በፌስቡክ ላይ የማነባቸውና የማያቸው የወረዱ ስድድቦችና ብልግናዎች ቃር ቃር እያሉኝ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን አንድ ነገር ተንኳሽ፣ ‹‹እንኳን ለአደዋ ድል በዓል አደረሳችሁ! ይህ የመልካም ምኞት መግለጫዬ እነ…ን አይመለከትም፤›› ብሎ ጽሑፉን ያሠፍራል፡፡ ወዲያው በግለሰቡ አጻጻፍ የተናደደ እዚህ ላይ ሊሠፍር የማይችል የብልግና መዓት ያወርድበታል፡፡ ይኼኔ በውስጣቸው ነገር የቋጠሩ የሁለት ጽንፈኛ ቡድኖች ጀሌዎች ከግለሰብ ማንነት እስከ ብሔር ብሔረሰብ ድረስ ዘልቀው ተባሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ገደል ገብቶ ምድረ ባለጌ እርስ በርሱ ሲበላላ መሀል ገብተው ለመገላገል የሞከሩ ሳይቀሩ ተሰደቡ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የፌስቡክ ገጼን ከፍቼ አይቼው አላውቅም፡፡
ይህን መረን የወጣ ብልግና በተመለከተ ከዚህ ቀደም ብዙዎች ሲመረሩበት ብሰማም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ጽንፍ የረገጡ ጥቂት ግለሰቦች ጉዳይ ግን ብሔራዊ መፍትሔ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ጨው ከተበተኑበት አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅም ሆነ ደቡብ አፍሪካ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መስማማት ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ አገር ቤት ያሉ የእነሱ ቢጤዎችም ትናንሽ ችግሮችን በማጋጋል ወደር የላቸውም፡፡ እኔን የሚገርመኝ ግን አነሱን በጋራ የሚያስማማቸው ጉዳይ ሲኖር ጊዜያዊ ፍቅራቸው ጣሪያ ይነካና ይካካባሉ፡፡ ትንሽ ልዩነት ሲፈጠር ደግሞ የአባት፣ የእናትና የትውልድ ሥፍራ ስምና ማንነት እየተብጠለጠለ ይሰደባል፡፡ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ብልግናዎች በስፋት ይቀርባሉ፡፡
አንድ ጊዜ አንዲት የእኔ ቢጤ ተራ ዜጋ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ ለእናት አገራችንና ለሕዝባችን ክብር ስትሉ ይህንን የብልግና ስድብ አቁሙ…›› በማለት በፌስቡክ ላይ ተማፅኖ ታቀርባለች፡፡ አንዲት ገራገር ሴት፣ ‹‹እውነትሽን ነው እህቴ አገራችንን ማሳፈር የለብንም…›› በማለት ሐሳቧን ታዳብራለች፡፡ በዚህ መሀል አንዱ እንደ ፊጋ በሬ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹የትኛው ሕዝብ? የትኛዋ አገር? የነፍጠኞቹ፣ የጠባቦቹ፣ የትምክህተኞቹ፣ ወይስ የምንዱባኖቹ…›› በማለት ነገር ሲያጋግል ያደፈጠው ኃይል ከየምሽጉ ወጥቶ የተለመደው የብልግና ስድብ ተጧጧፈ፡፡ የዚያን ቀን ከአፄ ቴዎድሮስ እስካሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ ስማቸውና የትውልድ ቦታቸው እየተጠራ ተዘለዘሉ፡፡ ጭፍን ተቃዋሚውና ጭፍን ደጋፊው ፊት ለፊት ቢገናኙ ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር የሚለውን ሳስብ ያስደነግጠኛል፡፡
የሃይማኖት ጉዳይንም በተመለከተ ምዕመናን ነን በሚሉ ግለሰቦች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ቀረሽ ስድድብ አስፈሪ ነው፡፡ አንዲት የለየላት ፀረ ኦርቶዶክስ የፌስቡክ አርበኛ የሰውን ልጅ የእምነት ነፃነት በመጋፋት የምታካሂደው ተግባር በራሱ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ለእሷ ምላሽ እንሰጣለን የሚሉ ደግሞ አላስፈላጊ ስድቦችንና ሌሎች ወገኖችን የሚያሳዝኑ ቃላት ይጠቀማሉ፡፡ ‹‹መናፍቅ››፣ ‹‹አሕዛብ››፣ ‹‹ፀረ ማርያም››፣ ‹‹መጤ››፣ ወዘተ ከመባባል አልፈው በብልግና ቃላት ይሞላለጫሉ፡፡ በፈጣሪ ፊት ለመቆም የሚያሳፍሩ ተግባራትን የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ከእምነታቸው አንፃር ለቆሙለት የሃይማኖት ተቋም እንዴት ጠበቃ መሆን እንደሚችሉ ያስገርማል፡፡ ፈተናው በዝቷል፡፡
ይኼ ፌስቡክ ለደህና ነገር መጠቀሚያ መሆን ሲገባው፣ በርካታ አስተማሪ ሊሆኑ የሚችሉ የሚነበቡ ነገሮች እያሉ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ጠቃሚ መሆኑ እየተረሳ ነው፡፡ ማንም ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ ሐሳብ ይዞ ሲመጣ የትችቱ መነሻም ሆነ መድረሻ የቀረበው ሐሳብ መሆን ሲገባው፣ ግለሰቡ ለምን እንዲህ ዓይነት አቋም ይኖርሃል ተብሎ ይሰደባል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠበቃ ነን የሚሉ ወገኖች ሳይቀሩ፣ ግለሰቡን በሚፈጽመው ድርጊት ምክንያት መተቸት ሲገባቸው ለምን ይህንን ሐሳብ ታራምዳለህ? ለምን ይህንን ፓርቲ ትደግፋለህ? ለምን ከእኛ በተቃራኒ ትገኛለህ? ወዘተ እያሉ የራሱንና የዘር ማንዘሩን ድራሽ ያጠፋሉ፡፡ ‹‹ሆዳም፣ ባንዳ፣ የጠላት ተላላኪ፣ ቅጥረኛ፣ ተንበርካኪ፣…›› እያሉ ሰድበው ለሌላ ሰዳቢ ይሰጡታል፡፡
የዋሆቹ ሴቶቻችን ፌስቡክ ላይ ፎቶዋቸውን ሲለጥፉ አድናቂዎቻቸው ‹‹አሪፍ›› እያሉ ሲያሞግሱ፣ ጽንፈኞቹ ደግሞ በስድብ ያሸማቅቁዋቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ‹‹ሌላ ነገር ፍለጋ›› እስከሚያስመስልባቸው ፎቶግራፎቻቸውን ሲለጥፉ መካሪ የላቸውም ያስብላል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ‹‹መብቴ ነው›› እስካለ ድረስ መብቱን ማክበር ማንን ይጎዳል? የዛሬ ዓመት ገደማ ይመስለኛል አንዲት ጓደኛችን ‹‹ፕሮፋይል›› ለውጣ በአዲስ ገጽታ የልደቷ ቀን ትቀርባለች፡፡ የሚያውቋት በሙሉ ‹‹መልካም ልደት›› በማለት መልካም ምኞታቸውን ይገልጹላታል፡፡ አንድ ጽንፈኛ ፖለቲካ ወፈፍ ያደረገው ታዋቂ ጋጠወጥ፣ ‹‹ቅዳሜና እሑድ ሳይቆጠር ሃምሳ ዓመት እንደሞላሽ እነዚህ የወንድ ያለህ የሚሉ ዓይኖችሽ ያሳብቃሉ…›› በማለት ሲሰድባት እንኳን እሷ በርካቶች አዘኑ፡፡ እሷም የፌስቡክ ገጿን ዘግታ ሥራዋ ላይ ብቻ ከማተኮር ውጪ ተስፋ ቆርጣለች፡፡
ከላይ የዘረዘርኩላችሁን ሁሉ የነገርኩት አንድ ጓደኛዬ በሁኔታው ማዘኑን ገልጾልኝ አንድ አስገራሚ ነገር ነገረኝ፡፡ እሱ እንደሚለው አንድ ለሰው ልጅ ነፃነት ደንታ የሌለው ግለሰብ አብራው በምትሠራው ወጣት ላይ አሳዛኝ ነገር ይፈጽማል፡፡ ጋብቻ ለመፈጸም የሁለት ሳምንት ጊዜ የቀራትን ወጣት ድንገት ከቢሮ ወጣ ማለት ተመልክቶ፣ ላፕቶፕዋ ውስጥ ያሉትን ፎቶዎች በሙሉ ኮፒ ያደርግና ይወስዳል፡፡ በአጋጣሚ የሴት ጓደኛዋ ያነሳቻትን የራሷን እርቃን ፎቶዎች አሳጥቦ ለዕጮኛዋ ይልክለታል፡፡ በዚህም ምክንያት የዋሁ ዕጮኛ ጋብቻውን ይሰርዛል፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ይለያያሉ፡፡ በኋላ በስሚ ስሚ ሲጣራ ይኼው ሰው ፎቶግራፎቹን መላኩ ይታወቃል፡፡ ለምን ተብሎ አጥብቆ ምክንያቱ ሲጠየቅ፣ ልጅቷና ይህ ክፉ ሰው በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ አመለካከት ስለሚለያዩ ብቻ ነው፡፡ የዘመናችን ጽንፈኝነት ሰውን እንዲህ አውሬ እያደረገው ነው፡፡
(ን. አለማየሁ፣ ከገርጂ)