Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽብርተኝነት የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተወሰነባቸው

በሽብርተኝነት የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተወሰነባቸው

ቀን:

– በድጋሚ ፍርድ ቤት ደፍራችኋል በሚል የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶ ለቅጣት ተቀጠሩ

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ጠምቶታልና እግዚአብሔር ፍትሕ ይስጠው›› አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበሩ

‹‹ተራ ስድብ ተሳድባችኋልና ማዕከላዊ እንድትመረመሩ እናዛለን›› ፍርድ ቤት

በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በሙግት ላይ የሚገኙት የአንድነት፣ የዓረናና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጥፋተኛ በተባሉበት ፍርድ ቤትን መድፈር ወንጀል ክስ፣ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔ ሰጠ፡፡

ተከሳሾቹ የሰባት ወራት የእስራት ቅጣት የተወሰነባቸው የዋስትና መብት ተከልክለው በእስር ላይ በሚገኙበት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ታኅሳስ 12 ለ13 አጥቢያ 2007 ዓ.ም. የተቋሙ አባላት ባልሆኑ የደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ናቸው ባሏቸው ግለሰቦች ተፈትሸው፣ ሰነዶችና ገንዘብ እንደተወሰደባቸው ለፍርድ ቤቱ ላቀረቡት አቤቱታ፣ ‹‹በማስረጃ የተደገፈ አይደለም›› በማለት ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን በመቃወም ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹ፍርድ ቤት ደፍራችኋል›› ተብሎ በተላለፈባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን በችሎት ሲያሰማ፣ የሦስቱም ፓርቲዎች አመራሮች በማጨብጨባቸው ችሎቱ ለደቂቃዎች ታውኮ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት አለመድፈራቸውንና በወቅቱ የተናገሩት መሯቸው እንደሆነ በቡድን ተናግረዋል፡፡

በፍርድ ቤት ሊናገሩ የቻሉት መሯቸውና ፍርድ ቤቱ ‘አሻንጉሊት ፍርድ ቤት’ በመሆኑ ፍትሕ እንደማያገኙ በማመናቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ችሎቱ እውነተኛ ችሎት ባለመሆኑ ችሎት አለመድፈራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የአመራሮቹን ንግግር አስቁሞ፣ ‹‹ተራ ስድብ ሰድባችሁናል፡፡ ፖሊስ ወደ ማዕከላዊ ወስዶ እንዲመረምራችሁ እናደርጋለን፤›› ካለ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ አሻንጉሊት ስለሆነ ፍትሕ እንደማያገኙ የተናገሩትን አቶ አብርሃ ደስታ እያስቀረፁ እንዲናገሩ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃቸው፣ ‹‹ሰምታችኋል ለምን በድጋሚ እናገራለሁ? ከዚህ በፊትም ተቀርጬ ነው ጉድ የሆንኩት፤›› በማለት ሳይናገሩ ቀርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተመካክሮ ሦስቱም አመራሮች ጥፋተኛ መሆናቸውን ከነገራቸው በኋላ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ‹‹እኛ በፍርድ ቤቱ ላይ እያፌዝን አይደለም፣ ታፍነናል፤›› ሲሉ ፍርድ ቤቱ አስቁሟቸዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንኤል ሽበሺ ሲጠየቁ፣ ‹‹ፍትሕ የለም …›› ሲሉ እሳቸውንም ፍርድ ቤቱ ሲያስቆማቸው፣ ‹‹ታዲያ እንዴት ልናገር?›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ከልክሎ ሦስቱም አመራሮች ከችሎቱ እንዲወጡ አዝዟል፡፡ አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ተጠምቷልና እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ይስጠው፤›› እያሉ ችሎቱን በፖሊስ ኃይል እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡

በሽብርተኝነት ከተጠረጠሩትና ክስ ከተመሠረተባቸው የአንድነት አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው ተነስተው አቤቱታ እንዳላቸው ሲናገሩ ተፈቀደላቸው፡፡ ታኅሳስ 12 ለ13 ቀን 2007 ዓ.ም. የማረሚያ ቤት አባላት ባልሆኑ ሰዎች ተፈትሸው ገንዘብና ሰነዶች እንደተወሰዱባቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታወሱ፡፡ በወቅቱ አቤቱታውን ያቀረቡት በጠበቃቸው በአቶ ተማም አባቡልጉ አማካይነት ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በወቅቱ የሰጠው ምላሽ ለደኅንነታቸው እንደሚያሰጋቸው ገልጿል፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ሲያመለክቱ ስላልተመዘገበላቸው አሁን እንዲመዘገብላቸው አመልክተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በጠበቃቸው በኩል ሲያመለክቱ፣ ከአንድ ጠበቃ የማይጠበቅ አቤቱታ መሆኑንና ማረሚያ ቤቱ የበቀል ዕርምጃ ቢወስድባቸውስ የሚል ምላሽ ፍርድ ቤቱ በመስጠቱ፣ ፍርድ ቤቱ ምንም እንደማያደርግላቸው በመገንዘባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አስሮዋቸው ዋስትና ሲከለክላቸው፣ ደኅንነታቸውን የሚጠብቅ ቢሆንም አሁን ግን ለደኅንነታቸው ሥጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ውድቅ በማድረጉ ምክንያት ይግባኝ ማለት አለማለታቸውን ወደፊት የሚያየው መሆኑን ገልጾ እንዲመዘገብላቸው ግን አሳስቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ አቶ ሀብታሙ አቤቱታቸውን በጽሑፍ አቅርበው ብይን እንደሚሰጥ፣ በሦስቱ አመራሮች ላይ ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ እንደሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ የወሰነው ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...