በኢትዮጵያ ትልቁን የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ የኢንዱስትሪ መንደሩ እውን ሲሆን፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በጫማ ማምረትና በቆዳ ውጤቶች፣ በምግብ ምርቶችና በግብርና ማቀነባበር መስኮች፣ ከዚያም በላይ በመድኃኒትና በኬሚካል አምራችነት፣ በማሽነሪዎችና በብርታ ብረት፣ በፕላስቲክና በጎማ ውጤቶች ላይ የሚሰማራ ግዙፍ አምራች ኢንዱስትሪ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህ ብቻ ግን አይወሰንም፡፡ የኮንስትራክሽንና የሕንፃ ግንባታ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክስ፣ የመስታወት፣ የዕደ ጥበባት፣ የመጋዘንና የሎጂስቲክስ መስኮችም በኢንዱስትሪ መንደሩ የሚካተቱ ናቸው፡፡ አለፍ ሲልም የትምህርት፣ የጤና፣ የላቦራቶር እንዲሁም የቴክኖ ፓርክ መስኮች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችም ይታሰባሉ፡፡ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ሆስፒታል፣ የገበያ ማዕከልና የንግድ ዓውደ ርዕይና ሌሎችም በኢንዱስትሪ ዞን ማስተር ፕላን ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ የባህል ማዕከልና ፕላዛ የኢንዱስትሪ ተዋናዮችን ለማስተናገድ ታስቦባቸዋል፡፡ በአውሮፓ ኮንስትራክሽን መስክ ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ዩሱፍ አኩን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ፕሮጀክታቸውን እዚህ ለመጀመር በሚችሉበት መንገድ ላይ እየተነጋገሩ ይገኛሉ፡፡ ንግግሩም ፕሮጀክታቸው በለገዳዲ ግድብ የውኃ ማጣሪያ ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚል ታግዶ ስለሚገኝ ነው፡፡ አማረ አረጋዊ በቱርክ ኢስታምቡል በነበረው ቆይታ የኢንዱስትሪ መንደሩ ምን ይዞ እንደመጣና ፕሮጀክቱን ለማስጀመር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ዩሱፍ አኩንን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ከተማ ግንባታ ላይ ከመሰማራትዎ በፊት በምን ሥራ ላይ እንደነበሩ ቢገልጹልኝ?
ዩሱፍ አኩን፡- በንግድና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የጠለቀ ተሳትፎ አለኝ፡፡ ኢኪቴሊ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ዞን ባለቤት ነኝ፡፡ ይህ ተቋም ላለፉት 45 ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኝ የቆየ ተቋም ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለዓመታት ስንሠራ ቆይተናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ገደማ ፒቪሲና ሌሎች የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን በማምረት ነበር የጀመርነው፡፡ ከዚህ በመነሳት እ.ኤ.አ. በ1963 ኢኪቴሊ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ መንደርን ለመመሥረት ወጠንኩ፡፡ ሲመሠረትም የቀድሞ የኢስታንቡል ከተማ ከንቲባ ትልቅ ስኬት እንደሆነ አረጋግጠው ነበር፡፡ ሁሉንም አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ከከተማ አውጥተናቸው ነበር፡፡ ሐሳቡ 15 የኢንዱስትሪ ተቋማትን ማቋቋም ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ከሁሉም ትልቁ የሆነው ግን ኢኪቴሊ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ዞን ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢስኮ ለተሰኘው ኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር ስሆን ኃላፊነቴም በላይኛው ማኔጅመንትና በከፍተኛው የአመራር መዋቅር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በኢስኮ ኅብረት ሥር 27 ያህል የኢንዱስትሪ ዞኖች ሲኖሩ መሥራችና ሊቀመንበር በሆንኩበት ዩኒየን ሥር የሚታቀፉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ቱርክ ምን ያህል ኢንዱስትሪዎች አሏት?
ዩሱፍ አኩን፡- በየመንደሩ ከሚገኙት በርካታ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባሻገር 218 አንዱስትሪ ተቋማት በቱርክ ይገኛሉ፡፡ ስም መጥቀስ ባልፈልግም ሱፐር ማርኬት ውስጥ የምታገኘው እዚሁ ቱርክ የተመረተ ዕቃ ነው፡፡ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጫማ፣ ብርታ ብረት፣ አውቶሞቢል፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ፕላስቲክ ወዘተ. ያሉት ምርቶች እዚህ የሚመረቱ ናቸው፡፡ እንደ መስታወት፣ ፕላስቲክና ብረታ ብረት ያሉት ምርቶች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ መልሰን (recycled products) እናመርታቸዋል፡፡ የማሸጊያ ምርቶች በማምረት ግንባር ቀደም ነን፡፡ በዚህ መስክ ፊተኛው ረድፍ ላይ ከሚገኙ አገሮች ተርታ እንመደባለን፡፡ አሁን የምንጨነቀው ኤክስፖርት ስለማድረግ እንጂ ከውጭ ስለማስገባት አይደለም፡፡ የማሸጊያ ምርቶች ዘርፍ በየዓመቱ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በቱርክ አንድ አባባል አለ፤ ‹‹ፈረሶች አንገት ላንገት ተያይዘው እንዲጋልቡ አድርግ›› የሚል ነው፡፡ ልክ እንደ ፈረሶቹ ሁሉ ኢንዱስትሪ፣ ግብርናና የእንስሳት እርባታ አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ አንድ አገር ከዚህ መርህ ውጭ ሆና ማደግ አትችልም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢንዱስትሪዎቻችሁ ምን ያህል ሰዎች ተቀጥረው ይሠራሉ?
ዩሱፍ አኩን፡- ኢኪቴሊ ኢንዱስትሪ ዞን በአንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለና ከልዩ ልዩ መስኮች የተውጣጡ 37 የኢንዱስትሪ ቀጣናዎችን ያቀፉ ኅብረት ሥራዎችና 30 ሺሕ ኢንተርፕራዞችን ያካተተ ዞን ነው፡፡ ከ350 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማሉ፡፡ በኢንዱስትሪ መንደሮች ውስጥ የሚያልፍ የምድር በታች የባቡር ትራንስፖርት ባይኖረንም የኢንዱስትሪ ዞኑ ግን ከቱርክ የባቡርና የኤርፖርት ሥርዓት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ለአገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ ለማበርከት እየጣርን ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር የአጋርነት ፕሮግራሞች አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- በሚያስፈልጓችሁ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የመንግሥት እገዛ ምን ይመስላል?
ዩሱፍ አኩን፡- በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ቦታ አመቻችቷል፡፡ መዘጋጃ ቤትም ሆነ መንግሥት መሬት፣ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አቅርበዋል፡፡ ትኩረት ልሰጥበት የምፈልገው ነገር ቢኖር የየትኛውም መንግሥት መዋቅር ወይም ፓርቲ አባል መሆን ይህንን ፕሮጀክት ከመደገፍ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ ሚኒስቴሮቹም ሆኑ መንግሥት ይለወጣሉ፣ የትኞቹም ግን ይህንን ፕሮጀክት አይቃወሙትም፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት መሬቱን ቢያቀርብም፣ ለዚያ ላቀረቡት መሬት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ግድ አይሉም፡፡ ሁሉም ኢንዱስትሪዎች የራሳቸው ማጣሪያ ስላላቸው አካባቢ ላይ ጉዳት አያስከትሉም፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ያሉ አገሮች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1995 የተፅዕኖ ግምገማውን መተግበር ጀምረናል፡፡ የእነዚህ ያደጉ አገሮችን ፖለቲካ ከተመለከትክ፣ የሚፈልጉትን ልማት ካሳኩ በኋላ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው አይጠይቁም፡፡ ሆኖም በታዳጊ አገሮች ላይ እንደ ማገጃ ድንበር ዓይነት አድርገው ግን ይጠቀሙበታል፡፡
ሪፖርተር፡- 37 ኢንዱስትሪዎችንና በርካታ ኢንተርፕራይዞችን የሚያስተዳድር ተቋም ፈቃድ እንዲህ በቀላሉ ለማግኘት ይቻለዋል?
ዩሱፍ አኩን፡- የፈቃድ ጉዳዮችን የሚከታተል ሌላ ክፍል አለ፡፡ ይህ ክፍል ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ በመሆኑም የማዘጋጃ ቤት ዓይነት ሥራ እንሠራለን፡፡ የቱርክ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈቃድ እንድንሰጥ የሚያስችለንን ሕጋዊ ሰውነት ሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም እኛም በፊናችን የኮንስትራክሽንና የኦፕሬሽን ፈቃዶችን እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮምና መሰል መሠረተ ልማቶችን እናቀርባለን፡፡ የዚህ ክፍል ሊቀመንበር በመሆን ለሃያ ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ላይ ለመስጠት የሚያስችል ተቋም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በርካት መንገዶች፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓቶችና የውኃ ማሠራጫ መስመሮች በኢንዱስትሪ መንደሩ ውስጥ ይታያሉ፡፡ ማን ነው የገነባቸው?
ዩሱፍ አኩን፡- በየኢንዱስትሪ ቀጣናው የሚገኙ ሁሉም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግንባታዎች አሏቸው፡፡ መንግሥት ለማኅበራቱ መሬት ያቀርባል፤ ግንባታው ግን በማኅበራቱ አባላት በኩል ይካሄዳል፡፡ መንገድና ሌሎች ከዋናው የኢንዱስትሪ ቀጣና ውጭ ያሉ መሠረተ ልማቶችን የሚገነባው መንግሥት ነው፡፡ ለሁሉም ኢንተርፕራይዝ ፈቃድ አላቸው፡፡ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከኢንተርፕራይዞቹ አቅም አኳያ በማስላት የሚፈልጓቸውን የግንባታ ዓይነቶች በሚያቀርቡት ገንዘብ መጠን እናካሂዳለን፡፡ ከዚህ በኋላ ንብረቱ የአባላቱ ስለሚሆን ማከራየትና መሸጥ ቢፈልጉ መብታቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሰው ሀብት ምንጫችሁ ምንድን ነው? የቴክኒክ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች አሏችሁ?
ዩሱፍ አኩን፡- ቴክኖ ፓርክ የሚባሉትን ተቋማት የመገንባቱ ሐሳብ ከጅምሩ መነሻው አዲስ ነገር ለመፍጠር ነው፡፡ የሚፈጠረው ነገር ቁሳዊ ወይም ሐሳባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ መንግሥት በዚህ ረገድ ጥሩ አካሄድ አለው፡፡ ከቴክኖ ፓርክ ተቋማት መንግሥት ታክስ አይሰበስብም፡፡ እነዚህ ተቋማት ልክ እንደ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ለኢንተርፕራይዞቹ የልምድ ማካበቻዎችና የቴክኖ ፓርኮቹ ማሻሻያ መንገዶች ለማሳየት የሚረዱ ማኅበራቱንና ዩኒቨርሲቲዎችም ስላሉ ተማሪዎች ሊጎበኟቸው ይችላሉ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ቴክኖ ፓርኮች የምርምር ውጤቶችን ያሰርጻሉ ማለት ነው?
ዩሱፍ አኩን፡- በመሠረቱ የምርምርና የልማት ቦታዎች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችም ተዋውቀዋል፡፡ በርካታ የኤሌክትሮኒክ ውጤቶችም ወደ ኢንተርፕራይዞቹ ተላልፈዋል፡፡ የእኛ ቴክኖ ፓርክ ለቱርክ አየር መንገዶች የጥገና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሰው አልባ በራሪ አካላትንም ሳያበረክት አልቀረም፡፡
ሪፖርተር፡- ለታዳጊ አገሮች ቴክኖሎጂዎቻችሁን ትሸጣላችሁ?
ዩሱፍ አኩን፡- ጥራት ያላቸውን ምርቶች እናመርታለን፡፡ እንደ ፈረንሳይና ጀርመን ላሉ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ከ60 እስከ 70 ከመቶ የሚሆኑት ምርቶች ይላካሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ምርት ጀርመን ትገዛለች፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቱርክ በቴክኖሎጂ የተራቀቀች አገር ናት እያሉኝ ነው ማለት ነው?
ዩሱፍ አኩን፡- በአሁኑ ወቅት ቱርክ የራሷን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኤክስፖርት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት ይኼንን ማሰብ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ በራሳችን ይህንን ለማድረግም ከባድ ነበር፡፡ አሁን ግን ለኤክስፖርት የሚሆኑ ሁሉንም ዓይነት ማሽነሪዎች እናመርታለን፡፡ መልካም የሚባሉ የግብርናና የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎችም አሉን፡፡ ኩባንያችን 1,800 ያህል የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማቴሪያሎች አሉት፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት አቅዳችኋል፡፡ እንዴት እየሄደ ነው?
ዩሱፍ አኩን፡- ስለዚህ ከመነጋገራችን በፊት አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን መገንባት በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ከተማዋን ከብክለት ከመታደግ ባሻገር፣ ለሰዎች ኑሮ ተስማሚ አካባቢ እንዲኖር ይረዳል፡፡ ስለዚህ ጠቃሚ ነገር መጠቆም እችላለሁ፡፡ አነስተኛና መካከለኛ መጠን ያላቸው ኢንተርፕራይዞች አሉን፡፡ አነስተኞቹ መካከለኛ፣ መካከለኞቹም ከፍተኛ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ መንግሥትም የኢንዱስትሪ ዞን ተቋማትን ይደግፋል፡፡ 60 ከመቶ በላይ የቱርክ ኢንዱስትሪዎች የተነሱት ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቱርክ የኢንዱስትሪ ዞን በመኖሩ ምክንያት የኑሮ ደረጃ መሻሻል አሳይቷል ማለት ይቻላል፡፡ ክሊኒኮች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች በከተማው ዙሪያ ተስፋፍተዋል?
ዩሱፍ አኩን፡- ይኼ ተግባር ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚያስገኝ ነው፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በኢንተርፕራይዙ ውስጥ ስለሠራ የምግብ ባለሙያ ብናስብ፣ አሁን ላይ የራሱን ድርጅት መክፈት የሚፈልግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ኢንተርፕራይዞች ልክ እንደ ትምህርት ቤት ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት ስለሚፈልጉት ኢንዱስትሪ ዞን ምን ያስባሉ?
ዩሱፍ አኩን፡- ቱርክ ሕዳር 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ትልቅ ጉባዔ አስተናግዳ ነበር፡፡ እርግጥ ይህ ጉባዔ በኢንዱስትሪ ዞን አባላት ዘንድ መካሄዱ የተለመደ ነገር ነው፡፡ በወቅቱ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አባዱላ ገመዳ በእንግድነት ከተገኙት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ለአሥር ቀናት በነበራቸው የቱርክ ቆይታ በኢንዱስትሪ ዞኑ ያለውን ነገር በሙሉ አስጎብኝተናቸው ነበር፡፡ የቀድሞው በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የአሁኑ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ዞን እንዳቋቁም ጠይቀውኝ ነበር፡፡ ካልተስማማን በቀር ከቱርክ ወደ አገራቸው እንደማይመለሱ ሁለቱም ተናግረው ነበር፡፡ በመሆኑም ስምምነት አደረግን፡፡ እርግጥ ያንን ቅድመ ስምምነት ፈረምኩ እንጂ እውን ይሆናል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር፡፡ ሆኖም ከስድስት ወራት በኋላ ግን ወደ ኢትዮጵያ በማምራት አቶ አባዱላን በጽሕፈት ቤታቸው አነጋገርኳቸው፡፡ መሬት እንዴት ማግኘት እንደሚገባን አቅጣጫውን አሳዩን፡፡ መሬትም ተከለልን፡፡ የአዲስ አበባ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ጣቢያ በተሰጠን መሬት አቅራቢያ እንደሚገኝ ግን አናውቅም ነበር፡፡ በመሆኑም ድርድሩ አንድ ዓመት ያህል ሲፈጅ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለግንባታ የምናውለው 30 ከመቶ ገንዘብ እንዲለቀቅልን ተስማምተው ነበር፡፡ በየካቲት 2004 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋብዘውን መንግሥታቸው የፕሮጀክቱ አካል እንደማይሆን አረጋግጠውልን ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም. ማብቂያ ገደማ ግን የኢንዱስትሪ ዞን ከመገንባት ሥራችንን የሚገታን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መጣ፡፡ የኢስታንቡል ዩኒቨርሲቲ ያጠናውን የተፅዕኖ ግምገማ ጥናት የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ውድቅ አደረገው፡፡ መሬቱ ሲሰጥም ከከተማው የውኃ ማጠራቀሚያ አቅራቢያ ላይ መሆኑን አልተገነዘበም ነበር፡፡ መሬቱ የመረጠበት አካባቢ ጥሩ አለመሆኑን ከመረዳታችንም ባሻገር ወደፊት በኢንዱስትሪ ባለቤቶች ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አውቀናል፡፡ በአዲስ አበባ ፕሮጀክቱን ለመተግበር እንደማይቻል በመግለጽ መንግሥት አማራጭ መሬቶችን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንድንፈልግ አማራጭ ቢያቀርብም ሳንቀበለው ቀርተናል፡፡ ከአዲስ አበባ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ቦታ እንዲሰጡን ነግረናቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምላሻቸውን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ በ30ም ሆነ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቦታ ብታገኙ ሥራችሁን ለመቀጠል ዝግጁ ናችሁ?
ዩሱፍ አኩን፡- በዚህ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ለመካተት የተስማሙ 120 ድርጅቶች ነበሩን፡፡ መጀመሪያ ላይ ሦስት የአሜሪካ ኩባንያዎች የነበሩ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ ታንዛንያ አምርተዋል፡፡ መሬቱን የሚሰጡን ከሆነ እኛ ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ ሆኖም በተፈጠረው ችግር ጊዜያችንንና ገንዘባችንን አጥፍተናል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠርም ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ዋስትና እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አካል የሚሆኑ ሌሎች የቱርክ ድርጅቶችንም እንድናካትት ጠይቀውናል፡፡ ኢንዱስትሪ ዞን የማቋቋም ዋናው ተግባር ድርጅቶች እንዲመጡ ማድረግ በመሆኑ መንግሥት በዚህ ረገድ ድጋፉን መስጠት ይኖርበታል፡፡ እስካሁን በርካታ ድጋፎችን አድርገዋል፤ የሚሉንን ለመስማትም እየተጠባበቅን ነው፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ዞን እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመሥራት ከምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ በጣም ጠቃሚው ነገር ነው፡፡