Friday, January 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከሻምፒዮናው ሊወሰድ የሚገባው ተሞክሮ

ከሻምፒዮናው ሊወሰድ የሚገባው ተሞክሮ

ቀን:

ሽር ጉዱ ተጠናቆ ባለፈው ሐሙስ በአዲስ አበባ ስታዲየም በይፋ የተከፈተው 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድምቀት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ እነሆ በመክፈቻው ቀንም በ3,000 ሜትር ሴቶች ወርቅና ብር፣ እንዲሁም በ3,000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል፡፡

ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያኑ ከቅርብ ተቀናቃኞቻቸው ኬንያውያኑ ጋር በመክፈቻው ዕለት በ3,000 ሜትር በሁለቱ ጾታ ያደረጓቸው ፉክክሮች በተለይም ሁለቱ በዓለም ላይ በሚታወቁባቸው በ5,000 እና በ10,000 ሜትሮች የውድድሩ ድምቀት እንደሚሆንም ተገምቶ ነበር፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሲካሄድ የሰነበተው ሻምፒዮና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረው ፋይዳ ሲታይ ደግሞ በርካታ እንደሆነ የስፖርቱ ቤተሰቦች ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህ ፋይዳዎች መካከል ወጣትና ዕድል ያላገኙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን በማስተዋወቅና በተተኪነት በመያዝ ረገድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት መሆኑም ታምኖበታል፡፡

ሌላው በአጋጣሚው ዕድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየምም በቀጣይ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በአመቺነት ሊዘልቅ ይችላል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ለአህጉራዊው ሻምፒዮና ዝግጅት ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉም ተገልጿል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በረዥም ርቀት ከፍተኛ ቦታ ላይ ከሚገኙት ጥቂት አገሮች ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ በጓዳዋ ምን ዓይነት ነገር እየተሠራ መሆኑን ያሳየችበት አጋጣሚ እንደነበርም ምስክርነታቸውን የሰጡ አገሮች አሉ፡፡

ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የታዩ እመርታዎችን በማሳደግና ጉድለቶችን በማስተካከል ረገድ በዚህኛው አህጉር አቀፍ ውድድር የተሻለ ነገር መታየቱም ተነግሯል፡፡ በዚህ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፉ አገሮች በዋናነት አንስተው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፡፡ ባለሙያዎችን እንዲካተቱ ባለማድረጉ ምክንያት በተለያዩ ችግሮች መተብተቡ የሚነገረው አትሌቲክሱ የሚወራውን ያህል አለመሆኑን ለማስገንዘብና ሕዝቡ በተተኪ አትሌቶች ዙሪያ ያለውን ሥጋት እንዲያራግፍ ከተፈለገ እንደዚህ ዓይነቶቹ ታላላቅ መድረኮች ምርጥ አጋጣሚዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡ የሚመዘገበው አጠቃላይ ውጤትም ከወዲሁ ለመገምገሚያነት እንደሚጠቅም ጭምር የተናገሩ አሉ፡፡ ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በጋዜጠኝነት እንዲሁም በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ እየሠሩ የሚገኙት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ይጠቀሳሉ፡፡ መድረኩ ለኢትዮጵያውያን ተተኪና ወጣት አትሌቶች ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና መጀመሩ በይፋ ከተበሰረበት ዕለት ቀደም ብሎ በነበሩት ሁለት ተከታታይ ቀናት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (ሲኤኤ) ዓመታዊ ጉባኤ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ አከናውኗል፡፡ የዘንድሮውን ከቀድሞዎቹ ጉባኤዎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2019 ድረስ ሲኤኤን የሚያስተዳድሩ አመራሮች ምርጫ መከናወኑ ነበር፡፡ በምርጫው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሤ በስተቀር የቀድሞዎቹ እንዳሉ በምርጫ እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ካሜሮናዊው ካልካባ ማልቡም ለሦስተኛ ጊዜ ሲኤኤን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ አቶ አለባቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበሩት ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠና  ምትክ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የሲኤኤ አባል በመሆን ተካተዋል፡፡ ወ/ሮ ብስራት ደግሞ በሐምሌ ወር መጀመርያ በቻይና ቤጂንግ በሚደረገው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ላይ አፍሪካን ወክለው እንደሚቀርቡ የሲኤኤና የካፍ አማካሪ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከሻምፒዮናው ቀደም ብሎ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ለሚከናወነው የሲኤኤ ምርጫ ከ50 በላይ አገሮች እንደተገኙ፣ ከነዚህ ውስጥ በሐምሌ ወር መጀመርያ ላይ በሚኖረው ምርጫ ሴኔጋላዊውን የአይኤኤኤፍ ፕሬዚዳንት ላምን ዲያክን ለመተካት በዕጩነት የቀረቡት እንግሊዛዊው ሰባሰቲያን ኮ እና ዩክሬናዊው ሰርጌ ቡካ ቡበካ እንዲሁም ሞሮኳዊቷ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ናዋል ኤል ሞትዋ ኬል እና ሌሎችም በአዲስ አበባ መገኘታቸው ለአገሪቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል፡፡ የነሱ መገኘትም ኢትዮጵያ በቀጣይ እንደነዚህ ዓይነት መድረኮችን ለማስተናገድ ዕድሉ እንዲኖራቸው ያደርጋልም ብለዋል፡፡

 በቀጣዩ የአይኤኤኤ ፕሬዚዳንት ለመሆንና በዋናነትም የአፍሪካን ድምፅ ለማግኘት በሲኤኤ ምርጫ ላይ የተገኙት እንግሊዛዊው ሰባስቲያን ኮ በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የለንደን ኦሊምፒክ ዝግጅትን በበላይነት በመምራት ይታወቃሉ፡፡ ሰባስቲያን እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ከዚያም በፊት በ1,500 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት እንደነበሩም ግለ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ዩክሬናዊው ሰርጌ ቡብካ በበኩላቸው የአገሪቱ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ  እንደሰባሰቲያን ሁሉ ቀደም ባሉት ዓመታት በምርኩዝ ዝላይ የዓለም ክብረ ወሰንን ክብርንም ያገኙ ናቸው፡፡ ሞሮኳዊቷ ናዋል ኤ ሞትዋኬልም እ.ኤ.አ. በ1984 ሎሳንጀለስ ኦሊምፒክ በ400 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

ለዚህ ታላቅ የአመራርነት ክብር የበቁት እነዚህ የቀድሞ አትሌቶች እንደነሱ ሁሉ ሌሎችም በተለያዩ አገሮች የስፖርት ተቋማትን የሚመሩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎች የኋላ ሥረ መሠረታቸው ሲታይ በስፖርት ዓለም ያለፉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አቶ ፍቅሩ ይኼ ዓይነቱ ተሞክሮ በኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽኖች መለመድ እንደሚገባውም ነው ያስረዱት፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...