Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፔትሮትራንስና መንግሥት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክርክር ሊጀምሩ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ተቀማጭነቱ በሆንግ ኮንግ የሆነው ፔትሮትራንስ የተሰኘው የቻይና የነዳጅ ኩባንያና የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በካሉብ ጋዝ ፕሮጀክት ጉዳይ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት የግልግል ፍርድ ቤት ክርክር ሊጀምሩ ነው፡፡

በኦጋዴን ክልል የሚገኙትን የካሉብና የሂላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶች እንዲያለማ የማዕድን ሚኒስቴር ለፔትሮትራንስ የሰጠውን የፔትሮሊየም ልማት ፈቃድ፣ ሚኒስቴሩ አላግባብ ሰርዞብኛል ያለው ፔትሮትራንስ ጉዳዩን ከሁለት ዓመት በፊት ጄኔቭ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የግልግል ተቋም አቅርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ እስካሁን ኩባንያውና የማዕድን ሚኒስቴር ያቀረቧቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ሲመለከት ቆይቷል፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፔትሮትራንስና ማዕድን ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በአካል ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ክርክር ይጀምራሉ፡፡

የማዕድን ሚኒስቴርን ወክለው የሚከራከሩት አቶ ዘውድነህ በየነ ኃይሌ የተሰኙ ነገረ ፈጅ ሲሆኑ፣ ፔትሮትራንስን በመወከል የሚከራከረው ላሊቭ የተሰኘ የስዊዘርላንድ የጥብቅና ቢሮ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴርና የፔትሮትራንስ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የካሉብና የሂላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶች፣ ሌሎች በኦጋዴን የሚገኙ ስምንት የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች በማሌዥያው ፔትሮናስ ኩባንያ ተይዘው የነበሩ ቦታዎች ናቸው፡፡ ፔትሮናስ ለቆ ከወጣ በኋላ የማዕድን ሚኒስቴር የጋዝ ክምችቶቹን የሚያለማና የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍለጋ ሥራ የሚያካሂድ ኩባንያ ለመምረጥ፣ እ.ኤ.አ. 2011 ያወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ፔትሮትራንስ በማሸነፉ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2011 ዓ.ም. የፔትሮሊየም ልማትና የምርት ክፍፍል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው በወቅቱ የማዕድን ሚኒስትር በነበሩት ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉና የፔትሮትራንስ መሥራችና ሊቀመንበር በሆኑት ሚስተር ጆን ቺን መካከል በሸራተን አዲስ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በኋላ የማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ ፔትሮትራንስ በገባው ውል መሠረት ሥራውን በአግባቡ አላካሄደም በማለት፣ የፔትሮሊየም ልማት ስምምነቱን ሰርዘዋል፡፡

በወቅቱ ወ/ሮ ስንቅነሽ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ፔትሮትራንስ ከወረቀት ያለፈ ሥራ መሥራት ያልቻለ ደላላ ኩባንያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹የመስክ ሥራ በታቀደው ጊዜ መጀመር አልቻለም፡፡ ከእንግዲህ መሬት ታቅፈው የሚቀመጡ ደላላ ኩባንያዎችን አንታገስም፤›› ብለው ነበር፡፡

የፔትሮትራንስ ኃላፊዎች የሚኒስትሯን ወቀሳ ያስተባብላሉ፡፡ ኩባንያው በወቅቱ ለሪፖርተር በሰጠው ምላሽ በዓለም አቀፍ የፔትሮሊየም ኢንዱስትሪ በተለመደ አሠራር፣ የመስክ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የሚሠሩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደነበር፣ ከጋዝ መሬቶቹና ከሌሎች የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች የተሰበሰቡ የፔትሮሊየም ዳታዎችን በመተንተን ላይ እንደነበርና ይህንንም የሚሠሩለት ዓለም አቀፍ አማካሪዎች ቀጥሮ በማሠራት ላይ እንደነበር ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ስምምነቱን በሰረዘበት ወቅት የመስክ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደነበር የገለጸው ፔትሮትራንስ፣ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት የወሰደው ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት በማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች እንቢተኝነት ከተደናቀፈበት በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ከፔትሮትራንስ የነጠቃቸውን የጋዝ መሬቶችና ስምንት የነዳጅ ፍለጋ ብሎኮች ፖሊጂሲኤል ለተሰኘ ለሌላ የቻይና ኩባንያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡   

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች