በአዲስ አበባ ከየካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሲደራደሩ የቆዩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር፣ ሲጠበቅ የነበረውን ውይይታቸው ባለመስማማት ተጠናቀቀ፡፡
ተደራዳሪዎቹ ያለውጤት ከተበተኑ በኋላ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባወጡት መግለጫ፣ በሁለቱ ወገኖች አለመግባባት የተነሳ በአገሪቱ ከዓመት በላይ በቆየው ቀውስ ‹‹ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ያሳዝናታል›› ሲሉም ተናግረዋል።
ኢጋድ በዚያች አገር ሰላም እንዲሰፈን ያደረገውን ያላሰለሰ ጥረት አንስተው፣ ይህ ጥረቱ ግን የተፈለገውን ውጤት አለማፍራቱን በመግለጫቸው ደጋግመው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሁለቱ ወገኖች ትርጉም አልባው ግጭት እንዲያበቃ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው፣ ከፖለቲካም ሆነ ከሞራል አንፃር ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብና መላው የኢጋድ አካባቢ ከደቡብ ሱዳናውያን ጎን መሆናቸውን ያረጋገጡት አቶ ኃይለ ማርያም በቅርብ ጊዜ ውስጥም ደቡብ ሱዳን ያጣችውን ሰላሟን እንደምታገኝ ተስፋቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)እስከ የካቲት 26 ቀን ድረስ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ድርድር እንዲያጠናቅቁ ቀነ ገደብ አስቀምጦ እንደነበር ይታወሳል።
በመጪው ሐምሌ ወር ሁለቱ ወገኖች የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የገቡትን ስምምነት እንዲያከብሩ ጥረቱ እንደሚቀጥልም፣ አቶ ኃይለ ማርያም በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።