Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በዓባይ ጉዳይ ረቂቅ ፖለቲካዊ መግባባት ላይ ደረሱ

ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በዓባይ ጉዳይ ረቂቅ ፖለቲካዊ መግባባት ላይ ደረሱ

ቀን:

በሱዳን ካርቱም  ለአራት ቀናት ሲመክሩ የቆዩት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውኃ ሀብት ሚኒስትሮች በዓባይ ወንዝ ላይ ከመግባባት ሊያደርሳቸው የሚችል ፖለቲካዊ ረቂቅ ሰነድ ላይ ተስማሙ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር ማኅበራዊ ገጻቸው የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ሦስቱ አገሮች ፖለቲካዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸው ረቂቅ ሰነድ ላይ መስማማታቸውን በተመለከተ፣ ለሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል፡፡

የሱዳንና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ በካርቱም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም እንዲሁም ሦስቱ አገሮች ስለሚተባበሩባቸው ዝርዝር ጉዳዮች የሚመለከተው ረቂቅ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ረቂቅ ስምምነትን ሦስቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለመሪዎቻቸው አቅርበው የሚፀድቅ ከሆነ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሳም አልሞጋሃዚ ረቂቅ ስምምነቱ የሚፀድቅ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ትብብር ማድረግ የሚቻልበትን የሚገዛ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የተደረሰው ስምምነት ቴክኒካዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ይዘቱ የተዘጋጀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሦስት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የግብፅና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዝግ ባደረጉት ስብሰባ፣ በግብፅ በኩል ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ድርሻ እንደማትጎዳ ግድቡንም ለመስኖ ልማት እንደማታውለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚቀበለው ሰነድ እንድትፈርም ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል ሙሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ ላይ ፖለቲካዊ ትብብር ማድረግ የሚያስችላቸውን የፖለቲካዊ ሰነድ ኢትዮጵያ አርቅቃ ለውይይት እንደምታቀርብ ቃል ተገብቶ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በፖለቲካዊ ረቂቅ ሰነዱ ውይይት ተደርጐበት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሦስቱ አገሮች የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ በህዳሴው ግድብ ላይ ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ አጥኚዎች፣ የቀረቡ ሁለት ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጥኚዎችን ለመምረጥ በካርቱም በውይይት ላይ ናቸው፡፡

ከቀረቡት አራት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ሁለት ወይም አንድ ኩባንያ በመምረጥ በቅርቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...