ከ20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ፣ ከአገሪቱ ጠቅላላ የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥ የ22.5 ከመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ አይካ አዲስ፣ ኦያፕ ኢትዮ ኢንዱስትሪ ኤንድ ትሬዲንግ፣ ሳይገን ዲማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ቢኤምኢቲ ኬብልስ እንዲሁም ኤምኤንኤስ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች ከቱርክ ከመጡና በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ በሰፊው እየተሳተፉ ከሚገኙት መካከል የጎመሩት ናቸው፡፡ በዚህም ከቱርክ የሚመነጨው የውጭ ኢንቨስትመንት እዚህ አገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ታዳጊ አገሮች ተርታ ግንባር ቀደም በመሆን እየመራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደሚለው ከሆነ፣ ምንም እንኳ ቻይናውያኑ በኩባንያዎቻቸው ብዛት ከፊት ቢሆኑም፣ ቱርኮች ኢንቨስት ባደረጉት ካፒታል መጠን ቀዳሚ ናቸው፡፡
ስለዚህም ከፍተኛውን የውጭ ኢንቨስትመንትና የካፒታል ድርሻን ቱርኮቹ በመያዛቸው ሳቢያ፣ ለመንግሥት ከወደ አውሮፓ የሚንቆረቆር፣ መስህብ ያለው ሙዚቃ የሆነለት ይመስላል፡፡ በዚያም ላይ ገና ተጀመረ እንጂ ብዙ ርቀት እንደሚጓዝ የሚጠበቀው የቱርኮቹ በብዛት መምጣት፣ ይበልጥ ወደ ጎመራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ኢትዮጵያና ቱርክን እንደሚወስድ ፍንጭ ካሳዩ ክስተቶች መካከል የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን በቅርቡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው አንዱና ትልቁ ነው፡፡
አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነታቸው ወቅት እ.ኤ.አ. በ2009 ቱርክን ጎብኝተው ነበር፡፡ በአገሬው ዘንድ በተለይ በኢስታምቡል ከተማ በግንባታው መስክ ስሙ የገዘፈውን ኩባንያ ባለቤት ካነጋገሩ በኋላ፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ፈገግ ያሰኘ ቀልድ መቀለዳቸው ይነገራል፡፡ ቢያንስ የመግባቢያ ሰነድ ሳይፈርሙ ቱርክን ተሰናብተው እንዳይሄዱ እንደዋዛ ተናግረው ነበር፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍንና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት እኚህን ሰው ደጋግመው አነጋግረዋቸዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ ሰውየው እዚህ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው ሲታወስ፣ በተለይ የወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን ‹‹የኢንቨስትመንቶች ሁሉ እናት›› በማለት ገልጸውት ነበር፡፡ በአገሪቱ በግዙፍነቱ ከተመዘገበው ፕሮጀክት ጀርባ ያሉት እኚህ ሰው ዩሱፍ አኩን ይባላሉ፤ የአኩን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ‹‹ልባችንን አሸነፉት›› በማለት ነበር ለባለሥልጣናቱ ንግግር አጸፋውን የሰጡት፡፡
አኩን ኮንስትራክሽን በቱርክ ትልቁን የኢንቨስትመንት ዞን የሚመራ ኩባንያም ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ስመ ገናና ኩባንያዎች ጋር በሚታወቅበት የኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሁም በዲዛይን ቁሳቁሶች የጠበቀ የንግድ አጋርነት አትርፏል፡፡ ኩባንያው አጋርነቱን ከመሠረተባቸው አገሮች መካከል ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ጣልያንና ደቡብ ኮሪያ ይጠቀሳሉ፡፡ ሚስተር አኩን ኢኪትሊ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ዞን በመባል የሚታወቀው፣ አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተንሰራፋው፣ 37 የኢንዱስትሪ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና 30 ሺሕ የሥራ ማስኬጃ ማዕከላትን ያቀፈው ለዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ዞን ባለቤትና ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ይህ ተቋማቸው በአምራችነቱና በመሠረታቸው የሥራ ቦታዎች ብዛት ከቱርክ ግዙፉ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የበቃ ነው፡፡
ይህንን መሰል የኢንዱስትሪ ማዕከል በኢትዮጵያ የመመሥረት ውጥን ያላቸው አኩን፣ እ.ኤ.አ. በ2009 አኩን ግሩፕ የተባለውን ኩባንያቸውን በመወከል በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ አቅራቢያ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል አንድ መቶ ሔክታር መሬት ለማግኘትም ችለዋል፡፡ የፕሮጀክታቸው ጠቅላላ ወጪ አሥር ቢሊዮን ዶላር ሲገመት ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ ይታሰባል፡፡
ኩባንያው እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን የአፈር ምርመራ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝና በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ግንባታ ሥራ እንደሚገባ የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ማሽነሪዎችና መሣሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እያጓጓዘ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከጅምሩ ግንባታ ይካሄድበታል ተብሎ የታሰበው የለገጣፎ አካባቢ፣ የለገዳዲ ግድብ ውኃ በሚያገኝበት ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ፣ ይህ ችግር በኢትዮ-ቱርክ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ሒደቱን ሊያጓትተው ችሏል፡፡ ለገዳዲ ግድብ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ላላት አዲስ አበባ ግማሽ እጁን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያሟላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ቱርኮች የኢንዱስትሪ ዞኖችን በመገንባትና በማስተዳደር ረገድ ትልቅ ተሰጥዖ እንዳላቸው የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ አውሮፓን ከእስያ ለምታገናኘው አገር ትልቅ የገቢ ምንጭ ከሚያስገኙላት ዘርፎች አንዱም ይኼው ዘርፍ ነው፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት በቱርክ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብር ከፋይ እኛ ነበርን፤›› በማለት ለሪፖርተር የገለጹት የዴሚርሲለር ሳናዪ ሲቲሲ ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ቶፕሱግሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎቹ ለውጭ ገበያ ምርቶቻቸውን በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ከ500 ድርጅቶች መካከል 200 ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ ናቸው፤›› በማለት ኩባንያዎቹ ወጪ ንግድ ተኮር መሆናቸውን ቶፕሱግሉ አስታውቀዋል፡፡
ቱርክ ሁሉን አቀፍ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ማዕቀፍ ውስጥ ካካተተቻቸው መካከል ለምርምርና ሥርፀት እንዲሁም ፈጠራ ተኮር ለሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች የምትሰጣቸው ድጋፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አምራችና ላኪ አገር ለመሆን በማሰብ፣ ቱርክ በቴክኖሎጂ ፓርኮቿ ላይ ተስፋዋን ጥላለች፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቿም ራዕይ ባላቸው የመስኩ ተዋናዮችና ተሰጥዖ ባካበተው የሰው ኃይሏ አማካይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ የቴክኖሎጂ ልማትና በቴክኖሎጂ ፓርኮች ውስጥ የሚካሄዱ የፈጠራ ሥራዎች፣ እ.ኤ.አ. በ2023 ለቱርክ የአሥር ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ሊያስገኙ እንደሚችሉ የቱርክ የሳይንስ፣ ኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ኒሓት ኤርጉን ከሁለት ዓመት በፊት ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹የቴክኖሎጂ ፓርኮችን በእጥፍ በማሳደግ የወጪ ንግዳቸው በአሥር እጥፍ የሚያድግበት ግብ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ ያነሰ ውጤት ከተመዘገበ እንደ ስኬት አይቆጠርም፤›› በማለት ሚኒስትሯ ኒሓት ኤርጉን መናገራቸውም ይታወሳል፡፡ በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ2003 ቱርክ ውስጥ ሁለት ብቻ የነበሩት የቴክኖሎጂ ፓርኮች፣ በአሁኑ ወቅት ከደርዘን በላይ ደርሰዋል፡፡ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ዞን ሳይወድ በግዱ የቴክኖሎጂ ፓርክን ማካተት እንደሚገባው የሚገልጹት ቶፕሱግሉ፣ የትኛውም የኢንዱስትሪ ቀጣና ያለ ቴክኖሎጂ ፓርክ ስኬታማ መሆን እንደማይችልም ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹ከአንድ ዓመት በፊት ከዪልዲዝ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት በማድረግ የቴክኖሎጂ ፓርክ ለመመመሥረት በቅተናል፤›› በማለት የቴክኖሎጂ ፓርኮችን ወሳኝ ሚና ያጠናክራሉ፡፡
በዚህ መሠረት በቴክኖሎጂ ምርምርና ሥርፀት ላይ የሚሠሩ ተቋማት የአሥር ዓመት የታክስ እፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ቶፕሱግሉ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዪልዲዝ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እያካሄደበት የሚገኘው የቴክኖሎጂ ውጤት፣ ሰው አልባ በራሪ አካል ሲሆን መጠሪያም ሔሮን ይሰኛል፡፡ በመካከለኛ ከፍታ፣ ረጅም ጊዜ እየበረረ ለመቆየት የሚችል ሰው አልባ በራሪ አካል መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ቱርክ በርካታ የሔሮን ሥሪቶች ያሏት ሲሆን፣ በቱርክ ዲዛይን የተደረጉና የተፈበረኩ የኤሌክትሮ ኦፕቲካል ንዑስ ሥርዓቶች የተገጠሙላቸው ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የቱርኮቹ ሰው አልባ በራሪ አካላት ASELFLIR-300T የተባሉትንና ከአየር ላይ የሚወሰዱ የምሥልና የዒላማ ማንሻ ሥርዓቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ሔሮንስ በተባሉት ሰው አልባ በራሪ አካላት ላይ ግዝፈት ባለው በASELFLIR-300T መሣሪያ አማካይነት የተጨመረባቸውን ተጨማሪ ጭነት ለመሸከም የሚያስችሉ ጠንካራ ሞተሮችም የተገጠሙላቸው ናቸው፡፡
ከአምስት ሺሕ በላይ መሐንዲሶችና ሳይንቲስቶች በዪልዲዝ የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ እየሠሩ እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ ከ75 ሺሕ ያላነሱ ሰዎችም በተለያዩ የቱርክ ቴክኖሎጂ ፓርኮች ውስጥ በተፈጠሩላቸው የሥራ ዕድሎች የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ዋናው የሥራ መስካቸውም ምርምርና ሥርፀት ነው፡፡
ዪልዲዝ የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ለኤሮስፔስ ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠትም ስሙ የሚነሳ የቴክኖሎጂ ምርምር ተቋም ነው፡፡ ‹‹ለአየር መንገዶች የሚሆኑ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችንና የአውሮፕላን ጥገና የሚረዱ ሶፍት ዌሮችን እናጎለብታለን፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ ገበያ አለን፡፡ ትልልቅ አየር መንገዶች ደንበኞቻችን ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ተቋማት በዓለም ላይ አሥር ብቻ ሲሆኑ በቱርክ ደግሞ አንድ ብቻ ነው ያለው፤›› ሲሉ ቶፕሱግሉ ስለተቋሙ የገበያ ድርሻና ተደራሽነት አስታውቀዋል፡፡
ይህ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አዳዲስ ምሩቃንን ከመመልመል ባሻገር የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠትም ይደግፋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክረምቱ ወራት የተግባር ልምምድ የሚደረጉባቸውን ፕሮግራሞችም ዘርግቷል፡፡ ‹‹ወደ እኛ የሚመጡት ለአንድ ወይም ለሁለት ወራት ለመሥራት ነው፡፡ በቆይታቸው ወቅት ግን ስለኢንዱስትሪው ይማራሉ፡፡ ጥሩ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች ካገኘንም ከምርቃታቸው በኋላ እንቀጥራቸዋለን፤›› በማለት ቶፕሱግሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ያሉትን ተግባራት አኩንና መሰሎቹ ኢትዮጵያ ውስጥም ለማከናወን ከሚያስቧቸው ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግም የኢትዮ-ቱርክ ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ዞን ፕሮጀክትን ከቱርክ ባሻገር፣ በጀርመን፣ በአሜሪካ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በጃፓን እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡ የኢንዱስትሪው ምህዋር ሚስተር አኩን፣ ኩባንያቸው በአፍሪካ ትልቁን የኢንዱስትሪ ዞን ልማት በኢትዮጵያና በቱርክ መንግሥታት ድጋፍ በቅርቡ እንደሚጀምር እርግጠኛ ናቸው፡፡ ሚስተር አኩን በመደምደሚያቸው ላይ ‹‹እኛ የምንፈልገው የመንግሥት ኃላፊዎች ዓለም አቀፍ ዋስትና (ሶቨሪን ጋራንቲ) እንዲሰጡን ሲሆን፣ ይህም ያስፈለገው ሌሎች ተጨማሪ መስኮች እንዳይገጥሙን ለመከላከል እንዲያስችለን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ቱርክ በአሁኑ ወቅት በግዙፍ ኢኮኖሚያቸው ከሚጠቀሱ ትልልቅ አገሮች ዘንድ ትመደባለች፡፡ አገሪቱ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ ከአገር ውስጥ ምርት አኳያ) 1.5 ትሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም ሲአይኤ የዓለምን እውነታዎች (World Fact book) በሚመለከት በሚያትመውና በድረ ገጹ በሚያሠራጨው መረጃ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የቱርክ የወጪ ንግድ ገቢ 167 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያሳያል፡፡ ወደ ውጭ ከሚላኩት ዋና ዋና ምርቶች ውስጥም አልባሳት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብ ምርቶች፣ ማሽነሪዎችና የትራንስፖርት ቁሳቁሶች ይጠቀሳሉ፡፡