Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ ነው

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ ነው

ቀን:

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ሲባል ከቆመበት ተነቅሎ በብሔራዊ ሙዚየም በክብር የተቀጠመው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፣ በሁለት ወራት ውስጥ የቀድሞ ቦታው እንደሚቆም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ከተሞች መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ ያቋቋሙት ኮሚቴ የሐውልቱን ወደ ቦታው በአግባቡ መመለስ እንደሚከታተሉ ታውቋል፡፡ ‹‹የሐውልቱን መመለስ ቢበዛ በሁለት ወራት ውስጥ እውን እናደርጋለን፤›› ሲሉ አቶ ዮናስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ሲባል ከባቡሩ ፕሮጀክት ጋር የተለያዩ የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኘው አሰር ኮንስትራክሽን መመረጡን አስረድተዋል፡፡

ቀላል የከተማ ባቡሩ ፒያሳ ምንሊክ አደባባይን አልፎ በምድር ውስጥ የሚጓዝ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማድረግ 20 ሜትር ጥልቀት ወደታች መቆፈሩንና በአሁኑ ወቅት ግንባታው ተጠናቆ በላዩ ላይ ተሽከርካሪዎች የሚያልፉበት አደባባይ በመገንባት ላይ ነው፡፡

በዚሁ ሥፍራ ላይ የቆመው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልትም ለዚሁ ግንባታ ሲል ከሥፍራው መነሳቱ ይታወሳል፡፡

አንዳንድ የሥነ ግንባታ ባለሙያዎች ባቡሩ ከሥር የሚያልፍ ሆኖ ሐውልቱ ደግሞ ከላይ በተገነባው አደባባይ ላይ የሚያርፍ መሆኑ ሥጋትን ፈጥሮባቸዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ ባቡሩ ከሥር በሚያልፍበት ወቅት የሚፈጥረው ንዝረት በሐውልቱ ላይ መሰንጠቅ ሊፈጥር ይችላል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ተገቢውን የምህንድስና ባለሙያዎች ተሳትፎን ያካተተ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ዮናስ ግን አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም ግንባታ መርገብገብን (ቫይብሬሽንን) እንዲችል ተደርጎ ነው የሚገነባው፡፡ መርገብገብ የሚፈጠር ቢሆንም ሐውልቱ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ይከናወናል ብለዋል፤››

በ1875 ዓ.ም. ፍቼ የተወለዱትና ከኢትዮጵያ የመጀመርያ አራት ጳጳሳት አንዱና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነት ሲያካሂድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተው ነበር፡፡ ከማይጨው መልስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን  ለአርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡

አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች በሰሜናዊ ምዕራብና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺስት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፣ ሕዝቡም ሆነ አገሪቱ ለፋሺስት ጣሊያን እንዲገዙ እንዲቀሰቅሱ ቢያዛቸውም፣ ‹‹እምቢ ለአገሬና ለሃይማኖቴ›› ብለው፣ ሕዝቡ ለፋሽስት ጣሊያን እንዳይገዛ በማውገዛቸው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ተቀብለዋል፡፡ ለመታሰቢያቸውም ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. ሐውልት እንደቆመላቸው ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ሙዚየም የቆመው  የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሁለተኛው ሐውልታቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሐውልት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የአለባበስ ትውፊት ያልተከተለ በመሆኑ ተነቅሎ በመናገሻ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አፀድ እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ከስፍራው ለጊዜው የተነቀለው ሐውልት የቀላል ምድር ባቡር ግንባታ ሥራው በተያዘለት ጊዜ ሲፈጸም፣ አዲስ በሚገነባው አደባባይ ላይ ሳይለወጥ በ2006 ዓ.ም. እንደሚመለስ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...