Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናማረሚያቤቶች አስተዳደር በሴት ጦማሪያን የቀረበበትን አቤቱታ የሚያስተባብል ምላሽ ሰጠ

ማረሚያቤቶች አስተዳደር በሴት ጦማሪያን የቀረበበትን አቤቱታ የሚያስተባብል ምላሽ ሰጠ

ቀን:

‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 በተደነገገው መሠረት እየተስተናገዱ ነው›› የሴት ታራሚዎች ጥበቃና ደኅንነት ዘርፍ አስተዳዳሪ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች መካከል ጣማሪና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪ ማኅሌት ፋንታሁን፣ በእስር ላይ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት የአያያዝ ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ላቀረቡት አቤቱታ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. አቤቱታውን የሚያስተባብል ምላሽ ሰጠ፡፡

በማረሚያ ቤቱ የሴቶች ጥበቃና ደኅንነት ዘርፍ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የተጠርጣሪዎቹን የክስ ጉዳይ እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያስረዱት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ቤተእግዜር ገብረሚካኤል፣ ተጠርጣሪዎቹ እንደማንኛውም ታራሚ ሁሉም ነገር እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21፣ ማለትም ‹‹በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡ ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸው ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፤›› የሚለውን ድንጋጌ በመከተል፣ ለሁሉም ጥበቃ ለሚደረግላቸውና ታራሚዎች እንደሚያደርጉት ለሁለቱ ተጠርጣሪ ሴት ጦማሪያን እያደረጉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት አቤቱታውን አስተባብለዋል፡፡

የተርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ማረሚያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ላይ አስተያየታቸውን ተጠይቀው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኞቻቸው በተደጋጋሚ እንደነገሯቸው ከደካማ እናትና አባታቸው በስተቀር ሌላ ሰው እንዳይጠይቃቸው ተከልክለዋል፡፡ እነሱም ቢሆኑ ለአጭር ደቂቃ ብቻ ዓይተዋቸው እንዲሄዱና የሌሎች ታራሚ ቤተሰቦች በማይመጡበት ጊዜ (ሰዓት) እንዲመጡ መደረጉ፣ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን መተላለፍ መሆኑን እንደገለጹለቸው ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል፡፡

ጠበቃ አመሐ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ የጦማሪያኑን አቤቱታ ማሰማታቸውንና የማረሚያ ቤቱ ተወካዮች፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ችግሩ እንዳለ እንደማያውቁና እንደሚያስተካክሉ ቃል ገብተው እንደነበር አስታውሰው፣ እሳቸው ማረሚያ ቤት ድረስ ሄደው ከኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ባደረጉት ውይይትም ስምምነት ላይ ደርሰው ተጠርጣሪዎቹ የፈለጉትን ያህል ጠያቂ መዝግበው እንዲሰጧቸው እንደሚያደርጉ ቃል ተገባብተው የተለያዩ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ለውጥ አለመታየቱን ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የጠያቂዎቻቸውን የስም ዝርዝር ከሰጡት ውስጥ አሥር ጠያቂዎች ወደ ማረሚያ ቤቱ የሄዱ ቢሆንም ተከልክለው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ማረሚያ ቤቱ በጥቅሉ ‹‹እየተጎበኙ ነው›› ቢልም፣ እነሱም ‹‹አልተጎበኘንም›› የሚል ጥቅል ምላሽ አለመስጠታቸውን የገለጹት ጠበቃ አመሐ፣ የሚጠየቁት በእናትና በአባታቸው ብቻ በመሆኑ፣ እንደሌሎቹ ታራሚዎች በአግባቡና በሕገ መንግሥቱ በተፈቀደው መሠረት ሌሎች ዘመዶቻቸው፣ የሃይማኖት አባቶችና የቅርብ ጓደኞቻቸው እንዲጠይቋቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ቤተእግዜርን ‹‹በማረሚያ ቤቱ ተደጋጋሚ የአያያዝ ችግር እንዳለ አቤቱታና ቅሬታ እየቀረበ ነው፡፡ ኃላፊዎች ተነጋግራችሁ ለምን አትፈቱትም?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ አስተዳዳሪዋ በሰጡት ምላሽ፣ የተጠርጣሪዎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የማረሚያ ቤቱ መሆኑን ጠቁመው፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየተጎበኙ መሆናቸውን፣ የተደረገባቸው ጫና እንደሌለና የተከለከለ ጎብኚ አለመኖሩን በመናገር አስተባብለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቃቸው አማካይነት በተደጋጋሚ ባቀረቡት አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...