(ፎቶ በታምራት ጌታቸው)
እንቢ አለች ኢትዮጵያ ቈንዳላ ተሠርታ
ቼኮስሎቫኪያ ገበረች ራሷን ተላጭታ
ነምሳ ጧት ገበረች ራሷን ተላጭታ
ፖሎኝም ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ኢጣሊያ ገበረች በጧት እጇን ሰጥታ፤
ሁንጋሪያ ዐበረች እባርነት ገብታ፤
ሩማንያ ዐበረች እባርነት ገብታ፤
ቡልጋርያም ዐበረች እባርነት ገብታ፤
ሆላንድ ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ዳንማርክ ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ኖርቬዥም ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ዩጎዝላቭ ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ግሪክም ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ሉክሳምቡር ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
ፈረንሳይ ገበረች ራሷን ተላጭታ፤
እንቢ! አለች ኢትዮጵያ ቈንዳላ ተሠርታ።
ታረቀኝ ተፈሪ
(የክብር ዘበኛ ፲ አለቃ፤ ሰቈጤ) ኻርቱም መስከረም 17 ቀን1933 ዓ.ም.
********
ጎጃም ሳይመታ
አለቃ ገብረሐና… አንዲት መልከ መልካም ሴት መኖሪያ ቤቷ ቀጠሮ ይዘው ኖሮ በሰዓታቸው ሲደርሱ ሴትዮዋ በሩን ገርበብ አድርጋ እሳቸውን ስትጠብቅ ቆይታ እንቅልፍ በዚያው ይዟት ሄዷል፡፡ አለቃ ገርበብ ያለውን በር ትንሽ ገፋ አድርገው ሲገቡ #እሜቲቱ$ ተኝታለች፡፡ አለቃ ከመደቡ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ወዲያው አንድ #የባዕድ$ ድምጽ ይሰማል ከስር፡፡ ብም …
#ትግራይን ምታ…$ አለች ሴትዮዋ፡፡ በእንቅልፍ ልቧ ነው፡፡ አለቃ #ፈገግ$ አሉና ተከታዩን ድምጽ ይጠባበቃሉ፡፡ አሁንም #ብም$ አለ፡፡
#ጐንደርን…$ ምታ አለች፡፡ አለቃ ሳቃቸውን በግድ አፍነው ይዘው… #እነዘ ይሴለሱ$ እያሉ አሁንም በልባቸው ቀጣዩን ይጠብቃሉ፡፡
#ብም$ አለ፡፡ እንደተለመደው
#ጐጃምን ምታ$ ብላ ከመቅጽበት ከእንቅልፏ ነቃች አለቃ መደብ ላይ ቁጭ ብለዋል፡፡
#ውይ… አፈር በሆንኩት አለቃ ቆዩ እንዴ ከመጡ… አለች$ የፊቷን ላብ በሸማዋ እየጠረገች እንደ ማፈርም እንደ መደነቅም እያለች፡፡
#አዎ…$ አሉ አለቃ፡፡ #ከመጣሁማ ቆየሁ ገና ጐጃም ሳይመታ ነው የመጣሁት…$ ሲሏት #ኡኡቴ…$ አለችና ወደ ሌላ ወጋቸው ተሸጋገሩ፡፡
- ንጉሤ አክሊሉ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ – ነው መልኳ›› (2001)
ሰው ጤፉ
- ዳኛ፡- የተከሰስክበትን ምክንያት ታውቃለህ?
- ተከሣሽ፡- አዎን ጌታዬ
- ዳኛ፡- ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?
- ተከሣሽ፡- ነኝ ጌታዬ
- ዳኛ፡- ታዲያስ
- ተከሣሽ፡- አለና
ሌላ እደግሞታለሁ
አለቃ ገብረ ሐና ወደመንገድ ሲሂዱ ይመሽባቸውና ወደሰው ቤት ጎራ ብለው የመሸብኘ መንገደኛ ነኝ ብለው ይጠይቃሉ። ባለቤቶቹም ቤት ለንግዳ ብለው ያስገቧቸዋል። ምግብ በላልተው መኝታ ደረሰ። አለቃ አይናቸው ቁልጭ ቁልጭ ሲል ኮረዳዋ «አለቃ ምን ፈለጉ?» ስትላቸው ልጄ ጎኔን የማሳርፈበት ነገር አምጪልኝ አሏት። እሷም እሺ ብላ አንድ የበግ አጎዛ ሰጠቻቸው። እሳቸውም «ምነው ልጄ ይህቺ ትበቃኝ» ሲሏት፤ «እሷን ሲጨርሱ ሌላ እደግምዎታለሁ» አለች ይባላል።
- አረፈዓይኔ ሐጎስ ‹‹የአለቃ ገብረ ሐና ቀልዶች›› (1982)
*****
የካውካሰስ ተራሮች የቋንቋዎች መናኸሪያ
በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ዓመተ ዓለም የኖረው ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ የታሪክ ምሁር “የተለያየ ባሕል ያላቸው በርካታ ሕዝቦች በካውካሰስ ይኖራሉ” ሲል ጽፏል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ ደግሞ ስትራቦ የተባለ ሌላ ግሪካዊ የታሪክ ምሁር በዚህ አካባቢ ስለሚኖሩ 70 የሚያክሉ ነገዶች ጽፏል። እያንዳንዱ ነገድ የራሱ ቋንቋ የነበረው ሲሆን ሁሉም ዳዮስኪዩሪየስ ትባል በነበረ ቦታ መጥተው ይገበያዩ ነበር፤ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ በአሁኑ ጊዜ ሱኩሚ ትባላለች። ከበርካታ አሥርታት በኋላ ሮማዊ ምሁር የሆነው ትልቁ ፕሊኒ፣ ሮማውያን በዳዮስኪዩሪየስ ለመነገድ 130 አስተርጓሚዎች እንደሚያስፈልጓቸው ጽፏል።
በዛሬው ጊዜ በካውካሰስ የሚኖሩ ከ50 የሚበልጡ ጎሳዎች አሉ። እያንዳንዱ ጎሳ በራሱ ባሕል፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በራሱ አለባበስ፣ ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንፃ ይኮራል። በዚህ አካባቢ በትንሹ 37 የሚያክሉ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው ሲሆን ሌሎቹ ቋንቋዎች ደግሞ በጥቂት መንደሮች ብቻ የሚነገሩ ናቸው። በቋንቋዎች ብዛት የበላይነቱን የያዘው በሩስያ የሚገኘው የዳግስታን ሪፐብሊክ ሲሆን 30 የሚያክሉ ጎሳዎች ይኖሩበታል። በእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ያለው መወራረስ እንዲሁም ከሌሎች የቋንቋ ቡድኖች ጋር ያላቸው ዝምድና እስካሁን ድረስ በውል አይታወቅም።
(ጄደብሊው ዶትኦርግ)
*********
ፈላስፋዎቹ እንዲህ አሉ
- አንዱን ሰው ማን ገሰፀህ ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም መልሶ የሰነፎችን ስንፍና አይቼ ራቅሁ ከዚህም የተነሳ ተገሰጽኩ አለ፡፡
- ዲዮጋንስ አንድ ሰነፍ ሰው በደንጊያ ላይ ተቀምጦ አየና፣ ደንጊያው በደንጊያ ላይ ተቀምጧል አለ፡፡
- አፍላጦንን ሰው ጠላቱን በምን መንገድ ሊበቀለው ይችላል ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም አብዝቶ ጥሩ ነገር ያደረጉለት እንደሆነ ነው ብሎ መለሰ፡፡
- ከጠቢባን አንዱን እንዲህ ብለው ጠየቁት፣ የሚጠቅምና የሚያስተክዝ ሥራ ምንድነው፡፡ እሱም የክፉ ሰዎች ሞት ነው ብሎ መለሰ፡፡
- ዲዮጋንስን ሞት እንዴት ናት ብለው ጠየቁት፡፡ እሱም ሀብታሞችን የምታስደነግጥ በድሆች ዘንድ ግን የምትፈለግ ናት አላቸው፡፡
- ዲዮጋንስ አንድ መልከ መልካም ሰው ሲዋሽ አየው፤ እሱም ቤቱ ያማረ ሆኖ የሚኖርበት ግን ክፉ ነው አለ፡፡
- አንድ አዋቂ ወደ ሌላ አዋቂ መኖሪያ ሄዶ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ብቻህን ስትኖር እንዴት አይሰለችህም አለው፡፡ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ እኔ እኮ ብቻዬን አይደለሁም፡፡ ከብዙ አዋቂ ሰዎች ጋር ነኝ ከእነሱም ጋር እነጋገራለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ እጁን ዘርግቶ ካጠገቡ ብዙ መጻሕፍት አወጣና ይህ ጋሊኖስ ሕያው ነው፡፡ አብቅራጥም ይገስጻል፡፡ ሶቅራጥም ያስተምራል፡፡ አፍላጦንም ይናገራል፡፡ አርስጣጣሊስ ምሳሌ ይመስላል፡፡ ሕርምስም ምላሽ ይሰጣል፡፡ ፎርፎርዬስ ይመክራል፡፡ ጐርጐርዮስ ይናገራል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ከፈለኩት ከእኔ ጋር ይጫወታል አለው፡፡
አንጋረ ፈላስፋ
የበሬው ጥጃ
አንበሳና ነበር አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንበሳው በሬ ሲገዛ ነብሩ ላም ይገዛና ከጊዜ በኋላ የነብሩ ላም ጥጃ ወለደች፡፡ ሆኖም አንበሳው ጥጃው የእኔ በሬ ጥጃ ነው በማለት ሲከራከር ነብሩ ጥጃው የእርሱ ላም የወለደችው መሆኑንና በሬ ጥጃ መውለድ እንደማይችል ሊያስረዳው ቢሞክርም አሻፈረኝ አለ፡፡
በመቀጠልም አንበሳው በጉልበቱ ተማምኖ “ጥጃው የእኔ በሬ ጥጃ ነው፡፡ ይህንን ማንም የሚስማማበት ነው፡፡ በሬ ጥጃ ሊወልድ ይችላል፤” በማለት መከራከር ያዘ፡፡
ነብሩም “እንግዲያው እነዚህ ምስክር የሚሆኑትን ሰዎች ልሰማቸው እፈልጋለሁና እነርሱም በሬ ጥጃ ይወልዳል ብለው ከመሰከሩ ጥጃውን ልትወስደው ትችላለህ፤” አለው፡፡
እናም የዱር እንስሳቱ ሁሉ ተሰበሰቡ፡፡ ጥንቸል ግን በጣም ጠንካራ፣ ሹልና እንደጦር የሰላ ሆኖ ከስሩ ጥንቸል ሊደብቅ እንዲችል ተደርጎ የተቦረቦረ ችካል ስታዘጋጅ ስለነበረ ከስፍራው አልገተኘችም ነበር፡፡ ይህንን የሚያዘጋጅላት ጓደኛዋ ስለነበረ ይህ ተዘጋጅቶ እስኪያልቅ መጠበቅ ነበረባት፡፡
በመጨረሻም ከስብሰባው ቦታ ስትደርስ “ይህን ሁሉ ጊዜ የት ነበርሽ?” ብሎ አንበሳው አፈጠጠባት፡፡ “ለምንድነው ያረፈድሽው?” ብሎም ጮኸባት፡፡
ጥንቸሏም “የአባቴ ረግረግ ቦታ ላይ የተነሳውን እሳት ሳጠፋ ቆይቼ ነው፤” ብላ መለሰች፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው “ደም ያስቀምጥሽና! አባትሽ ምንም መሬት የለውም፤ ቢኖረውም እንኳ ረግረጋማ ቦታ ላይ እሳት ሊነሳ አይችልም፡፡ ለምንድነው የምትዋሺው?” አላት፡፡
እርሷም “እንግዲያውማ በሬ እንዴት ጥጃ ይወልዳል? አንተ ራስህ አጭበርባሪ ነህ፣ በጉልበትህ ብቻ የምትመካ!” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው በጣም ተበሳጭቶ በመዳፉ ጥንቸሏን ሊመታት ሲሞክር ጥንቸሏ ከችካሉ ስር ወዳለው ጉድጓድ ዘላ ገብታ ተደበቀች፡፡ የአንበሳው መዳፍ ከጉድጓዱ ውስጥ ሲገባ እንደሚታወቀው የአንበሳ ጉልበት ያለው ከመዳፉ ላይ ነውና ጥንቸሏን ያገኛት መስሎት መዳፉ ችካሉ ላይ ስለተቀረቀረ ደሙ በየቦታው መፍሰስ ጀመረ፡፡
ደሙንም ከመዳፉ ላይ ይልስ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ የዱር እንስሳቱ በሙሉ አምላክ በአንበሳው ላይ እንደፈረደበት አወቁ፡፡ ፍርዱም የአንበሳ የጥንካሬ ተምሳሌት የሆነው መዳፉ ላይ ስላረፈ ጥጃው የነብሩ እንደሆነ ተስማሙ፡፡
እንስሳቱም “ሙሉ ቀን በአንበሳው ጥንካሬና ኃይል ፍራቻ ምክንያት በሐሰት ለመመስከር እዚህ ዋልን፡፡ ነገር ግን ጥንቸሏ መልካም ነገርን አደረገች፡፡ እውነቱንም ነገረችን፡፡ አሁን በነፃነት ወደየመጣንበት መመለስ የምንችል ሲሆን፣ ከዛሬ ጀምሮ አንበሳው ሳይሆን የእንስሳት ሁሉ ንግሥት ጥንቸሏ ናት፤” ብለው ተስማሙ፡፡
በባህላችንም የእንስሳት ንጉሥ ጥንቸል ነው፡፡
- በመተኪያ ሊብሪ የተተረከ የአሪ ብሔረሰብ ተረት