‹‹ሪል ስቴቱ ችግር ውስጥ የወደቀው ሀብት አጥቶ ሳይሆን እምነት በመጥፋቱ ነው›› አቶ ኤርሚያስ አመልጋ
መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበሩ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከሁለት ዓመታት በፊት በድንገት ከአገር በመውጣታቸው፣ ሥራውን አቋርጦ የነበረውና በተለይ በቤት ገዢዎች ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት አክሰስ ሪል ስቴት፣ ከየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛ ሥራውን መጀመሩ ተገለጸ፡፡
አክሰስ ሪል ስቴት ሥራውን መጀመሩን ይፋ ያደረገው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ድርድር በሕግ ያለመጠየቅ ዋስትና ተሰጥቷቸው፣ በስደት ለሁለት ዓመታት ከቆዩበት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱ በ15ኛ ቀናቸው፣ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በሰጡት ቁጥብ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
አቶ ኤርሚያስ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ይመሩት የነበረው አክሰስ ሪል ስቴት፣ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ቤት ገዢዎች ሙሉ ክፍያ፣ ግማሽና የተወሰኑ ክፍያዎችን ተቀብሏል፡፡ ለቤት ገዢዎቹ በገቡት ውል መሠረት ቤታቸውን ገንብቶ ለማስረከብ ውል የፈጸመ ቢሆንም፣ የገባውን የውል ግዴታ በወቅቱ ሊወጣ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ከአስገንቢዎቹ በተፈጠረ ጫና ምክንያት አቶ ኤርሚያስ ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ አማካይነት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉበት ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የአክሲዮን ማኅበሩን ችግር ለመፍታት ሲንቀሳቀስ እንደነበር፣ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢና የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም አክሲዮን ማኅበሩ ወደተፈለገው የሥራ እንቅስቃሴ እንዲገባና ወደ ውጤት እንዲመለስ ለማድረግ፣ ከአገር ወጥተው ከነበሩት የማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ ጋር የቀጥታ ድርድር በማድረግ፣ በሕግና በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲ የተቀመጡ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና ሕጉ የሚፈቅደውን በሕግ አግባብ በማድረግ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አቶ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ፣ ተቋቁሞ ለነበረው ዓብይና ቴክኒክ ኮሚቴ (ከቤት ገዢዎች፣ ከውጭ ጉዳይ፣ ከንግድ፣ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተወከሉ ናቸው) የሥራ ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀው፣ አሥር ገጽ ጥቅል ዕቅድ ማቅረባቸውንም አቶ ኑረዲን አስረድተዋል፡፡ ከየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮም መደበኛ ሥራ መጀመራቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
እሳቸው ይመሩት በነበረው አክሰስ ሪል ስቴት ላይ የተፈጠረው ችግር ለባለጉዳዮቹ፣ ከውጭ ሆኖ ለሚመለከተውም ሆነ ለራሳቸው ሊታሰብ የማይችልና ግራ የሚያጋባ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገር መባሉ ትክክል መሆኑንና ነገር ግን ለምን እንደተፈጠረ፣ ማን ችግሩ እንዲፈጠር እንዳደረገና ሌሎች እውነታዎችን ጊዜውን ጠብቀው እንደሚናገሩ ቃል ከመግባት ባለፈ በወቅቱ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
‹‹አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ትልቅ ሀብት ይዟል፡፡ ከችግርም የሚያድነው ይኸው ትልቅ ሀብት ነው፡፡ መንግሥትም አምኖበት የገባው ትልቅ ሀብት ያለው ድርጅት በመሆኑ ነው፤›› ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ሥራውን ሊያቆም የቻለው ሀብት አጥቶ ሳይሆን እምነት በመጥፋቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እምነት ከሌለ ሁሉም ነገር እንደሚሸረሸርና እንደሚሸሽ የጠቆሙት አቶ ኤርሚያስ ቤት ገዢው፣ ባለድርሻው፣ ሕዝቡና መንግሥት እምነት ካላቸው ድርጅቱ ሊፈርስ እንደማይችል ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ አሁን ትልቁ ዓላማቸው እምነት መገንባት እንደሆነም አክለዋል፡፡ ድርጅቱ እንዳይፈርስ መንግሥት እጁን አስገብቶ ውሳኔ ማሳለፉ ሊያስመሰግነው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በአክሰስ ሪል ስቴት ያለው ሥራ ያንን ያህል የሚያስጨንቅና የሚያስቸግር ባለመሆኑ በቀላሉ እንደሚከናወን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ቤት የገዛም ሆነ የአክሲዮኑ ባለድርሻ የሆነ ሰው ቤቱን ከፈለገ ቤቱን፣ ወይም የከፈለውን ገንዘብ ከነወለዱ እንደሚያገኝ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው፣ ድርጅቱና መንግሥት በአጭር ጊዜ የሚፈጽሙት ተግባር መሆኑንም አክለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት መብታቸውን በሕግ ለማስከበር ወደ ፍርድ ቤት ከሄዱ ቤት ገዢዎችና ድርጅቶች የተወሰኑት በሒደት ላይ ቢሆኑም፣ የተወሰኑት ውሳኔ አሰጥተው በአፈጻጸም ላይ መሆናቸው በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኑረዲንና አቶ ኤርሚያስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱ በሕግ አግባብ ማግኘት የሚገባቸውን ማግኘት መብታቸው መሆኑን፣ ኮሚቴውም ሆነ መንግሥት በሕግ የተያዙ ጉዳዮችን የማስቆም መብት እንደሌላቸውና ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን አቶ ኑረዲን ተናግረዋል፡፡ ሪል ስቴቱም በሕግ አግባብ መፍትሔ ለማምጣት ወደ ፍርድ ቤት እንደሚሄድ፣ አንዳንድ ውሳኔ የተሰጠባቸው ክሶች አክሰስ ሪል ስቴት መጥሪያ ሳይደርሰው፣ በፍርድ ቤት ቆሞ እንዲከራከር ሳይደረግና ምንም ዓይነት ጥሪ ሳይደረግለት የተላለፉ በመሆናቸው፣ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ይግባኝ በማለት፣ ውሳኔዎቹን እንደሚያስቀለብሱና ችግሩን በመግባባት እንደሚፈቱ ተስፋ እንዳላቸው አቶ ኑረዲን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቶቹ የሰጡት ውሳኔ አብዛኛውን ኅብረተሰብ ያማከሉ ውሳኔዎች ከሆኑ እንደማይቃወሙና ውሳኔውን እንደሚያከብሩም አክለዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስም የአቶ ኑረዲንን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ በዋናነት ከአገር እንዲወጡ ያስገደዳቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ቤት ገዢዎች ቤቱን የሚረከቡበት ቀነ ገደብ በማለፉ፣ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ የጻፉላቸው ቼኮች በቂ ስንቅ ስላልነበራቸው በባንክ በማስመታት በደረቅ ቼክ ሊከሷቸው በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑንና (ፖሊስ ጣቢያ ታስረው በዋስ መፈታታቸው ይታወሳል) ደረቅ ቼክ በወንጀል የሚያስጠይቅ በመሆኑ፣ እንዴት ዋስትና ሊሰጣቸው እንደቻለ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኑረዲን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኑረዲን እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ፖሊሲና የወንጀል ሕግ በሚፈቅደው መሠረት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር በደንብ ተመርምሮና ተረጋግጦ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለጊዜው ያለውን ችግር እንዲያስጨርሱ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳስመጣቸውም ገልጸዋል፡፡ የተመሠረተባቸውን ክስ በመፍራት አገራቸውን ትተው ለተሰደዱ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ዕድል ለምን እንዳልተሰጠ ለቀረበላቸውም ጥያቄ፣ አቶ ኑረዲን ሌላውም ይህንን ዕድል የማግኘት መብት እንዳለው ከመጠቆም ያለፈ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም፡፡ መንግሥት እጁን እንዲያስገባ የተደረገው የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት መሆኑንም አክለዋል፡፡
የአቶ ኤርሚያስ መምጣት መንግሥት ባቋቋመው ዓብይና ቴክኒክ ኮሚቴ ሥራ ላይ ተጨማሪ እርሾ ከመሆን ባለፈ በሥራው ላይ የሚቀንሰውም ሆነ የሚጨምረው ነገር እንደሌለ በመናገር፣ ‹‹አቶ ኤርሚያስ ባይመለሱም ኖሮ አክሲዮን ማኅበሩ ሥራውን መሥራቱ አይቀርም ነበር፤›› የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ባለአክሲዮኖቹም ሆኑ ቤት ገዢዎቹ እምነት ሊያድርባቸው እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ኑረዲን፣ በሦስት ሌሎች ሪል ስቴቶች ከ198 በላይ ቤት ገዢዎች ላይ ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ፣ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ችግሩ እንዲፈታ ማድረጉን በመጠቆም፣ የአክሰስ ሪል ስቴት ደንበኞችም በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በአክሲዮን ማኅበሩ ላይ ኃላፊ ወይም የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው እንደማይቀጥሉና አክሲዮን ማኅበሩ አዲስ ቦርድ መርጦ፣ በሰነዶች ማረጋገጫና መመዝገቢያ ጽሕፈት ቤት ዕውቅና አሰጥቶ በሥራ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ አቶ ኤርሚያስ የኋላ ደጀን ሆነው ሥራውን የመምራትና የማሠራት ኃላፊነት ብቻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ ከፈለገ ሊያሳትፋቸውና አባል ሊያደርጋቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ከአገር እንደወጡ ተመልሰው እንደሚመጡ ማሳወቃቸውን አስታውሰው፣ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ከሁሉም ድርጅቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘውን ጋቢ የተሰኘውን ኩባንያ ጨምሮ ከሌሎቹም ጋር በመደራደር እንደየፍላጎታቸው ሊፈጽሙላቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ከአገር ከወጡ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ዕቅዳቸው እንደነበርና መንግሥት እንደሚያስራቸው እየነገራቸውም ቢሆን ይመጡ እንደነበር የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹እኔ አንደ አንድ ግለሰብ መታሰር አለመታሰር አስበርግጎኝ አያውቅም፡፡ ማንም ይታሰራል ይፈታል፡፡ ችግር የለውም፡፡ እስር ቤት እንዳቀባበሉ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ዕረፍት ይሆናል፡፡ እሱ የሚያስጨንቅ አይደለም፡፡ በታሪክም፣ አሁንም ማንም ታስሮ ይፈታል፡፡ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር ግን ሥራ ነው፤›› ብለው፣ እሳቸው ቢታሰሩ ኖሮ አክሰስ ሪል ስቴት የባሰ ብትንትኑ ይወጣ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው የማይሆን ነገር ከፊታቸው ተደቅኖ በማየታቸው መሸሻቸውን አምነዋል፡፡ ‹‹ጥፋት ካለብኝ እኔም ዜጋ ነኝ በጥፋቴ መታሰር አለብኝ፡፡ ክሱን ፈርቼና ሸሽቼ አልቀርም፡፡ መንግሥት ዋስትና ባይሰጠኝም ኖሮ መምጣቴ አይቀርም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ለአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች እንደየፍላጎታቸው የቤት ግንባታውን በጀመሩ አንድ ዓመት ውስጥ ሠርተው ለማስረከብ ቃል ገብተው መመለሳቸው ታውቋል፡፡