Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ኮማኖየ›› - የጌዴኦ ጥንታዊ የሴቶች አስተዳደር ሥርዓት

‹‹ኮማኖየ›› – የጌዴኦ ጥንታዊ የሴቶች አስተዳደር ሥርዓት

ቀን:

በሔኖክ ሥዩም

ዛሬ ላይ ብዙዎችን የሚያነጋግረው የሴቶች ጭቆናና ጥቂት ሥልጡን አገሮችን ደረት ያስነፋው የሴቶች መጠነኛ የኃይል /ሥልጣን/ ተጋሪነት እንደ እኛ ላሉ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት ሕዝቦች የተደበላለቀ ስሜት ይፈጥርብን ይሆናል፡፡ ልዩ ልዩ ጥናቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ሴት ነገሥታት፣ አካባቢያዊ መሪዎችና አብዮተኞች እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡

የዮዲት የጀግንነትን ታሪክ፣ የነባቲ ድል ወንበሪን እልህ፣ የእነ እቴጌ ሰብለ ወንጌልን ወኔ፣ የእቴጌ ምንትዋብን ብስለትና የእነ እቴጌ ጣይቱን ቆራጥነት የምንመዘው ከኢትዮጵያውያንት ነገሥታት ታሪክ ነው፡፡ ወደ ጌዴኦ ልውሰዳችሁ፡፡

የጌዴኦ ታሪክ የሚያነሳው አንድ ገጽታ ሴትን በሚመለከት ያለንን ነባር የሥነ ጾታ አስተሳሰብ ያሳያል፡፡ ጌዴኦ ሴት ወላድ በመሆኗ ንግሥት ናት የሚል እምነት አለው፡፡ ይህ እምነት የተቀዳው ከነባር ባህሉ ነው፡፡ ባህሉ የሴት ልጅን መውለድ ማጥባት ማሳደግ የቤት ውስጥ ኃላፊነት የመሳሰሉ ክህሎቶችን ወደር አልባ አድርጎ ስለሚመለከት ለሴት ልጅ የሚሰጠው ክብር ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም የባህላዊ አስተዳደሩ መሥራች ሴት ናት የሚል የቀደመ እምነት አለ፡፡

የጌዴኦ ባህል ዛሬም ይህንን ያሳያል፡፡ ዛሬም ጌዴኦ ተሰብስቦ አምላክን የሚለምነው  ሴትና ሕፃናትን ከፊት በማስቀደም ነው፡፡ ባህሉ ሴትና ሕፃናት ንጹኃን ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም ማጌኖ ወይም ፈጣሪ እነሱ የቀደሙበትን ምህላ ይሰማል የሚል እምነት አለ፡፡ አኮማኖየ የሚባለው የጌዴኦ ባህላዊ አስተዳደር ሴት መር አስተዳደር ሲሆን ሥርዓቱ በጎሣሎ ባህላዊ የአስተዳደር ሥልት እስኪቀየር ድረስ በጌዴኦ ዘንድ የሠራ ባህል ነው፡፡

አኮማኖየ የአንዲት ሴት አስተዳደር መንግሥትም አይደለም፣ ሥርወ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ሥርወ መንግሥትም የተለያዩ ሴቶች እየተተካኩ ሥልጣኑን በመያዝ አስተዳድረዋል፡፡ ይህ መተካካትም የአንዲት ሴት አኮማኖየ የአስተዳደር ዘመን በዕድሜ ምክንያት ሲያበቃ ሌላኛይቱ እየተተካች ለረዥም ዘመን የቆየ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡

ይህ ወቅት አስገራሚ ክስተቱ የሥራ ክፍፍሉ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሴቶች የሚሠሩት ልጅ የመመገብ፣ የማዘል፣ የመንከባከብ፣ ምግብ የማብሰልና እንጨት የመልቀም ተግባራትን የሚሠሩት ወንዶች ነበሩ፡፡ ይህንን እውነታ አንጋፋ የጌዴኦ የሀገር ሽማግሌዎች ከቀደሙት አባቶቻቸው እንደተቀበሉት ሁሉ ዛሬም ለልጆቻቸው ያወሱታል፡፡

ይህ ዘመን ብዙ ከዛሬው ዘመን ጋር የሚቃረኑ እውነታዎች ያሉት ነበር፡፡ ለምሳሌ ጋብቻ በሁለቱ ጥንዶች ስምምነት ቢከናወንም የጋብቻ ጥያቄው የሚቀርበው ግን በሴቷ ነበር፡፡ ጋብቻው ፍጻሜውን የሚያገኘውም በሴቷ ቤት ነበር፡፡ አኮማኖየ መንግሥቱን እንደምታስተዳድረው ሁሉ በየቤቱ ያሉ እማወራዎችም የቤታቸው አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡

የተወለደው ልጅ በእናቱ የሚጠራ ሲሆን የንብረት ባለቤትነት ደግሞ የሚስት ነው፡፡ ቤተሰባዊ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ወሳኝ የሚባለው ውሳኔ የሚሰጠው በሴቷ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ከዘውዳዊ አገዛዝ ጋር ተመሳሳይነት ሲኖረው ችሎትን ጨምሮ ውሳኔዎችን የምትሰጠው ደግሞ ንግሥቲቷ ናት፡፡ ይህች ንግሥት በምንም መልኩ ሴቶችን ተጎጂ የሚያደርግ ውሳኔ እንደማትሰጥ ይነገራል፡፡

ለአኮማኖዬ ሥርዓተ መንግሥት መውደቅ ምክንያት የሚባለውን በተመለከተ የጌዴኦ አባቶች ሲገልጹ የወንዶች ጭቆና መብዛትና የሴቶች የበላይነት በከፍተኛ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ነው ይላሉ፡፡ ከዚያም ወንዶቹ ንግሥቲቷን በመገርሰስ የወንዶች የበላይነትን በእያንዳንዷ ሴት ላይ የሚጭን አዲስ ሥርዓት ተመሠረተ፡፡

በመጨረሻም አኮማኖዬ የሚባለው ሥርዓት በወንዶች ምሥጢራዊ አመፅ ተወግዶ የጎሣሎ አስተዳደራዊ ሥርዓት ተተካ፡፡

ከአዘጋጁ፤- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...