Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመንግሥት ሹማምንት የኃላፊነትና የተጠያቂነት ወሰን በግልጽ ይታወቅ!

  በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ዋና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት ዜጐች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን ተረድተው በሥርዓት እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታዊ ተቋማት አወቃቀርና የሹማምንቱ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰን ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ዜጐች የታክስና የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑና ለአገራቸው ባላቸው አቅምና ዕውቀት እንዲያገለግሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን የሚያስፈጽሙ የመንግሥት ተሿሚዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት አሠራር ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡

  የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲጐድለውና የሹማምንቱ የተጠያቂነት ወሰን በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ፣ የዜጐች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ተሿሚዎች በአግባቡ የሥራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፡፡ ባለጉዳዮች አንድ ተሿሚ የያዘውን ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ለወራት ይንከራተታሉ፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ግዴታውን እየተወጣ፣ ተሿሚው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ማከናወን ሲያቅተው እንዴት ነው የሚጠየቀው? የት ነው የሚከሰሰው? የት ነው የሚዳኘው? በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

  ባለጉዳዮችን እያንገላታ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቅም ለማጋበስ የሚፈልግና ሥልጣኑን መከታ በማድረግ ሕግ የሚጋፋ ሹም ማን ነው የሚያስታግሰው? ኢሕአዴግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ‹‹ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አልታገስም›› ሲል ይደመጣል፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ የሥርዓቱ አደጋ እንደሆኑ ይወተውታል፡፡ ነገር ግን የሰው ኪስ ካልዳበሱ ሥራ መሥራት የማይሆንላቸው ሙሰኞች ሕዝብ እያማረሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ባለጉዳዮች መብታቸውን ለማስከበር ከሙሰኞች ጋር መደራደር እንደሌለባቸውና ድርጊቱም ሕገወጥ መሆኑ ቢታመንም፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ የተደራጁ ኃይሎችን እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በደላላና በጉዳይ አስፈጻሚዎች አማካይነት መረን የተለቀቀውን ሙሰኝነት መንግሥት ካልዘመተበት ማን ይቋቋመዋል? እኔ ሙሰኝነትን አይዞህ አላልኩም ብሎ በድፍረት ካላስታወቀ እንዴት ሊኮን ነው? በዚህ ላይ የራሱ የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ግልጽ ሆኖ መታወቅ አለበት፡፡ የሹማምንቱም ተጠያቂነት እንደዚሁ፡፡

  በዘመናዊው ዓለም መንግሥት ሕዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት የሚያገኘው በሕዝብ ነፃ ፈቃድ ነው ሲባል፣ ይህ ከሕዝብ በነፃነት የተሰጠ አደራ የኮንትራት ስምምነት ነው ማለት ነው፡፡ የምርጫ ወቅት ደግሞ የኮንትራት ማደሻ ጊዜ በመሆኑ ለዚህ ስምምነት መገዛት የግድ ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ዘመናዊ እሳቤ ውስጥ ሆኖ ሕዝብን ያገለግላል ሲባል፣ በመንግሥት ውስጥ የመሸጉ የተደራጁ ኃይሎች ሰብዓዊ መብት ሲጥሱና የሕግ የበላይነትን ሲጋፉ ዝም ከተባለ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ወሰኑ አልታወቀም ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ስለዴሞክራሲ መነጋገር አይቻልም፡፡ እንነጋገር ከተባለ ደግሞ የዜጐችን መብት እየደፈጠጡ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሰበካ የሚያደርጉ ሹማምንት፣ እናንተስ ምን እያደረጋችሁ ነው ተብለው ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በጥፋታቸው መጠንም ሕጋዊ ቅጣት ይከናነቡም ዘንድ ተገቢ ነው፡፡ እንዲህ ካልተደረገ ስለግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዴት መነጋገር ይቻላል?

  የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕጉ ዜጐችን ካልታደገ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ካላገለገሉ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች ሕዝቡን በሥርዓት ካላስተዳደሩ፣ የገበያውን ጤናማነት እየተቆጣጠሩ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት እንዲያሰፍኑ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግዴታቸውን ካልተወጡ፣ የሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካልተወጡ፣ ግዴለሽነትና ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ አካላት እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ከተደረገ፣ ወዘተ መንግሥት አገር እያስተዳደርኩ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፡፡ ይልቁንም አሉታዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ግለሰቦችና ቡድኖች እየቦረቦሩት ነው ማለት ይቀላል፡፡ ስለዚህ ምን ታስቧል? በእጅ ላይ ያለ አፋጣኝ መፍትሔስ ምንድነው?

  ምንም እንኳን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ‹‹ገበያ መር›› ነው ተብሎ ቢነገርም፣ በእርግጥ ገበያው በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ሕግጋት ነው የሚመራው? ወይስ የጥቂት አድመኞች መፈንጫ ነው? እነዚህ ገበያውን ሥርዓተ አልባ ያደረጉ ኃይሎችስ ማንን ተማምነው ነው ሕዝብ የሚያስለቅሱት? የሸቀጦችንና የአገልግሎቶችን ዋጋ እንደፈለጉት እንደ ካርታ ሲፐውዙት ማን ነው የሚጠይቃቸው? በሕዝቡ ውስጥ ማኅበራዊ እኩልነት ሰፍኖ ዜጐች በአገራቸው ልማት ተሳታፊና የውጤቱ የጋራ ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው፣ ይህ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚሆኑ ራስ ወዳዶች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ በተለይ የመንግሥት ሥልጣንን ላልተገባ ዓላማ በማዋል ዜጐችን የሚያስለቅሱ ኃይሎች እንዴት ነው በዚህ ድርጊታቸው የሚቀጥሉት? የኃላፊነቱና የተጠያቂነቱ ወሰን የት ጋ ነው?  

  የመልካም አስተዳደር እጦት የአገር አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ በተደጋጋሚ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙባቸው የውይይት መድረኮች ብዙ ተብሏል፡፡ ነገር ግን የችግሮቹን ምንጮች ታሪካዊ ዳራ እያወሱ በይደር ከመተው ይልቅ፣ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ወገኖች መጠየቅ ማንን ይገዳል? በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ‹‹ራዕይ›› እና ‹‹ተልዕኮ›› እንዲሁም ‹‹የሥነ ምግባር መርሆዎች›› የሚሉ ታፔላዎች ቢለጠፉም ፋይዳ ቢስ ሆነው ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ መፍትሔ ያጣ ነገር ተሸክሞ ከመዞር፣ ችግሩን አሽቀንጥሮ መጣልና መገላገል ለምን ያቅታል? የተጠያቂነትና የኃላፊነት ወሰን በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ አገር ይታመሳል፡፡

  የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ መደበላለቅ እንደሌለበት አገር ያወቀው ሀቅ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በተለይ በምርጫ ወቅት የመንግሥት ንብረት፣ የሰው ኃይልና ገንዘብ መጠቀም የለበትም፡፡ ነውር ነው፡፡ ለምርጫ ሊያገለግሉ የሚችሉ የመንግሥት ቁሳቁሶች ቢኖሩ እንኳ በሕጉ መሠረት ከሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ጋር መካፈል አለበት እንጂ፣ እንደ ራሱ ንብረት ለብቻው መገልገል የለበትም፡፡ ምናልባት ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የተሻለ ተጠቃሚነት አለው ቢባል እንኳን፣ ይሉኝታ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን መርህ በመጋፋት አላስፈላጊ ተግባራት የሚፈጽሙ ሹማምንትን ማን ነው የሚቆጣቸው? እንዴትስ ነው የሚጠየቁት? ልጓም ያስፈልጋል፡፡

  የሕዝብ አደራ አለብኝ የሚል መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን ከማሳደግና መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ማኅበራዊ ዋስትና ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የኑሮ ውድነትን በማርገብ፣ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት በማስፈን፣ የዜጐችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን በማስፋት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት በማስከበርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ይገለጻል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖረው ደግሞ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲታይበት ነው፡፡ ባለሥልጣናቱም በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲደረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመንግሥት ሹማምንት የኃላፊነትና የተጠያቂነት ወሰን በግልጽ ይታወቅ የሚባለው!       

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

  ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...