታ ሽልማቶችም አግኝታችኋል፡፡ ከሥራዎቻችሁ ትልቁ ስኬት የምትለው የቱን ነው?

ዘለቀ ገሠሠ፡- እነ ክዊንስ ጆንስና ማይክል ጃክሰን ቁጭ ብለው ግራሚ ላይ መጫወት ትልቅ ነው፡፡ ዘረኝነትን ለማጥፋት የሚዘጋጅ ‹‹ኤስኦኤስ›› የተባለ ኮንሰርት ላይ ሩብ ሚሊዮን ሕዝብ በተሰበሰበበት ከዚጊ ጋር ‹‹ማንዴላ ነፃ ውጣ›› ብለናል፡፡ ዓለምን በመዞር ሙዚቃ ምንም የማይበግረው ኃይል እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ግለ ሕይወቴን የሚተርክ መጽሐፍ እያዘጋጀሁ ስለሆነ ሁሉም በመጽሐፉ ይካተታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...