Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትከመራጩ ሕዝብ በቀር ሌላ ‹‹አምላክ›› አናምልክ

ከመራጩ ሕዝብ በቀር ሌላ ‹‹አምላክ›› አናምልክ

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

በኢትዮጵያ የምርጫ ካሌንደር መሠረት አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ የድምፅ መስጫ ዕለት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ከየካቲት 16 ቀን ጀምሮ ደግሞ የድምፅ መስጫውን ዕለት የምርጫ ካሌንደሩ የኋሊት መቁጠር ጀምሯል፡፡

በምርጫ ሕጉ መሠረት የምርጫ ዘመቻ እንቅስቃሴ የሚጀምረው ዕጩ ተወዳዳሪዎች በዕጩነት ተመዝግበው መታወቂያ ካገኙበት ቀንና ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ፕሮግራም ወይም የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነው፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2007 ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመሻሻሉ በፊት (እስካሁን የተሻሻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው) የዕጩነት ማረጋገጫ መታወቂያ ካርድ የሚሰጥበት ጊዜ ከየካቲት 2 ቀን እስከ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ተብሎ ተይዞ ነበር፡፡ የካቲት 7 ቀን 2007 ደግሞ የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በይፋ የሚጀምርበት ቀን ሆነ ተወሰነ፡፡

- Advertisement -

የዕጩዎች ምዝገባ የጊዜ ገደብ በአንድ ሳምንት በመራዘሙ ምክንያት፣ በተለይ የምርጫ ዘመቻው እንቅስቃሴ የሚጀምርበት ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ ‹‹የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ›› በአንድ ሳምንት ከተራዘመ በኋላም፣ እንዲሁም የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴው ከየካቲት 16 ቀን ጀምሮ እነሆ አሁን ድረስ የቀጠለና በመካሄድ ላይ ያለ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የዕጩዎችን ማንነት አናውቅም፡፡ የዕጩ ተወዳዳሪዎችን የተጠናቀረ ሊስት (የስም ዝርዝር) ይፋ ሆኖ አላየንም፡፡ የመጀመሪያው እግረ መንገዳችንን የምናነሳው የዛሬው ጉዳይ አንዱ ይኸው ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋናው ጉዳይ ግን በአንድ የምርጫ ክልል (ወይም የምርጫ አጥቢያ) ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩ ተወዳዳሪነት የመቅረብ መብትን በ12 የወሰነው የምርጫ ሕግ ይዘትና አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡

ጉዳዩን በሰፊውና በዝርዝር መመልከት ይቻለን ዘንድ መጀመሪያ በሕግ የተወሰኑ የቁጥር ጉዳዮችን ጠጋ ብለንና አገላብጠን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው በሕገ መንግሥቱ በራሱ የተወሰነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት የሚመረጡ ከ550 የማይበልጥ ቁጥር ያላቸው እንደራሴዎች ናቸው፡፡ ይህን የደነገገው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱና በ1999 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ መሠረት የኢትዮጵያ የምርጫ ክልሎችና የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ550 አይበልጥም፡፡ በዚህ ‹‹ተዓምራዊ›› ወይም ‹‹አስማታዊ›› ቁጥር መሠረት ያለፉት ምክር ቤቶች አባላት ቁጥር ብዙ ጊዜ 547 ነበር፡፡ የአሁኑም እንደዚያው ነው፡፡

የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ከ550 የምርጫ ክልሎች (የምርጫ አጥቢያዎች) በላይ አያስተናግድም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴዎችም ከ550 አይበልጡም የማለት ሥሌት ትርጉምም ከአንድ የምርጫ ክልል አንድ ተወካይ ማለት ነው፡፡ ይህ ግን የሥሌትና የሒሳብ ውሳኔ አይደለም፡፡ ሕጉ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ የምርጫ ክልል አንድ ተወካይ ብቻ ይመረጣል ይላል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃምሳ ሚሊዮን በነበረበት ጊዜም አሁን 90 ሚሊዮን ገባ ሲባልም፣ ወደ ፊትም በመቶ ሚሊዮን ቤት ሲቆጠርም የተወካዮቹ ብዛት ከ550 አይበልጥም፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በአንድ የምርጫ ክልል ለአንድ የምክር ቤት መቀመጫ አንድ ዕጩ ብቻ ማቅረብ አለበት (አንቀጽ 46/4)፣ ማንኛውም ሰው በዕጩነት የሚቀርበው በአንድ የምርጫ ክልል ብቻ ነው (56/1) ቢባልና እንዲህ ያለ የቁጥር ገደብ ቢኖር ትርጉም ይሰጣል፡፡

ምርጫ 2007 ላይ ያነጋገረውና ነገር ያመጣው ግን ከዚህ የተየ የቁጥር ውሳኔ ነው፡፡ ይህም የዕጩዎችን ብዛት የሚወስነው የምርጫ ሕጉ ድንጋጌ ነው፡፡ በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም ይላል፡፡ (49/1) የአዋጁ አንቀጽ 49 የተቀሩት ድንጋጌዎች ሌሎች ንዑሳን አንቀጾች ከ12 በላይ ዕጩዎች ሲኖሩ የሚለዩበትን ሁኔታ የሚደነግጉ ናቸው፡፡ በአንድ የምርጫ ክልል ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ቁጥር ከዚህ በላይ (ለምሳሌ ከ12) መብለጥ የለበትም ማለትን የመሰለ የቁጥር ገደብ ግን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪዎች ብቻ የመጣ ‹‹ፍርጃ›› አይደለም፡፡ በክልል ምክር ወይም በሌሎች የምርጫ ደረጃዎች የሚቀርቡ ዕጩዎችን ብዛትም ገደብ አለበት፡፡

የምርጫ ሕጉ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ የምርጫ ክልል አንድ ተወካይ ብቻ ይመረጣል እንደሚል ከፍ ሲል ገልጸናል፡፡ የክልል ምክር ቤቶች የዚህ አቻ ድንጋጌ የክልል ምክር ቤቶች (ከአንድ የምርጫ ክልል የሚመረጡ) አባላት ቁጥር በየክልሉ ሕግ መሠረት ይወሰናል ይላል (አንቀጽ 28/4)፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት የምርጫ ክልሎቻችን ለፌዴራል ምክር ቤት አንድ ሰው ብቻ፣ ለክልል ምክር ቤት ከአንድ በላይ የሆነ ሰው የሚመርጥባቸው የምርጫ ክልሎች (አጥቢያዎች) ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ክልል ስንል የዘጠኙ ክልልና የ550ው ክልል አይምታታም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ማዕቀፍ ውስጥ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ የምርጫ ክልል የሚመረጠው አንድ ተወካይ ብቻ ነው፡፡ የክልል ምክር ቤቶች አባላት ቁጥር ደግሞ በየክልሉ ሕግ ውሳኔ መሠረት ይወሰናል፡፡

ለምሳሌ አዲስ አበባ የ23 የምርጫ ክልሎች አገር ናት፡፡ ከ550 የማይበልጡ ተወካዮች መርጦ ከሚልከው ድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ ሃያ ሦስቱን የምትመርጠው አዲስ አበባ ናት፡፡ እንዲያም ሆኖ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወካዮች ቁጥር 138 ነው፡፡ በዚህ ሥሌት ከአንድ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልል ውስጥ የሚመረጠው በአማካይ ስድስት ሰው ነው ማለት ነው፡፡

በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ቁጥር ከ12 መብለጥ የለበትም ከተባለ (አንቀጽ 49/1)፣ በአንድ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚቀርቡ ዕጩዎች ብዛትስ ገደብ የለውም እንዴ? ብለን ብንጠይቅ አዋጁ በአንቀጽ 46(6) ይህንን መወሰን የቦርዱ ሥልጣን አድርጎ ይወስናል፡፡

የጠቀስነውን የአዲስ አበባን ምሳሌ ይዘን እንቀጥል፡፡ አዲስ አበባ ለአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 (ስለዚህም 12×23) ከ276 ዕጩዎች መብለጥ አይችሉም፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የሚያስፈልጉትን 138 ተወካዮች ለመምረጥ በአንድ የምርጫ ክልል የሚቀርቡትን የዕጩዎች ብዛት የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 49(6) መሠረት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች 23 ስለሆኑ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ቁጥር 138 በመሆናቸው በአማካይ ከአንድ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልል ስድስት ሰው መመረጥ ስላለበት፣ ቦርዱ ለምሳሌ በአንድ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከአንድ የምርጫ ክልል ከ72 (6×12) መብለጥ የለባቸውም ብሎ ሊወስን ይችላል ማለት ነው፡፡ ዕጩዎቹ ከ72 ከበለጡ፣ እዚህም ላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅድሚያ በዕጩነት እንዲመዘገቡ ያደርጋል፡፡ በፖለቲካ ድርጅቶች የቀረቡት ዕጩዎች ከ72 በላይ ከሆኑ ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ላገኙት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ቀሪዎቹ በዕጣ ይለያሉ ወዘተ…

በአዲስ አበባ ምሳሌነት የክልሎችን ጉዳይ ያመጣነው በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም የሚለው ሕግ፣ የክልሎችን የዕጩዎች ብዛት ራሱን በውክልና ለቦርዱ የሰጡበትን ‹‹የባሰ›› ሁኔታ ለማሳየትም ነው፡፡

በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ ስለሌለበት፣ በዚህ ሥሌት በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከ6,600 ዕጩ ተወዳዳሪ በላይ ቢንቀሳቀስ ክልክል ነው ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ 547 ተወካዮች ለመምረጥ ከዚህ የሰፋ ምርጫና ውድድር አትፈቅድም ማለት ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 38 የማናቸውንም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩት የአብዛኞቹ የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች ‹‹የማንኛውም ሰው…›› ሆነው ሳለ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ከተቀሩት ሌሎች (የዜግነት የንብረት) መብቶች ጋር የኢትዮጵያውያን ብቻ ሆነው ተደንግገዋል፡፡ በርካታ አገሮች ውስጥ ለተወሰኑ የቀበሌ፣ የአጥቢያና የጭቃ ዓይነት ምርጫዎች የመሳተፍ መብትን ከዜጋም በላይ ለነዋሪ (ለቋሚ ነዋሪ) ጭምር ቢሰጡም በአገር የመንግሥት አስተዳደር የመሳተፍ መብት የዜጋ መሆኑ ተገቢ ነው፡፡ ኦባማ የተወለዱት አሜሪካ አይደለም ማለት አይነት መከራከሪያ የመጣው እንደዚህ ባሉ አገሮች ከዜግነት በላይ (በሕግ ወይም በቅባት ከሚገኝ ዜግነት በላይ) ከዜጋ መወለድ ወዘተ ግዴታ የሚያደርግ የጠበቀ የምርጫ ሕግ ስላለም ጭምር ነው፡፡

ለዜጋ ብቻ የተከለለውና ዜጋ ላልሆነ የተከለከለው የመምረጥና የመመረጥ መብት ከዚያም በላይ የዕድሜና የነዋሪነት መመዘኛዎች ሁሉ አሉበት፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በአንድ የምርጫ ክልል ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 ወይም ለክልል ምርጫ ሲሆን ደግሞ ምርጫ ቦርድ ከሚወሰነው ቁጥር በላይ መሆን የለበትም ማለት የጤና ነው ወይ ተብሎ መጠየቁ ተገቢና ጤናማ ጥያቄ ነው፡፡

የሚገርመው የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን የዕጩዎችን ብዛት በቁጥር የወሰነውና ከዚያ ሲያልፍም መለያ ዘዴውን የደነገገው በኩራትና በልበ ሙሉነት እንደሚነገረው፣ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ትናንት በ1999 ዓ.ም. አይደለም፡፡

ድኅረ ደርግ የወጣው የመጀመሪያው የምርጫ ሕግ የብሔራዊ፣ የክልላዊና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣው የጥር 30 ቀን 1984 አዋጅ ነው፡፡ ይህ ሕግ እንዲህ ያለ የዕጩዎች ብዛት የሚወስን ገደብ አልነበረውም፡፡ የዕጩዎችን ብዛት የሚወስን ድንጋጌ የያዘው የምርጫ ሕግ የወጣው በ1985 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላትን ለማስመረጥና ጉባዔውንም ለመጥራት የሚያስችል፣ በሚፀድቀው ሕገ መንግሥት መሠረት ሙሉ የሕዝብ ውክልና ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችሉ ምርጫዎች የማስፈጸሚያ ሥርዓት የሚደነግግ የምርጫ ሕግ መኖር አለበት ተብሎ አዋጅ ቁጥር 64/1985 ወጣ፡፡ ከነሐሴ 17 ቀን 1985 ጀምሮ የፀናው የምርጫ ሕግ የመጀመሪያውን የዕጩዎች ብዛት የሚወስን ድንጋጌ አዋጅ (አንቀጽ 43)፣

 1. በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም፣
 2. ለመመረጥ የተመዘገቡ ዕጩዎች ከ12 በላይ በሚሆኑበት ጊዜ በብዛት የድጋፍ ፊርማ ያገኙት 12 ዕጩዎች ተለይተው ለውድድር ይቀርባሉ፣
 3. ዕጩዎች ያገኙት የድጋፍ ፊርማ እኩል በሚሆንበት ጊዜ ለውድድር የሚቀርቡት በዕጣ ይለያሉ ተባለ፡፡ (በዚህ ሕግ መሠረት ለዕጩነት ከሚያበቁ መመዘኛዎች መካከል ዕጩው ከሚወዳደርበት የምርጫ ክልል ከተመዘገቡት መራጮች ውስጥ ከ500 የማያንስ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ መቻል ነው)፡፡

ከዚህ የ1985 ሕግ በኋላ የ1987 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ ወጣ፡፡ ይህ ሕግ የወጣው ‹‹ሕገ መንግሥቱን ያፀደቀው የሕገ መንግሥት ጉባዔ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት፣ በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት የመሪዎቹን ብሔራዊና የክልል ምርጫዎች እንዲያካሂድና እንዲያስፈጽም ሙሉ ውክልናና ሥልጣን የሰጠው በመሆኑ›› ነው፡፡ በዚህ የ1987 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ መሠረት ለዕጩነት ከሚያበቁ መመዘኛዎች አንዱ በፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት የቀረበ ዕጩ ከ500፣ በግል የቀረበ ከሆነ ከአንድ ሺሕ የማያንስ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተደረገና ከጥር 10 ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ ማሻሻያ ሕግ ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት የሚቀርብ ዕጩ ማሰባሰብ የነበረበት የ500 የድጋፍ ፊርማ ቀረ፡፡

የ1987 የምርጫ ሕግ

 1. በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም፣
 2. ለመመረጥ የተመዘገቡ ዕጩዎች ከ12 በላይ በሚሆኑበት ጊዜ በብዛት የድጋፍ ፊርማ ያገኙት 12 ዕጩዎች ተለይተው ለውድድር ይቀርባሉ፣
 3. ዕጩዎቹ ያገኙት የድጋፍ ፊርማ እኩል በሚሆንበት ጊዜ ለውድድር የሚቀርቡት በዕጣ ይለያሉ አለ፡፡ የዚህም ተፈጻሚነት እስከ 1997 ዓ.ም. ቀጠለ፡፡

በ1997 ዓ.ም. ጥር ወር የምርጫ ሕጉ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 438/97 ወጣ፡፡ ይህ ማሻሻያ አዋጅ የወጣው ‹‹በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሠረት ከዚህ በፊት በዴሞክራሲያዊ አኳኋን በተካሄዱት ምርጫዎች የተገኙትን መልካም ልምዶች ሁሉ አጠናክሮ መቀጠልና ቀጣዩን የምርጫ ሒደት አፈጻጸም ይበልጥ ማዳበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

‹‹በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ጋር ለማጣጣም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 111/1987 ማሻሻል አስፈላጊ›› ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

አዋጁ ካሻሻላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዕጩዎችን ብዛት የሚመለከተው ድንጋጌ ነው፡፡ ከፍ ሲል እንዳለ ሙሉ ቃሉን የጠቀስነው የዕጩዎችን ብዛት የሚደነግገው የ1987 ዓ.ም. ሕግ ተሰረዘና በአዲሱ ተተካ፡፡ በዚህም መሠረት የዕጩዎች ብዛት፣

 1. በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም፣
 2. የዕጩዎች ብዛት ከ12 ከበለጠ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅድሚያ በዕጩነት እንዲመዘገቡ ይደረጋል፣
 3. በፖለቲካ ድርጅቶች የቀረቡት ዕጩዎች ከ12 በላይ ከሆኑ ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ላገኙ ከስድስት ለማይበልጡ ድርጅቶች ቅድሚያ ይሰጣል፣ ቀሪዎቹ በዕጣ ይለያሉ፣
 4. በፖለቲካ ድርጅቶች የቀረቡት ዕጩዎች ከ12 በታች ከሆኑ የቀሩት ቦታዎች ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ባገኙ የግል ተወዳዳሪዎች እንዲሞሉ ይደረጋል፣
 5. እኩል የድምፅ ብዛት ያላቸው ዕጩዎች ካሉ በዕጣ እንዲለዩ ይደረጋል፣
 6. በአንድ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ወይም ለሌሎች የምርጫ ደረጃዎች የሚቀርቡ ዕጩዎች ብዛት በቦርዱ ይወሰናል፣ የዕጩዎች ቁጥር ቦርዱ ከወሰነው ቁጥር በላይ የሆነ እንደሆነ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 መሠረት ይወሰናል፣
 7. በዚህ አንቀጽ መሠረት ዕጣው የሚወጣው የሚመለከታቸው ዕጩዎች ወይም ተወካዮቻቸው በተገኙበት ይሆናል፡፡

የ1999 ዓ.ም. የተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 49 ‹‹የዕጩዎች ብዛት ስለመለየት›› ድንጋጌ በምርጫ 97 ዘመን ውስጥ የተሻሻለው የምርጫ ሕግ ‹‹የዕጩዎች ብዛት›› ድንጋጌ ቀጥተኛና ትክክለኛ ግልባጭ እንጂ ያልነበረ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በአንድ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ቁጥር የመወሰን አሠራር ከ85 የጀመረ፣ በ87 እና በ97ም የነበረ እንጂ 2002 ምርጫ ላይ ተፈጻሚነቱን የጀመረ የ1999 ሕግ አዲስ ፈጠራ አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላት ምርጫ፣ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫም ጭምር የተካሄደው የዕጩዎችን ቁጥር የሚወስን ሕግ ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

ደጋግመን እንደገለጽነው የመጀመሪያው የ1985 ዓ.ም. የምርጫ ሕግ የ1987ቱም ጭምር በአንድ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከ12 መብለጥ የለባቸውም ይላል፡፡ ይል ነበር፡፡ በ2007 ምርጫ ተፈጻሚ ሆኖ የሚገርሙ ሰለባዎችን የጣለው የምርጫ ሕግ የዕጩዎች ብዛት ድንጋጌ በ1999 ዓ.ም. ሕግ የያዘውን ቅርፅና ይዘት ያገኘው ከአሥር ዓመት በፊት በምርጫ 97 እንቅስቃሴ ሒደት ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ‹‹ማናችንም›› የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሚከነክነው እንዲህ ያለን ሕግ በምርጫ 97 ውስጥና ከዚያ በኋላም ማስተዋል የቻለ ብሔራዊ ህሊናና ግንዛቤ አለመኖሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን (የዕድሜ፣ የምርጫ ክልሉ ውስጥ ኗሪ የመሆን፣ ወዘተ) መመዘኛዎችን ሲያሟሉ የመምረጥና የመመረጥ መብት አላቸው ለየሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ፣ በሌላ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ይበልጥ የተጠናከረና ሕገ መንግሥታዊ ምሽግ የገነባ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምዕራፍ በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች (የመምረጥና የመመረጥ መብትን ጨምሮ) ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በርካቶቹን መሠረታዊ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን አፅድቃ የራሷ ሕግ አካል አድርጋለች፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ የዕጩዎችን ቁጥር በምርጫ ክልል የሚወስን ሕግ ልትደነግግ አትችልም፡፡ እንዲህ ያለ ሕግ የዴሞክራሲያዊው ምርጫ የጭቃ እሾክ ነው፡፡

እንዲህ ያለ ሕግ አንቅቶ፣ ጠንስሶ፣ ወጥኖ የተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቅለት ያቀረበው የመንግሥት የአስፈጻሚው አካል ዓላማ ግር ቢልም፣ ከሁሉ የበለጠ የሚያሳዝነው የተቃውሞው፣ የምሁሩ፣ የወዘተው ጎራ የዚህ ድንጋጌ እባጭ እስኪፈነዳ ድረስ ችግሩን ሳያውቅና ሳናውቅ መቆየታችን ነው፡፡ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው፡፡

የምርጫ ቦርድ አመራሮች፣ አስተያየት ሲሰጡ የሚሰሙ የሕግ ባለሙያዎች የተመራጮች ብዛት በቁጥር መወሰን አለበት ብለው የሚከራከሩበት ዋነኛውና ምናልባትም ብቸኛው ምክንያት፣ የምርጫውን ሥራ አካሄድ ከመምራት አኳያ ቁጥሩ ‹‹ማኔጀብል›› መሆን ስላለበት ነው፡፡ የምርጫው ሒደት በቀላሉ የሚመሩትና በቁጥጥር ሥር የዋለ መሆን አለበት የሚሉ ሰዎች፣ የሚፈሩትን የመጨረሻውንና ከፍተኛውን አደጋ እስቲ አርቀን እንመልከት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የ547 ግፋ ቢል ደግሞ የ550 የምርጫ ክልል አገር ናት፡፡ እያንዳንዱ የምርጫ ክልል (ኮንስቲትዌንሲ) በየምርጫ ዘመኑ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በ550 ተካፍሎ ከሚገኘው አማካይ ቁጥር ጋር ተቀራራቢ የሆነ የሕዝብ ብዛት የሚያጠቃልል የምርጫ ክልል ነው፡፡ ጉዳዩን አጠርና ቀለል ለማድረግ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ 100,000 ነዋሪ አለ እንበል፡፡ ለነገሩ ለአቅመ ምርጫ በቅቶ የተመዘገበው ከ34 ሚሊዮን በላይ ነው ስለተባለ፣ የእያንዳንዱ የምርጫ ክልል አማካይ ሕዝብ ቁጥር ከዚያ በታች ነው፡፡ 60 ወይም 70 ሺሕ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ያን ያህል ሕዝብ ምረጡኝ ብሎ ቢንቀሳቀስ ይህን በምን ይመልሱታል? ተብሎ ተፈርቶ ከሆነ ህንድ በሁሉም ረገድ ግሩም ምሳሌ ናት፡፡

የህንድ ሕዝብ 1.2 ቢሊዮን ነው፡፡ በምርጫ 2014 የተመዘገበው የመራጭ ሕዝብ ቁጥር 814 ሚሊዮን ነው፡፡ ህንድም እንደ ኢትዮጵያ የ543 የምርጫ ክልል አገር ናት፡፡ ህንድ በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ዴሞክራሲ የምትባል ናት፡፡ 543 ወንበር ለመወዳደር የተመዘገቡት የ2009 ምርጫ ዕጩዎች ቁጥር 8,070 ነበር፡፡ በአገሪቱ የ16 አጠቃላይ ምርጫ ታሪክ ውስጥ አጠቃላይ የዕጩዎች ትልቁ ቁጥር 13,952 ነበር፡፡ በአንድ የምርጫ ክልል የቀረበ ዕጩ ተወዳዳሪ በአማካይ 26 ያህል ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ህንድ ውስጥ ተጀምሮ እስኪጨረስ የአንድ ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ትልቁ ቁጥር ከ43 (2009 እ.ኤ.አ.) በልጦ አያውቅም፡፡ በአንድ ወቅት (በ1996) ለተሚልናዱ የክልል ምክር ቤት በተደረገ ውድድር ከአንድ የምርጫ ክልል 1,033 ተወዳዳሪ ዕጩዎች ተሠልፈዋል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ትልቁ ‹‹አደጋ›› የምርጫ ወረቀቱን መጽሐፍ አካል (Booklet) አድርገው ማሳተማቸው ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በህንድ እንዲህ ሆነ አይደለም፡፡ ክርክራችን ታሚል ናዱ ‹‹ተሰማ ወሬ›› የሚልም አይደለም፡፡ በህንድ የምርጫ ሕግ ውስጥ የዕጩዎችን ቁጥርና ብዛት የሚገድብ ድንጋጌ የለም የሚልም አይደለም፡፡ የምርጫውን አስተዳደርና ሥራ አካሄድ “Unmanageable” (ከቁጥጥር ውጭ) ያወጣዋል ብሎ እንዲህ ያለ ገደብ ማበጀት የሚፈቅድ ሕገ መንግሥት የለንም፡፡ የምርጫ ቦርድ ሥራ ይህን ‹‹ማኔጅ›› ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ሌላ ሥራ የለውም፡፡ የምርጫ ቦርድ ወይም የማንኛውም የምርጫ ሥራ አካሄድ ተቋም ተግባር ይኸው ነው፡፡

ደጋግመን እንደገለጽነውና አስፈላጊ በሆነ ቁጥርም እየደገምን የምናስረግጠው ኢ – ሕገ መንግሥታዊ የሆነው፣ የዕጩዎችን ብዛት የሚደነግገው የኢትዮጵያ ሕግ የወጣው ድኅረ ምርጫ 97፣ በ1999 ዓ.ም. አይደለም፡፡

ይልቁንም በምርጫ 2002 ሥራ ላይ የዋለው የ1999 የተሻሻለው የምርጫ ሕግ የዕጩዎች ብዛት ድንጋጌ የአዋጅ ቁጥር 438/1997 የአንቀጽ 43 ድንጋጌ የካርቦን ኮፒ ወይም ትክክል ግልባጭ ነው፡፡

በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የሚወዳደሩት የዕጩዎች ብዛት ከአሥራ ሁለት አይበልጥም የተባለውም በዚያው የ97 ምርጫ ጭምር ቢሆንም፣ የአሥራ ሁለት ቁጥር ‹‹ህልውና›› በ85 ዓ.ም. በ87 ዓ.ም. የምርጫ ሕጎች ጭምር ነበር፡፡

በስመ ጥሩና ‹‹በስመ ጥሩ›› ምርጫ 97 ተፈጻሚነት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በጥር ወር 97 አገር ያስተዋወቀው የምርጫ ሕግ አዲስ ነገር ቢኖር በአንድ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመመረጥ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከአሥራ ሁለት መብለጥ የለባቸውም የተባለው ድንጋጌ (በ85፣ በ87ም የነበረው)፣ የክልሎችም የዕጩዎች ብዛት ቁጥር ገደብ የሚመለከት ሕግ ጭምር ይዞ መውጣቱ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ወይም ለሌሎች የምርጫ ደረጃዎች የሚቀርቡ ዕጩዎች ብዛት በቦርዱ ይወሰናል፣ የዕጩዎች ቁጥር ቦርዱ ከወሰነው ቁጥር በላይ የሆነ እንደሆነ ለሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት በተወሰነው መሠረት ይፈጸመል ይላል፡፡ ይህ በ97ም በ99ም በአሁኑ ሕግ ያለ ድንጋጌ ነው፡፡

የመጀመሪያው ቀደም ሲል ያነሳነው ጥልቅ ጥያቄ መጀመሪያ እንዲህ ያለ ሕግ መኖሩ ነው፡፡ ይኑር ከተባለም ደግሞ ይህን ቁጥር የመወሰን ሥልጣን ለቦርዱ መሰጠቱ ነው፡፡ ለየክልሉ ሕግ አውጪ አካል ሳይሆን ለቦርዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ቦርዱ ይህንን ሥልጣን ምን አደረገው ነው? ቦርዱ ይህንን ሥልጣኑን የተወጣውና ቁጥሩን የወሰነው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግ (መመርያ) እንደሚነግረን ከነሐሴ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ አፈጻጸም መመርያ (ቁጥር 1/2001) ነው፡፡

ገደቡ መኖሩ ‹‹አልበቃ›› ብሎ፣ ሥልጣኑ ለቦርዱ መሰጠቱ ሲገርም፣ ቦርዱ ደግሞ ሥልጣኑን የተወጣውና ቁጥሩን የወሰነው ‹‹መመርያ›› በሚባል፣ ሌላው ቀርቶ በነጋሪት ጋዜጣ እንኳን የመታተም ክብር በሌላው የ‹‹ሕግ›› ዓይነት ነው፡፡

የምርጫ ቦርድ መመርያ ይህንን ይላል፡፡ (አንቀጽ 18)

 1. በአንድ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ወይም ለሌሎች የምርጫ ደረጃዎች የሚቀርቡ ዕጩዎች ብዛት ቦርዱ እንደሚወስን በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 6 በደነገገው መሠረት፣

ሀ. ለክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል እስከ 24 ዕጩዎች ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

ለ. ለዞን ምክር ቤት አባላት ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል እስከ 24 ዕጩዎች ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

ሐ. ለወረዳ ምክር ቤት አባላት ምርጫ በአንድ ቀበሌ እስከ 24 ዕጩዎች ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

መ. ለከተማና ለክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባላት ምርጫ በአንድ የከተማ ቀበሌ እስከ 24 ዕጩዎች ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

ሠ. ለቀበሌ ምክር ቤት አባላት ምርጫ በአንድ የቀበሌ ምርጫ ክልል ወይም ጎጥ ወይም መንደር እስከ 100 ዕጩዎች ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

 1. ቦርዱ ከላይ በንዑስ አንቀጽ 3 ከወሰነው ቁጥር በላይ ዕጩዎች የቀረቡ ከሆነ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ)፣ (ለ)፣ (ሐ)፣ (መ) እና (ሠ) መሠረት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ይለያሉ፡፡
 2. ዕጩ ለመለየት የሚወጣው ዕጣ የሚመለከታቸው ዕጩዎች ወይም ተወካዮቻቸው በተገኙበት ይከናወናል፡፡
 3. የምርጫ ክልሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመዝጋቢ ተወዳዳሪዎችን በየምክር ቤቱ የምርጫ ዓይነት ለይተውና ሕጉ በሚያዘው መሠረት የሕዝብ ታዛቢዎች ባሉበት የማጣራቱን ሥራ ያከናውናሉ፡፡ በዚህ በራሱ መሠረት የዕጩዎች ብዛት ገደብ እስከ 24 እስከ 100 ድረስ ከፍ ይላል ማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥርም ሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት የፈለገውን ያህል ከፍ ቢልና ቢበዛ የኢትዮጵያ የምርጫ ክልል ከ550 በላይ በጭራሽ አይሆንም፡፡ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ፣ አሥር ቤት ውስጥ የተወሰኑ፣ ወይም መቶ ቤት ድረስ የበዙና የተትረፈረፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሕዝብ ቁጥርም በመቶ ሚሊዮን ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ከተገመተ ቆይቷል፡፡

በባለ ብዙ ፓርቲ አገር የብዛት ገደቡ በሕግ የማይወሰነው የፓርቲዎች ቁጥር ብቻ አይደለም፡፡ የአንድ የምርጫ ክልል (ኮንስቲትዌንሲ) ዕጩዎች ቁጥርና ብዛትም ጭምር ነው፡፡

የማንኛውም ዜጋ በየራሱ አገር አስተዳደር ውስጥ የመሳተፍ መብት (ለምርጫ ዕጩ ሆኖ የመቅረብ እኩል ዕድልን ጨምሮ) የገዛ ራሱ ትክል የውስጥ ገደብ አለው፡፡ ዜግነት አንዱ ነው፡፡ ዕድሜ ሌላው ነው፡፡ በምርጫ ክልሉ ነዋሪ መሆንም ገደብ ነው፡፡ የአዕምሮ ሁኔታ፣ የወንጀል ድርጊት፣ ሲቪል መብት ማጣት፣ ከአንድ በላይ በሆነ የመራጮች መዝገብ መግባት ከተመራጭነት ውጪ የሚያደርጉ መቆጣጠሪያዎች ናቸው፡፡ ሌሎችም በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡

እነዚህ መቆጣጠሪያዎችንና ቅድመ ሁኔታዎች በልዩ ልዩ ልክና መልካቸው በየአገሩ ሲቀመጡ ‹‹እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይመጣ ግፋው›› እንዳይሆኑ ራሳቸው ጥብቅና ብርቱ ክልከላ አለባቸው፡፡

የአንድ አገር ምርጫ ሥራ አካሄድና አስተዳደር ‹‹ለያዥ ለገራዡ›› ገርና ቀና የሚሆነው የምርጫውን የገዛ ራሱን ተፈጥሮአዊና ባህሪያዊ ትክል ሕግጋት አውቆና ተረድቶ በእነሱ መሠረት ሲረማመዱ እንጂ፣ እንደ ቁጥር ያለ ባዕድ ገደብ በመለጠፍ አይደለም፡፡

የምርጫውን ሥራ አካሄድና አመራር ገርና ቀና ለማድረግ ፉክክርን የፊጥኝ የሚያስር የቁጥር ገደብ ማበጀት፣ ዕጣና ሎተሪን፣ ዕድልንና ገጠመኝን የአንድ አገር ሕግ አካል ማድረግ በእኛ የኢትዮጵያ የአንድ የምርጫ ክልል ሕዝቦች ላይ ‹‹ሌላ አምላክ ማምለክ››፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ላይ ሉዓላዊነታቸውም በሚገለጽበት አሠራር (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8) ላይ መቀለድ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...