Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየቁጠባ ሒሳብን በማንኛውም ሰዓት ማንቀሳቀስ ካልተቻለ ለምን እንቆጥባለን?

የቁጠባ ሒሳብን በማንኛውም ሰዓት ማንቀሳቀስ ካልተቻለ ለምን እንቆጥባለን?

ቀን:

በአሁኑ ወቅት ባንኮች ቁጠባ የሚያድፍበት ዘመን መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በርካታ ቅርንጫፎችን መክፈት ልዩ ሒሳቡን ማዘጋጀት፣ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማዘጋጀት፣ የባንኮች የዕለት ተዕለት ሥራ ሆኗል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ረገድ ከ900 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ ልዩ የሕፃናት፣ የወጣቶችና የሴቶች ቁጠባን በማዘጋጀት ‹‹ቆጥበው ይሸለሙ›› በሚል የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በዚህ ሰሞን ያጋጠመኝ ኩነት ግን ከዚህ የባንኩ ዓላማ የሚፃረርና ሊታረም የሚገባው ሆኖ አገኘሁት፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በባንኩ የከፈትኩትን ሒሳብ አልፎ አልፎ ካልሆነ በየቀኑ አላንቀሳቅሰውም፡፡ እንዲህ ማድረግ እንኳን ለደመወዝተኛ፣ ለነጋዴም አይቻለውም፡፡ ሒሳቡን በመጨረሻ ያንቀሳቀስኩት ከወር በፊት ነው፡፡ በዚህ ሰሞን ገንዘብ ቸግሮኝ በባንኩ አንድ ቅርንጫፍ ሳመራ ‹‹ሒሳብህ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል አሉኝ›› በወቅቱ ገንዘቡን በጣም እፈልገው ስለነበር ካውንተሩ ላይ ድርቅ ብዬ ቀረሁ፡፡ የባንክ ሠራተኛዋ ሒሳብ ወደከፈትክበት ቅርንጫፍ ሄደህ ምክንያቱን ጠይቅ ብላ ስለመከረችኝ፣ ደምበል ወደሚገኘው የባንኩ አፍሪካ ጎዳና ቅርንጫፍ አመራሁ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታትን ባለሙያ ስጠይቃት ‹‹ሒሳቡ ረዥም ጊዜ ሳልተንቀሳቀሰ ለራስህ ብለን እንዳይንቀሳቀስ (Inactive) አድርገነዋል፤›› ብላ መልስ ሰጠችኝ፡፡ ሒሳቡን ያንቀሳቀስኩት ከወር በፊት ነው፣ ብዙ ሩቅ አይደለም፤ ከዚያም በላይ ገንዘቤን በፈለኩት ጊዜ ካላንቀሳቀስኩ ትርጉም እንደማይኖረው በመግለጽ የታገደበትን ምክንያት ጠየኳት፡፡ ባንከሯም ማብራራት ቀጠለች ‹‹ሒሳቡ እንዳይንቀሳቀስ የተደረገው በባንክ ሕግ መሠረት ነው፡፡ የባንኩ የሙስና ሠራተኞች ለረዥም ጊዜያት ያልተንቀሳቀሰን ሒሳብ እንዳይመዘብሩት በማሰብ ለእርስዎ ጥንቃቄ በማለት ዕርምጃውን ወስደናል፤›› አለች፡፡

ባንከሯ የሰጠችኝን መልስ በቁጠባ ሒሳብ ደብተሩ ጋር ከተቀመጡትና ከሕጉ አንፃር ብመረምረውም የባንኩ አቋም ውኃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በውሉ ላይ ያለ ደንበኛው ፈቃድ የደንበኛውን ሒሳብ ባንኩ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ በቁጠባ ሒሳቡ ላይም የተሰጠ የፍርድ ቤት ዕገዳ የለም፡፡ ለደንበኛው ጥቅም ነው ከተባለም፣ ለደበኛው ማሳወቅ አይቀልም ኖሯል? ይኼም አልተደረገ፡፡ ለሁለት ወር ሒሳቡ አለመንቀሳቀሱ ባንኩን ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ባንኩ ከሚከፍለው ወለድ መጠን በላይ በመጠየቅ ለተበዳሪ ያዳርሰዋል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ባስብም የባንኩን ሥራ ተገቢነት የሚያረጋግጥልኝ መልስም፣ ሕግም አጣሁ፡፡ ሰዎችን ስጠይቅ ተመሳሳይ ልማድ መኖሩንና እነሱም እንዲህ ያለው ተግባር ሲያጋጥማቸው እጅጉን እንደተበሳጩ ነገሩኝ፡፡

መፍትሔ ነው ያደረኩት በባንኩ ያለኝን ሒሳብ በመዝጋት በሌላ ባንክ ገንዘቤን ማስቀመጥ ነው፡፡ አማራጭ ባለበት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኢንተርኔትና በሞባይል የባንክ አገልግሎት በሚሰጥበት ዘመን፣ በአካል ያውም ጊዜውን ሰውቶ ለመጣ ደንበኛ የባንኩ ዕርምጃ ምኅረት የለሽ ነው፡፡ የቅርንጫፉ የብቻው አሠራር ይሁን የባንኩ ፖሊሲ መረጃ ማግኘት ግን አልቻልኩም፡፡ የቅርንጫፉ ሰዎች ግን ሒሳቤን በመዝጋቴ የተደሰቱ እንጂ የፀፀታቸው አይመስሉም፡፡ የሚከፈላቸው ደመወዝ፣ የአገሪቱ ትላልቅ የልማት ሥራዎችም በቁጠባ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ በብድር ተሰጥቶ ወይም በትርፍ በተገኘው ገንዘብ መሆኑን ዘንግተውት ይሆን?

(ታሪኩ ደነቀኝ፣ ከብሥራተ ገብርኤል)

********

የቀድሞ ምክር ቤት አባላት በቤት ላይ ቤት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?

ይህን ማስተዋሻ እንድጽፍ ያስገደደኝ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በትውልድ አካባቢያቸው የራሳቸው ወይም የግላቸው መኖሪያ ቤት እያላቸው መንግሥት ግን እንደየምርጫቸው ኮንዶሚኒየም ቤት ለእያንዳንዱ አባል ከፈለገው ሳይት የፈለገውን የቤት ዓይነት እንደተሰጠ ይታወቃል፡፡

 እነዚህ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለሦስተኛ ጊዜ ቤት ለማግኘነት በማሰብ በአዲስ አበባ በተለያዩ ባንኮች የኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ በመቆጠብ ላይ ይገኛሉ፡፡ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምክር ቤት በነበሩበት ጊዜ በተሰጣቸው ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ እየኖሩ ቢገኙም፣ የሌሎችን ዜጎች ዕድል ለመሻማትና ለመጉዳት በማሰብ ይመስላል አሁንም የቤት ዕጣ ውስጥ እየገቡ ያሉት፡፡ በድጋሚ ተመዝግበው በተለያዩ ባንኮች የኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ ጀምረዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ለሕዝብ  ነው ወይስ ለሆዳቸው የቆሙት? የሚመለከተውን አካል መጠየቅ የምፈልጋቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. በኦሮሚያ ክልል ከአንድም ሁለት የግላቸው ቤት እያላቸው በተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው ምክንያት ለሦስተኛ ጊዜ ኮንዶሚኒየም ቤት ከመንግሥት ተሰጥቷቸው ሳለ ይህም ሳይበቃቸው አራተኛ የመንግሥት ቤት ለማግኘት በተለያዩ ባንኮች ተመዝግበው በመቆጠብ ላይ የሚገኙ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባሎች ጉዳይ እንዴት ይታያል? ማነው ስለዚህ ጉዳይ የሚመለከው?
  2. መንግሥት ኮንዶሚየም ቤት የሰጠው ግለሰብ በድጋሚ ተመዝግቦና ቆጥቦ  ተጨማሪ ቤት ማግኘት ይችላል ወይ?
  3. በግላቸው ተወዳድረው ወይም ሕዝብ ወክሏቸው ምክር ቤት የነበሩ አባላት፣ ቤት ከመንግሥት ከተሰጣቸው በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት መመዝገብ ይችላሉ ወይ?
  4. በተለይ በርካታ የኦሮሚያ ክልል የቀድሞ የምክር ቤት ተወካዮች በአዲስ አበባ  በተለያዩ ባንኮች ተመዝግበው በመቆጠብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሲብስም አንድ ሰው በሁለት የተለያዩ ባንኮች እየቆጠበ እንደሚገኝ እንሰማለን፡፡ ለአንድ ግለሰብ ሦስት ቤት መስጠት መነሻው ምንድን ነው?
  5. በክልሎች የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችና በአዲስ አበባ የተሠሩት ቤቶች አስተዳደርም ሆነ አረካከብ ላይ ያለው ቅንጅት ምን ይመስላል? ምንክያቱም በክልል የተገነቡትን ወስደው በአዲስ አበባም የወሰዱ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃልና ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዴት ያየዋል? የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ መልሱን በሪፖርተር ላይ ባነብ ደስ ይለኛል፤ ደግሞም እጠብቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ ነውና የሚመለከተው አካል መልስ ይስጥበት፡፡

(ከአሴ ብራ፣ ከአዲስ አበባ)

  •  

ፕሪምየር ሊጉ ከልካይ ያጣ ስጥ ሆነ እንዴ?

 በአገራችን ከሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮች ዋናውና ከተጀመረም ከአሥርት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣  ከጅማሬው አንስቶ የነበረው የተጫዋቾች ክፍያና ጥቅማጥቅም መጠን ቀስ በቀስ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢመጣም በተቃራኒው ግን የክለቦች የእርስ በርስ ፉክክር አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም ከሚሉ ፉክክሮች በቀር ከዓመታት በፊት የነበረውን ማራኪ ውበት ማሳየት ከተሳነው ሰንበትበት ብሏል፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት በተለይ ተጫዋቾች ከእነሱ የሚጠበቀውን ብቃትና ክህሎት ለተመልካች አለማሳየታቸው ሲሆን፣ ይህም ሊጉ ፉክክር አልባ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፣ ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም›› እንዲሉ እግር ኳስ ተጫዋቾች ለሊጉ የሰጡት ቦታ አናሳ በመሆኑ ተገቢውን የስፖርት ስሜትና ፉክክር ለማየት አላስቻለንም፡፡ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ታቅፈው ተሳታፊ ከሆኑ ወዲህ የራሳቸውን ብቃትና ክህሎት ለማሳደግ በጎንም የሊጉን ውበት ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት በእኔ እምነት አናሳ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህንን ስል ተጫዋቾች እንደሚፈልጉት ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖላቸዋል ለማለት አይደለም፡፡  የግል ብቃታቸውና ክህሎታቸውን ዕለት ተዕለት በማሳደግ ከእግር ኳሱ መጠቀም የሚገባቸውን ያህል በአግባቡ እየተጠቀሙ ያሉ ጥቂት ተጫዋቾች መኖራቸውንም ሳልዘነጋ ነው፡፡

 ‹‹ለሺሕ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› ነውና ይህንን ሐሳብ እንዳነሳ ያስገደደኝ የአገር ውስጥ ስፖርትን በተለይ ፕሪምየር ሊጉን በአትኩሮት እንደመከታተሌ፣ በአገሪቱ ስፖርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በሚዘጋጅና በቅርቡ በተላለፈ ፕሮግራም ላይ የፕሪምየር ሊጉ አንደኛ አጋማሽ የውድድር ጊዜ የተጠናቀቀ እንደመሆኑ ክለቦች የተለያዩ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ላይ የሚገኙበት ጊዜ መሆኑን አስመልክቶ የተነሳ ሐሳብን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ከአምስትና ስድስት ዓመታት በፊት ጥሩ አቋም የነበራቸውና ከዚያ ወዲህ ግን እግር ኳስን በማንኛውም ክለብ ታቅፎ በመደበኛነት መጫወትን ያቆሙ ተጫዋቾች፣ አሁን በተከፈተው የፕሪምየር ሊጉ የዝውውር መስኮት በውጤት ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ክለቦች ለመፈረም ድርድር መጀመራቸው፤ እንዲሁም በክህሎት ሳይሆን በጥቅማጥቅም ምክንያት ለመፈረም ካሰቧቸው ክለቦች ውስጥ ለአብዛኞቹ ፊርማቸውን ስለማኖራቸው ስንሰማ፣ ሊጉ ከዓመት ዓመት መሻሻል አለማሳየቱን ያሳየናል፡፡

ለዓመታት ከእግር ኳስ የራቁ የቀድሞ ተጫዋቾች ክህሎትና ብቃት ላለፉት አምስት ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ እግር ኳስ እየተጫወቱ ካሉት ጋር ልዩነት እንዲኖረው ካልተደረገ፣ ፕሪምየር ሊጉ ማንም መንገደኛ እንሚዘግነው ከልካይ አልባ ስጥ ውድድሩም ባለበት መቆሙ ማንኛውም ተጫዋች ባሰኘው ጊዜ፣ ጥሩ ክፍያና ጥቅማጥቅም ሊያገኝ የሚችልበትን ወቅት እየጠበቀ እንዳሻው በሊጉ የሚሳተፍበት ከሆነ፣ መሻሻል አይችልም የሚል የግል አቋም አለኝ፡፡

ለአብነት ያህል በቅርቡ በሚዲያ የሰማሁትን ጠቀስኩ እንጂ የሊጉን ወደፊት ያለመራመድ የተረዱና በአሁኑ ወቅት ኳስ ያቆሙ በርካታ ተጫዋቾች አሁንም በሊጉ መጫወት እንደሚችሉ በተለያየ ጊዜ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ ሊጉን አሁን ከሚገኝበት ይልቅ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች፣ የክለብ ኃላፊዎችና አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ከስፖርቱ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን በመወጣት የሊጉን ጥራት በማሳደግ የአገሪቱን የእግር ኳስ ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ፡፡

በመጨረሻም በ1990ዎቹ ዓመታት ደምቀው ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረውና በ2005 ዓ.ም. ከአሸዋ ሜዳ አስከ አርጀንቲና በሚል ርእስ በሰጠው የግል እውነተኛ ታሪክ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ አሸናፊ ግርማ በአሁን ወቅት ለሚጫወቱ ተጫዋቾች እንዲሁም የሊጉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያስችላል በማለት ባስተላለፈው መልዕክት ሐሳቤን ላጠቃልል፡፡ ‹‹አንድ ተጫዋች ትልቅ ደረጃ ለመድረስ በመጀመርያ የእግር ኳስ ፍቅር፣ ዓላማና ዲሲፕሊን ሊኖረው ይገባል፡፡ ችሎታውና ለኳስ ያለው ፍቅር ተጫዋጭ ከሆነ ዓላማውን ለማሳካት ያግዘዋል፡፡ ችሎታ ያለ ዓላማና ሥነ ምግባር የትም ሊያደርስ አይችልም፤›› ብሏል፡፡ ስለዚህ መቼ ይሆን የአገሪቱ ሊግ ከልካይ የሌለው ስጥ ከመሆን ወጥቶ የማይናቅ፣ ጠንካራና የተከበረ የሚሆነው? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡

               (ቶፊቅ ተማም፣ ከአዲስ አበባ)

*******

መንግሥት ያቋቋመው ኢንዱስትሪ ወይስ አትሌቲክስ መንደር?

‹‹መንግሥት በሲኖትራክ ሳቢያ የሚከሰተውን አደጋ የሚያጠና ግብረ ኃይል ማቋቋሙ ተሰማ›› የሚል ዜና በየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ላይ ሳነብ፣ አሁንም ‹‹ገና ጥናት?›› ነበር ያልኩት፡፡ ከነአባባሉ፣ ‹‹አለንጋ እስኪገዙ፣ በክርን ይተክዙ›› ነውና ከጥናቱ ቀድሞ ቀላሉን ነገር ብንጀምር መልካም ይመስለናል፡፡ ምክንያቱም ከጥናቱ በፊት እንዳናልቅ ሥጋት ስላለን፡፡

ለሕዝብ ግልጽና ሁሌም የሚታየው የሲኖትራኮች ከመጠን ያለፈ በረራ ወይም ገደብ የለሽ ፍጥነታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ መንግሥት፣ ‹‹የኢንዱስትሪ ዞኖች›› ብሎ ከከለላቸው አካባቢዎች መካከል፣ ‹‹ግዙፍ›› የተባለው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ መንደር ነው፡፡ ይህ መንደር በገርጂ መብራት ኃይል በኩል ጃክሮስ አደባባይ ሲደረስ ወደ ቀኝ በመታጠፍ የረርን፣ ጎሮንና ሠፈራን አልፎ የሚገኝ ነው፡፡ ወደዚህ ኢንዱስትሪ ዞን ከሚጓዙት ተሽከርካሪዎች የሚበዙት ሲኖትራክ የሚባሉት ከባድ የጭነት መኪኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ገና ጃክሮስን እንዳለፉ ለውድድር የተጠሩ ይመስል የሚከንፉበት ፍጥነት ነዋሪውን በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ሰቀቀን ውስጥ ከቶታል፡፡ በተለይ ሠፈራ አደባባይን ወይም መስጊድን ከተሻገሩ በኋላ የሚታየው ክንፊያ ተዓምር ያሰኛል፡፡ አንዳንዶችማ፣ ‹‹መንግሥት ያቋቋመው ኢንዱስትሪ ነው ወይስ አትሌቲክስ መንደር?›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ይህ መንገድ እግረኞች በብዛት ከሚጓጓዙባቸው አንዱ ሲሆን፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች የሚገኝበት ቢሆንም ከልካይ የሌላቸው፣ ልጓም አልባ ጋላቢዎች ሰዉን እየገጩና እየቀጩ ከዚህ ዓለም ያሰናብታሉ፡፡ እየታየ ያለው፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ የሚደረግ ሩጫ እንጂ መከላከሉ ላይ የሚሠራ ሥራ አይደለም፡፡ የሲኖትራክ አሽከርካሪዎችን አትኩሬ ስመለከታቸው፣ ጥቂት የማይባሉት የልጅነት ወይም አፍላ የጉርምስና ጊዜያቸውን አጣጥመው ያልጨረሱ ናቸው፡፡

ለማንኛውም ሥራ ለትልቅ ነገር የሚታጭ ሰው ልምዱና ብስለቱ ታይቶ እንጂ፣ ‹‹ተምሯል›› የሚል ወረቀት ስለያዘ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ሌላ ደረጃ በደረጃ ያሉትን የትምህርት ሒደቶች ሳይከታተሉና በዚያ ሠርተው ሳይፈተሹ በአንድ ጊዜ አናት ላይ ፊጥ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በሲኖትራክ አሽከርካሪዎች ላይ የሚታየውም ይኸው ነው፡፡ ከብስለት ማነስ በተጨማሪ በአንድ ጊዜ አራተኛ መንጃ ፈቃድ ላይ ጉብ ተብሎ መሪ እየጨበጡ እንደገድለኛ ዜጎች ላይ በማናለብኝነት መፈርጠጥ፣ መብቱን እየተጋፉ ሕይወቱን ለአደጋ ከማጋለጣቸውም ባሻገር ራሳቸውንም የማይወጡት ችግር ውስጥ እየከተቱ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ መንግሥትም የዕድሜ፣ የብስለት መመዘኛዎችና የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡን ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡    

(እስክንድር መርሐጽድቅ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...