የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሞሮኳዊቷ ናዋል ኤል ሞትዋኬልት ከ18 ወራት በኋላ በሚካሄደው የሪዮ ዴጂኔሮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በብስክሌትና በቦክስ ስፖርቶች ተሳትፎ ይኖራት ዘንድ የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ የሚሰጥበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሐሙስ ሞሮኳዊቷ ናዋል ኤል ከኦሊምፒክ ኮሚቴው ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለና ከሌሎችም ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ባለፈው ግንቦት የአይኦሲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቶማስ ባች በኢትዮጵያ ተገኝተው የአገሪቱን ስፖርት ለማገዝ ቃል የገቡትን አጠናክረው እንዲቀጥሉበት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረኮች አመርቂና ተጨባጭ ውጤቶችን ከምታስመዘግብበት አትሌቲክስ በተጨማሪ ድጋፍና የሙያ እገዛ ቢደረግላቸው ውጤት እንደሚመጣባቸው የሚታመንባቸው እንደ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌትና ቦክስ እንዲሁም ለአትሌቶች ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ)፣ ለአሠልጣኞችና ለሌሎችም የየዘርፉ ባለሙያዎች ዘመናዊና ሳይንሳዊ ሥልጠና ለመስጠት የአይኦሲ ፕሬዚዳንት ቃል ከገቡት ይጠቀሳል፡፡
የተገባውን ቃል እንደሚያውቁ የተናገሩት የአይኦሲ ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ ይኼው ተግባራዊ እንዲሆንና ከዚህ እንደተመለሱም ከፕሬዚዳንቱ ጋር በመነጋገር ድጋፍና ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን እንደገለጹ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡