የጎዳና ሯጮች (Road Runner) የሚባሉ ወፎች ስማቸውን ያገኙት ከመኪና ፊት ለፊት በመሮጣቸው ነው፡፡ የምድር ኩኩ (Ground Cuckoo) እና እባብ በል (Snake Eater) ሌላው ስማቸው ነው፡፡ እነኚህ ወፎች ራትል እባብ (Rattle Snake)ን ሲያጠቁ፣ ሲገሉና ሲመገቡ ይታያሉ፡፡ ወፎቹ እባቡን የሚያጠቁት ክንፋቸውን ዘርግተው ላባቸውን በመበተን ሲሆን፣ ይህም የእባቡን ጥቃት ከላባው አልፎ እንዳይሄድ ያደርገዋል፡፡ በመጨረሻም ጭንቅላቱን አግኝተው እባቡን ይመቱትና የጦርነቱ ፍጻሜ ይሆናል፡፡ የሚመገቡት የሚችሉትን ያህል ውጠው በመፍጨት ነው፡፡ የተረፈውን የእባቡን አካል ደግሞ እያንጀላጀሉ እስኪውጡት ድረስ ወዲያ ወዲያ ይዘዋወራሉ፡፡
ሌሎች ወፎች ጭልፊትና ንስር አልፎ አልፎ እባብ ይበላሉ፡፡ ነገር ግን ዝነኛው ገዳይ ጸሐፊ ወፍ (Secretary Bird) ነው፡፡ ስማቸውንም ያገኙት ላባቸው ወደ ኋላ ቀሰር ያለ በመሆኑና ይህም ከድሮዎቹ ጸሐፊዎች (የላባ ብዕር ከጆሮዎቻቸው ኋላ ሸጎጥ ያደርጉ ስለነበር) ጋር ስለሚያመሳስላቸው ነው፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004 ዓ.ም.)