Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አላና ፖታሽ ከያራ ጋር እየተደራደረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የነበረው ስምምነት ሳይቋረጥ እንዳልቀረ እየተነገረ ነው

ምርት የሚጀምርበት ጊዜ ተራዝሟል

ተቀማጭነቱን በካናዳ ቶሮንቶ ያደረገው አላና ፖታሽ፣ በኢትዮጵያ ለማምረት ያቀደውን የፖታሽ ምርት ከሌሎች አዳዲስ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ለማምረት እየተደራደረ ነው፡፡ በቅርቡ ከእስራኤሉ ኩባንያ አይሲኤል ጋር በጋራ ለመሥራት ያደረገው ስምምነት ግን ሳይስተጓጎል እንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡

ከአላና ፖታሽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኩባንያው ከሦስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በድርድር ሒደት ላይ ነው፡፡ በዋናነት ግን ከኖርዌይ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ያራ ኢንተርናሽናል ጋር ስምምነት ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአላና ፖታሽን አዳዲስ ድርድሮች በተመለከተ የተሰራጩ መረጃዎችም እንደሚያመለክቱት፣ ያራ ኢንተርናሽናል ከሌሎች ኩባንያዎች በተለየ ከአላና ፖታሽ ጋር በጥምረት ሊሠራ እንደሚችል ነው፡፡ የሁለቱም ኩባንያዎች ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ አካባቢ የሚገኙ ከመሆኑም በላይ፣ በጋራ የአካባቢውን መሠረተ ልማት፣ የጂቡቲን ወደብና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ስለሆነ ወደ ስምምነት ለመድረስ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

አላና በኢትዮጵያ የፖታሽ ማዕድን አምርቶ በዓለም ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ ዕቅዱን ከዳር ለማድረስ ከሌላ ኩባንያ ጋር በጥምረት መሥራትን እንደ አማራጭ እየተመለከተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አላና ፖታሽ በቅድሚያ ለማምረት ያቀደው ሙሪዮት የተባለውን የፖታሽ ምርት ቢሆንም፣ በዓለም ገበያ በጣም ተፈላጊው የአቅርቦት እጥረት የሚታይበትና በዋጋም ውድ የሆነው ሰልፌት የተባለው የፖታሽ ማዕድን እየሆነ በመምጣቱ አላና ፊቱን ወደ ተፈላጊው ምርት እያዞረ ነው ተብሏል፡፡

የአላና ፖታሽ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፋርሃድ አባሶቭ ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ፖታሽ ለማምረት በሽርክና ወይም የፋይናንስ ድጋፍ ከሚያደርጉ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በጥምረት በመሥራት በሳምንታት ውስጥ ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡

በዚህም መሠረት ከያራ ኢንተርናሽናል ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችለው ድርድር ከተሳካ፣ በተለይ ሰልፌት ፖታሽ ለማምረት አሁን ያለውን መዋቅር ማሻሻል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቱም ወደ 787 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ብለዋል፡፡

ያራ ኢንተርናሽናል ባለፈው ወር በዓመት 600 ሺሕ ቶን የሰልፌት ፖታሽ ምርት በኢትዮጵያ ለማምረት እንደሚችል ይፋ ያደረገ ቢሆንም፣ ይህ ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ የሚደርስ እንዳልሆነ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

አላና ሙርየት ፖታሽን ለማምረት የሚያስችለው የፋይናንስ ድጋፍ ካገኘ የማምረቻ ፋብሪካውን ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2015 አጋማሽ መጀመር ይፈልጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 ደግሞ ምርቱን ለገበያ የማቅረብ ውጥን ይዟል፡፡ ሰልፌት ፖታሽን ደግሞ በቀጣይ ለማምረት ነው ያሰበው፡፡ ቀደም ብሎ በአላና ታቅዶ የነበረው የማምረቻውን ተከላ በማጠናቀቅ እ.ኤ.አ. በ2016 ምርቱን ለመጀመር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምርት የሚጀምርበት ጊዜ እ.ኤ.አ. ወደ 2018 ለመራዘሙ ዋናው ምክንያት፣ ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ (አይሲኤል) ከተባለ ግዙፍ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመሥራት የተደረሰው ስምምነት ሊሳካ ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው እየተባለ ነው፡፡

የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገልጹት ግን፣ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ እንደተባለው እንዳልከሰመ ነው፡፡ ሆኖም ሰሞናዊው የአላና ፖታሽ እንቅስቃሴና ከአዳዲስ ኩባንያዎች ጋር ለመጣመር እያደረገ ያለው ድርድር፣ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የነበረው ውል በመቋረጡ ነው የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ግን ‹‹የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ ሥራችንን እየሠራን ነው፡፡ ውሉ ቢቋረጥ ይህንን የመግለጽ ኃላፊነት አለብን፤›› በማለት አስተባብለዋል፡፡

የአላና ፖታሽ ኃላፊዎች ሰሞኑን ለሮይተርስ ‹‹በጣም ፈጥነን መጓዝ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ አላና ሙርየት ፖታሽን በጥምረት ከእስራኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ ጋር በማካሄድ ባለፈው ዓመት የመግባቢያ ሰንድ ተፈራርሞ እንደነበርም ዘገባው ያስታውሳል፡፡

አላና በቅድሚያ ለማምረት የሚፈልገውን ሙርየት ፖታሽ በገበያ ላይ የውድድር ጫና ሊፈጥሩበት የሚችሉ አዳዲስ ኩባንያዎች ወደ ማምረት ገብተዋል፡፡ ለዚህም ኩባንያው ሰልፌት ፖታሽ ቢያመርት አዋጪ መሆኑን ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡

ይህ የአላና ሰሞናዊ መረጃ ፕሮጀክቱን አካሄድ እየቀየረው ነው፡፡ የአላና ፖታሽ በቶሮንቶ በአክሲዮን ገበያ ያለው ዋጋ በ2.6 ከመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን፣ ይህም አላና አዳዲስ አማራጮችን እንዲያይ እያስገደደው ነው፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት አላና ፖታሽ ከእስራኤሉ ኬሚካል ኩባንያ ጋር አድርጎት የነበረው ስምምነት በመፍረሱ፣ ሌላ ኢንቨስትመንቶችን በአማራጭነት እንዲመለከትና የፕሮጀክቱን አካሄድ እንዲለውጥ እያደረገው ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ሁለቱ ኩባንያዎች ያደረጉት ስምምነት፣ የእስራኤሉ ኩባንያ የአላና ፖታሽ ባለአክሲዮን ለመሆን የሚያስችለውን ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የአክሲዮን ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ነበር፡፡ ከአክሲዮን ግዥውና በሽርክና ለመሥራት ካደረጉት ስምምነት ባሻገር፣ የእስራኤሉ ኩባንያ ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በኬሚካል ኢንዱስትሪ ገበያ ውስጥ ያለውን ልምድ በመጠቀም የአላና ፖታሽ ምርትን ለማሻሻጥ ይችላል የሚልም ነበር፡፡

በአፋር ክልል በዳሎል 160 ካሬ ኪሎ ሜትር በሆነ ቦታ ላይ ፖታሽ ለማምረት ሥራ የጀመረው አላና ፖታሽ በይዞታው ላይ ከ1.2 ቢሊዮን ቶን በላይ ፖታሽ ዕምቅ ሀብት ማግኘቱን አረጋግጦ፣ በዚሁ መሠረት ወደ ምርት ለመግባት ሲንቀሳቀስ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

አላና ፖታሽ ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለውን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲችልም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለይ ምርቱ ከሚገኝበት ዳሎል እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ የባቡር መስመር እንደሚዘረጋ ተገልጾ፣ ለዚህ የባቡር መስመር ዝርጋታም አላና ፖታሽ ድጋፍ አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች