ተስፋዬ የማነህ የሲኖትራክ አሽከርካሪ ሲሆን፣ የአሽከርካሪነት ሙያ የጀመረው ደግሞ በ18 ዓመቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የቤት መኪና፣ ታክሲ፣ ኮብራ፣ አይሱዙና የከተማ አውቶቡስ አሽከርክሯል፡፡
የመንጃ ፈቃዱን ያወጣው አዲሱ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት እንደሆነ የሚናገረው ተስፋዬ፣ ሲኖትራክ ማሽከርከር የጀመረው በአራተኛ መንጃ ፈቃድ ነበር፡፡ ‹‹2002 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነበር ሲኖትራክ የያዝኩት፡፡ በወቅቱ ያስቸገሩኝ አንዳንድ ቴክኒካል ነገሮች ነበሩ፡፡ በተለይም ማርሽ ማስገባት ከብዶኝ ነበር፡፡ የሲኖትራክ ማርሽ እንደ ሌሎቹ ተሽከርካሪዎች ቀላል አይደለም፡፡ ብልሃት አለው፤›› ይላል፡፡
እንደ እሱ ገለጻ፣ መሰል ክስተቶች በማንኛውም አዲስ ብራንድ ተሽከርካሪ ላይ የሚስተዋሉ ሲሆን፣ በጊዜ ሒደት ከተሽከርካሪው ጋር በመለማመድ ይቀረፋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥንቃቄ ጉድለት በርካታ አደጋዎች በሲኖትራክ እየደረሰ መሆኑን ይናገራል፡፡
‹‹አብዛኞቹ የሲኖትራክ ሾፌሮች ወጣቶች ናቸው፤›› የሚለው ተስፋዬ አሽከርካሪዎቹ አዲሱን መንጃ ፈቃድ የያዙ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ በሥራው በቂ ልምድ ሳያካብቱ ከባድ ተሽከርካሪ መያዝ ለአደጋ ያጋልጣል ይላል፡፡
‹‹እኔ መንጃ ፈቃድ ባወጣሁበት ጊዜ የፈቃድ አሰጣጡ ሒደት በየሁለት ዓመቱ በመሆኑ በቂ ልምድ ማካበት ችያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ፈቃድ የሚያገኙት ወጣቶች በቀጥታ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ በመሆኑ ልምድ ሳይኖራቸው አሽከርካሪ ይሆናሉ፤›› በማለት ይናገራል፡፡
ሲኖትራክ ምቹና ከሌሎቹ ተሽከርካሪዎች በተለየ ፈጣን ነው፡፡ አሽከርካሪው ፍጥነቱን ለማየት ካልሞከረ የቱን ያህል እየፈጠነ እንደሆነ ስለማይታወቀው አደጋ ይፈጠራል፣ የገልባጭ ሲኖትራክ አሽከርካሪዎች ብዙ ጊዜ ከሚፈቀደው ቶን በላይ በመጫን አደጋ ውስጥ ይገባሉ ይላል፡፡ ‹‹ተሽከርካሪው ከሚችለው በላይ ሲጭን ፍሬን መያዝ ያስቸግራል፡፡ እንደ ሲኖትራክ ባሉ ፈጣን ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ እየበረሩ መጥቶ ድንገት ፍሬን መያዝ የመገልበጥ ዕድሉን ከሌሎቹ ከፍ ያደርገዋል፡፡››
ያለዕረፍት ማሽከርከር ሌላው ችግር ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ አሽከርካሪዎች ቀንም ሌሊትም ያሽከረክራሉ፡፡ ድካምና እንቅልፍ ስለሚጫጫናቸውም ብዙ ጊዜ አደጋ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተስፋዬ ቀን በመደበኛ ደመወዙ ሥራውን ሚያከናውን ሲሆን፣ አልፎ አልፎ አበል ተከፍሎት በማታው ክፍለ ጊዜ እንደሚያሽከረክር ይናገራል፡፡ ነገር ግን አድካሚ በመሆኑ ብዙም አይዳፈረውም፡፡ በሌሊት ጉዞ የሚደርሰው አደጋም ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡
ሌላው ባለንብረቶች ጋር የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ ብዙዎቹ ባለንብረቶች አዲስ መንጃ ፈቃድ ያላቸውን አሽከርካሪዎች ይመርጣሉ፡፡ ‹‹ሲቀጥሩ ወጣት፣ ትዳር የሌላቸው የትም ቦታ ሲታዘዙ መሄድ የሚችሉ ብለው ነው የሚቀጥሩት፤›› በማለት በባለንብረቶቹ ኃላፊነት የጐደለው ተግባር ልምድ የሌላቸው ወጣቶች የሚቀጠሩበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻል፡፡ ይህም ለአደጋው መባባስ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
የአደጋው መበራከት በኅብረተሰቡ ዘንድ ያሳደረው የሥነ ልቦና ጫና ቀላል አይባልም፡፡ በተለይም በሌሎች መኪና አሽከርካሪዎች ላይ ያለው ጫና ከባድ ነው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ካህሳዬ በግል መኪናቸው ሲንቀሳቀሱ በሰላም ስለመመለሳቸው ሥጋት አላቸው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሲኖትራክ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹ሲኖትራክ ከሩቁ ሳይ ቶሎ ብዬ መንገድ እለቃለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ብዙ ጊዜም በዳገታማና ቁልቁለታማ መንገዶች ላይ ሲያጋጥማቸው ጭንቀታቸው ያይላል፡፡ ‹‹አደባባይ ላይ እንዲያልፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ቀድሞ አደባባይ ውስጥ ለገባ ተሽከርካሪ ቢሆንም መብታችንን አሳልፈን ለሲኖትራክ አሽከርካሪ እንሰጣቸዋለን፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው የሚያደርሱትን አደጋ እያየን ቅድሚያ ይሰጡናል ብለን ማመን ይቸግረናል፤›› ይላሉ፡፡
ተሽከርካሪዎቹ ቀላል በመሆናቸው ፍጥነታቸውን መቆጣጠር እንደሚከብድ የሚናሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ በፈጣን መንገዶች ላይ እንኳን ከሚፈቀደው ፍጥነት በላይ በማሽከርከር አደጋዎች እንደሚከሰቱ ይናገራሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ሲኖትራኮች ትራፊክ በማይጨናነቅበት በማታው ክፍለ ጊዜ ቢሠሩ ይመክራሉ፡፡ በወጣትነት ሲኖትራክ ማሽከርከርም ከባድ እንደሆነ በማመን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1956 በቻይና የከባድ ተሽከርካሪ አምራች ሆኖ ሥራ የጀመረው ሲኖትራክ፣ ዛሬ የዓለም ገበያ ላይ ለሽያጭ ከሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አገሮች ወደ አገራቸው ማስገባት ከጀመሩም ሰነባብተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም የኮንስትራክሽን ሥራዎች በተበራከቱበት ሁኔታ የሲኖትራክ የሥራ ድርሻ ላቅ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ከጥቅሙ ጐን ለጐን የሚያደርሰው አደጋም ያን ያህል ነው፡፡ አሽከርካሪዎቹ በሚያደርሱት በርካታ አደጋዎችም በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹‹ቀይሽብር›› የሚል ስያሜ አትርፏል፡፡ የተሽከርካሪዎቹ ቁጥር ከሌሎቹ አንፃር ዝቅተኛ ቢሆንም የሚደርሰው የአደጋ ብዛት የትየሌለ ሆኗል፡፡ በማኅበራዊ ድረገጾችም በኢትዮጵያ ሲኖትራክ የተነፃፀረው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት ከተፈረጀውና ሰዎችን በመቅላት ከሚታወቀው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አይኤስ ጋር ነው፡፡
ከደረሱት አደጋዎች ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲሱ አዳማ ፈጣን (ኤክስፕረስ) ጐዳና ላይ የደረሰውን አደጋ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አደጋው 11 ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን፣ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ሥራ ባልጀመረውና በከተማው በተዘረጋ ቀላል የባቡር ፕሮጀክት ላይ አደጋ ካደረሱ አሽከርካሪዎች ሲኖትራክ አብላጫውን ሥፍራ ይይዛል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ተሽከርካሪዎቹ ቁጥራቸው ከሌሎቹ ተሽከርካሪዎች አነስተኛ ቢሆንም እንቅስቃሴያቸው ብዙ ነው፡፡ በኮሚሽኑ መረጃ አያያዝ ሥርዓት አደጋዎች ሲመዘገቡ በተሽከርካሪው ልዩ ስም ሳይሆን፣ በወጣለት ምድብ ቢሆንም አብላጫው አደጋ የሚደርሰው በሲኖትራክ አሽከርካሪዎች መሆኑን ያምናሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ 9970 አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፣ የጭነት መጠናቸው ከ41 እስክ 100 ኩንታል በሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ያይላል፡፡ በአደጋ አድራሽነታቸውም በስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች መካከል ሲኖትራክ አንዱ ነው፡፡ የሲኖትራክ አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ጊዜ አደጋ በማድረስ የአደጋውን ቁጥር እንዳበዛዙት ይናገራሉ፡፡
‹‹ለምሳሌ በመገንባት ላይ በሚገኘው የባቡር መንገድ ላይ አደጋ ካደረሱ ተሽከርካሪዎች መካከል ሦስቱ ሲኖትራኮች ናቸው፡፡ እንዲሁም በአዲስ አዳማ መንገዶች አሰቃቂውን አደጋ ያደረሰው የሲኖትራክ አሽከርካሪ ነው፡፡ በከተማ ውስጥም እኔን ጨምሮ በብዙ ሰዎች ላይ አደጋ ደርሷል፡፡ ከከተማ ውጪም እንደዚሁ በርካታ አደጋዎችን በመፍጠር ቀዳሚ ሆኗል፤›› የሚሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ በተሽከርካሪዎች መካከል በሚፈጠር ግጭትም የሲኖትራክ አሽከርካሪዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡
በፍጥነት ማሽከርከር፣ የብቃት ማነስ፣ ከተሽከርካሪው ጋር አለመለማመድ በብዛት የሚስተዋሉ የአደጋው መንስኤዎች ናቸው፡፡ ‹‹በቴክኒክ ጉድለት ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎች የሉም ማለት ባይቻልም፣ ብዙዎቹ አደጋዎች የሚከሰቱት በአሽከርካሪዎች ባህሪ ነው፡፡ ፍሬን አስቸግሯቸው አደጋ የፈጠሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
አንድ አሽከርካሪ በቀን ከ8 ሰዓት በላይ መሥራት አይችልም፡፡ እንዲሁም በየ4 ሰዓቱ ዕረፍት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን ምን ያህል አረፉ ምን ያህል ሠሩ የሚለውን ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙዎቹም አደጋዎች የሚደርሱት በድካምና በእንቅልፍ ልብ ስለሚነዱ ነው፡፡
በመንግሥት በኩል አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን፣ ፖሊስ ኮሚሽንና መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ በመሆን የመንቀሳቀሻ ሰዓት መገደብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡን አውጥተው ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ጠዋት በሥራ መግቢያ ሰዓትና ከሰዓት ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል፡፡ በመሆኑም ጥቂት የማይባሉ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዙን አክብረው አደጋውን ለመቀነስ ቢቻልም አንዳንድ ሰርጐ ገቦች እንደሚያስቸግሯቸው ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ መድረኮችም ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቁጥጥሩን ዘመናዊ በማድረግ አደጋዎችን መቆጣጠር ይቻላል የሚሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ፣ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የሚመለከታቸው አካላት ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ አቤልነህ አግደው በትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሒደት ኃላፊ ናቸው፡፡ ‹‹በተሽከርካሪ አደጋ ንብረትና የሰው ልጅ ሕይወት እናጣለን፤›› የሚሉት አቶ አቤልነህ፣ አደጋውን መከላከል የሁሉም ኃላፊነት ነው፣ ስለዚህም የክልልና የከተማ ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ ፀጥታ አስከባሪዎች የፍትሕ አካላት የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማትን ኅብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አደጋዎች እየደረሱ ያሉት ከተሽከርካሪው የቴክኒክ ችግር አልያም ደግሞ በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ አይደለም፡፡ ‹‹መኪናውን የምንገዛው ከዓለም ገበያ ነው፡፡ ሌሎችም አገሮች መኪናውን ይገዛሉ፡፡ አደጋ ደረሰ ሲባል የሚሰማው ግን እዚህ ብቻ ነው፡፡ ለዓመታት ያለምንም አደጋ ያሽከረከሩ ሰዎች አሉ፡፡ የቴክኒክ ችግር ቢሆን የአንዱ መኪና ደህና ሆኖ የሌላው መኪና ችግር የሚኖርበት አጋጣሚ አይኖርም፤›› ይላሉ፡፡ እስካሁን ያለው የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያሳየውም ከቴክኒክ ችግር ሳይሆን በአሽከርካሪው የባህሪ ችግር መሆኑን ነው፡፡
አቶ አቤልነህ እንደሚሉት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ለሚነሳው ቅሬታም ብዙ የዓለም አገሮች የሚጠቀሙበትን የመንጃ ፈቃድ ደብተር አሰጣጥ ነው፡፡ አሠራሩ በሌላው ዓለም የፈጠረው ችግር ከኢትዮጵያ ሲነፃፀር ኢምንት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ችግር የብቃት ነው፡፡ ባለንብረቶች ብቃት ያላቸውን ሰዎች መቅጠር አለባቸው፡፡ አለዚያ ግን ወጣቶች ኃላፊነት መሸከም አይችሉም ወደሚል አንድምታ ያመራል፡፡
‹‹እየተፈጠረ ያለው አደጋ የአገርን ገጽታ ያበላሻልና ችግሩ የት ጋ ነው ያለው የሚለውን ለማየት የዳሰሳ ጥናት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ አቤልነህ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ችግር የለበትም ቢሉም፣ ባለንብረቶች ግን ብቃት ያላቸውን መቅጠር አለባቸው ብለዋል፡፡ ሆኖም የትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአንድ አሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ሥልጠናውን በብቃት ጨርሷል ሲል ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ካነጋገርናቸው መካከል አሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ባለሥልጣኑ ዞር ብሎ ሥልጠናውንም ሆነ መንጃ ፈቃድ አሰጣጡን ሊፈትሽ ይገባል ይላሉ፡፡ በቀደሙት ጊዜያት 18 ዓመት ሞልቶት ሁለተኛ መንጃ ፈቃድ ያወጣ ግለሰብ ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ሁለት ዓመት እየሾፈረም ይሁን አይሁን ይጠብቃል፡፡ ሦስተኛ ከያዘ በኋላ አራተኛ ለማውጣት እንደገና ሁለት ዓመት ይጠብቃል፡፡ አሽከርካሪው በየመንጃ ፈቃዱ አንድ ደረጃ በጨመረ ቁጥር የሁለት ዓመት ጊዜ ከመጠበቁም በላይ በእርከኑ የጽሑፍም የተግባርም ፈተና ይወስዳል፡፡ ከሁለተኛ መንጃ ፈቃድ ጀምሮ ያሽከረክራል ተብሎ ከሚታመነውና፣ ያገኛል ከሚባለው ልምድ በተጨማሪ በዕድሜ መብሰል፣ ኃላፊነት መውሰድ ተጨማሪ ልምዶችን እንዲያካብት ያደርጉታል፡፡ አሁን ይህ የለም፡፡
እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ አገላለጽ፣ የ18 ዓመት ወጣት ኃላፊነት አይሸከምም የሚል ድምዳሜ ላይ ባያደርስም ማንም ወጣት ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ሲይዝ ዓለምን እንደተቆጣጠረ ያህል በሙሉ ልብ መኪናውን ከሚፈለገው በላይ አይነዳውም፣ እያንዳንዷን ነገር ለመሞከር አይደፍርም ብሎ መገመት ግን አይቻልም፡፡ በመሆኑም አዲሱ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ክለሳ ሊደረግበት ይገባል፡፡
ሥልጠናው እንዳለ ይቀጥል ብሎ ከታመነበት ደግሞ ቢያንስ ከባድ መኪና የሚያሽከረክሩ ዕድሜ ከ21 ዓመት በላይ እንዲሆን፣ 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁና ስለመኪናው ባህሪ አንብበው መረዳት የሚችሉ እንዲሆኑ፣ ኮድ 3 ላይ የሚሠሩ ማለትም ንግድ የሚሠራ መኪና ከሌላው በተለየ ሌላ መስፈርት ሊወጣላቸውም ይገባል፡፡ ልምድ፣ ዕድሜ፣ ትምህርት መስፈርቶች ውስጥ መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚወስዱት ሁሉ፣ የመኪና አሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ በገለልተኛ ወገን እንዲሰጣቸው ቢደረግ ችግሩ እየተቀረፈ ሊሄድ ይችላል፡፡ ይህ በሕገወጥ መንገድ ሕጋዊ ያልሆነ መንጃ ፈቃድ አላቸው የሚባሉትንም ከመስመር ያስወጣል፡፡