Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሻራ ለማኖር

አሻራ ለማኖር

ቀን:

ተወልዶ ያደገው፣ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለውና በሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ የሠለጠነው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ከሥልጠናውም በኋላ መርካቶ አካባቢ በቴክኒሽያንነት ሠርቷል፡፡ በመቀጠልም በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በረዳት ካሜራ ሠራተኛነት ለስድስት ዓመታት ያህል አገልግሏል፡፡ በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ወቅት በባድመና በፆርና ግምባሮች በተካሄዱ ዐውደ ውጊያዎች በሙያው ተሠልፏል፡፡

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሉክሰምበርጋዊ የሆነው ወጣት ዓለማየሁ ወርቁ፣ ከአንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆቹ ጋር ወደ ሉክሰምበርግ ካቀና 14 ዓመት ሆኖታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሉክሰምበርግ በሚገኝ የስዊድን ኤሌክትሮኒክስ ካምፓኒ ውስጥ በኤሌክትሪሽያንነት እየሠራ ነው፡፡

ዓለማየሁ በሚኖርበት ሉክሰምበርግ ከአራት ወራት በፊት ኢንተርኔት ከፍቶ ሲዳስስ ዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣን ያገኛል፡፡ በድረ ገጹ ከሠፈሩት መረጃዎች መካከል በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ችግረኛና ከደሃ ደሃ ቤተሰብ የወጡ ልጆች በባዶ ሆዳቸው እየተማሩ መሆኑን የሚጠቅስ ይገኝበታል፡፡ ምግብ የማግኘት ችግር ያለባቸውን ልጆች ከሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የተማረበት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሚገኘው የብርሃንህ ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡

ዓለማየሁ ይህ ዓይነቱን መረጃ ካነበበ በኋላ መንግሥት ሁሉን ነገር አድርጐ እንደማይዘልቅ፣ በዚህም የዜጐች ተሳትፎና እገዛ ሊቸረው እንደሚገባና እሱም አንዱ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት በወቅቱ እንደወሰነ ይናገራል፡፡ ‹‹እንደ ግለሰብ ምን ማድረግ አለብኝ የሚል ጥያቄ በውስጤ ተጫረ፤›› የሚለው ዓለማየሁ ባለበት አገር ሆኖ ገንዘብ ወደ ማሰባሰቡ ሥራ ተሰማራ፡፡

ልጆቹ ከትምህርት ቤታቸው፣ አባትየው ደግሞ ከሚሠራበት ኩባንያ ከሥራ ባልደረቦቹና በቅርብ ከሚያውቃቸው ጓደኞቹ ያሰባሰቡትን 1,700 ዩሮ (40,000 ብር) ወደ አገር ቤት ይዞ መጣ፡፡ በብርሃንህ ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ 30 የአፀደ ሕፃናት፣ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚማሩ 173 ችግረኛ ተማሪዎች የምግብ፣ የዩኒፎርምና የትምህርት መሣሪያዎች እገዛ አድርጓል፡፡ የችግሩ መጠን በስፋት ለተንሰራፋባቸውና ወደ 20 ለሚጠጉ ተማሪዎች ወላጆችም በነፍስ ወከፍ 400 ብር ለግሷል፡፡

ልገሳው የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አለመሆኑን የተናገረው ዓለማየሁ በሚኖርበት አገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በድህነት ላይ ለመዝመት፣ በመማር ማስተማሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ የበኩሉን አሻራ ለማኖር ቆርጦ መነሳቱን አስታውቋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኘው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት (መዋለ ሕፃናት) ርዕሰ መምህር አቶ ግርማ ዳባ እንደሚገልጹት፣ በመዋለ ሕፃናቱ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ በአካባቢው በላስቲክ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ቤተሰቦች የወጡ ናቸው፡፡ እኩሉ ደግሞ ከአጐትና አክስቶቻቸው ጋር ተጠግተው የሚኖሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በዘመድ አማካይነት ከገጠር መጥተው አድካሚ ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ