የቅድመ ሰው አመጣጥ ታሪክን በመጠኑ የሚቀይር የታችኛው መንጋጋ ክፍል ቅሪት በአፋር ክልል ሌዲ ጉራሩ አካባቢ መገኘቱ ይፋ ሆነ፡፡
ዓለም አቀፉ የሳይንቲስቶች ቡድን በአፋር ክልል ፍለጋውን ማድረግ ከጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የታችኛው መንጋጋ ቅሪተ አካል ከነጥርሱ የቡድኑ አባል በሆነው በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርቱን እየተከታተለ በሚገኘው ኢትዮጵያዊ አቶ ቻላቸው ሥዩም መገኘቱን፣ የቡድኑ መሪ የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቷ ዶ/ር ኬይ ሪድ የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡
የቅድመ ሰው አመጣጥ ጥናት ሳይንስ (ፔሌአንትሮፖሎጂ) በርካታ የቀደምት የሰው ዘር ባህርያትና ዓይነት በየወቅቱ በሚገኙ ግኝቶች አማካይነት ሳይንሳዊ ግኝቶችን ሲመልስ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ የጥናት ዘርፍ ያልተመለሱ በርካታ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥያቄዎችን መመለስ አዳጋች እንደሆነ የተመራማሪ ቡድኑ መሪ ዶ/ር ኬይ ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህም ሳይንሳዊ ጥያቄዎች መካከል የቅድመ ሰው ልጅ አመጣጥ ሐረግ የመጨረሻው ቅርንጫፍ ሆሞ ሃቢሊስ ሲሆን፣ ከ2.3 ሚሊዮን ዓመት በፊት በምድር ይኖር እንደነበርና የዘር ሐረጉም ከሉሲና ከሌሎች አውስትራሎፒተከስ ዝርያዎች እንደሆነ በጥናት የተረጋገጠ ነበር፡፡
የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያዎች ይኖሩበት በነበረ ሦስት ሚሊዮን ዓመትና የሆሞሃቢሊስና ሌሎች የሆሞሳፒያንስ ዝርያዎች ይኖሩ ነበር ተብሎ በተገመተበት 2.3 ሚሊዮን ዓመት መካከል፣ ምን ዓይነት የቅድመ ሰው ዘር ነበር የሚለውን የሚመልስ ቅሪት አለመኖሩን የጥናት ቡድኑ መሪ ዶ/ር ኬይ ተናግረዋል፡፡
በአፋር የተገኘው የታችኛው አገጭ አካል ቅሪት ግን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ፍንጭ ከመስጠቱም ባሻገር፣ አሁን ባለው ሳይንሳዊ ድምዳሜ ሆሞሃቢሊስ የጥንታዊ ሰው ዘር የመጨረሻ ሐረግ መሆኑ ቀርቶ፣ ሆሞሃቢሊስ ዝርያዎች ይኖሩ ከነበረበት 2.3 ሚሊዮን ዓመት፣ ከ400 ሺሕ ዓመት በፊት የተሻለ ለሰው ዘር ቅርብ የሆነ ቅድመ ሰው ዘር መኖሩን ያረጋገጠ መሆኑንም ዶ/ር ኬይ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ግኝቱ በአውስራሎፒቲከስና በሆሞ መካከል የነበረውን ክፍተት የሞላ ነው ተብሎለታል፡፡ በቅሪተ አካሉ ላይ የተገኙ ባህርያዊ መረጃዎች ማለትም የጥርሶቹ ቅርጾች፣ አወቃቀርና የመሳሰሉት ከሉሲና ከሆሞሀቢሊስ ባህርያት የሁለቱንም የያዘ መሆኑን ዶ/ር ኬይ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የተገኘው ቅሪት በሆሞ ዝርያዎች መካከል እንዲካተት አስችሎታል፡፡
የአውስትራሎፒቲከስና የሆሞ ዝርያዎች ይኖሩበት በነበረ ዕድሜ መካከል ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ተከስቶ እንደነበርና ይህም በሁለቱ መካከል ምንም ዓይነት ቅሪተ አካል ግኝቶች እንዳይገኙ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል፣ በተጨማሪም ይኼው የአየር ንብረት ለውጥ ለሆሞሳፒያንስና ሌሎች የሆሞ ዝርያዎች መፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ተመራማሪዎቹ የተገኘው የታችኛው አገጭ ቅሪትን ምሉዕ የሚያደርግ ቅሪት ለማግኘት የምርምር ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለቅድመ ሰው አመጣጥ ምርምር ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን የገለጹት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፣ የዚህ አዲስ ግኝት የላብራቶሪ ምርምር ሙሉ በሙሉ የተካሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሉሲ ቅሪት ከተገኘ በኋላ አምስት ዓመት በውጭ ላብራቶሪ ምርምር መካሄዱን የገለጹት አቶ ዮናስ፣ መንግሥት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ በኢትዮጵያ በመገንባቱ ሳይንቲስቶች ምርምራቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ተረጋግተው እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡