መቼም ቢሆን የማይታክተውና ተስፋ የማይቆርጠው የእግር ኳሱ ቤተሰብ ‹‹አንድ ቀን ይሳካል›› በሚል የማይናወጥ አቋሙ በኢትዮጵያ እግር ኳስ መፃኢ ዕድል ላይ እምነቱ የፀና ይመስላል፡፡ ይሁንና ይህን እምነቱን ነፍስ የሚዘራበት ሁኔታ ግን ገና የተፈጠረ አይመስልም፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ራሷ በመሠረተችው አህጉራዊ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ብቅ ብላ የሚሊዮኖችን ልብ ያስፈነጠዘችው አገር፣ በዚያው የውኃ ሽታ ሆና ላለመቅረቷ ምንም ማረጋገጫ አለማሳየቷ ጥሩ ማሳያ ይመስላል፡፡
ተስፋውን አሟጦ መጣል ያልቻለውና በእግር ኳሱ ፍቅር ያበደው ተመልካች ግን አንዳች ተአምር ተፈጥሮ እግር ኳሱ በቋሚነት የሚያድግበትን ዕለት በትዕግሥት ከመጠባበቅ አልቦዘነም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ወሳኙን ሚና የሚጫወተው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ቢሆን ይህንን የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳምጦ ጥሙን የሚቆርጥለትን ሁኔታ ለመፍጠር ትጋት እያሳየ አይመስልም፡፡ ይሁንና በአሠልጣኝ ቅያሬ ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ የሚመስለው የፌዴሬሽኑ ጥረት ከንቱ ሆኖ አለመቅረቱን ማንም ሰው እርግጠኛ ሆኖ ሊናገረው አይችልም፡፡
ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በማይዘነጋው መልኩ ደምቆ በታየበት የአፍሪካ ዋንጫው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከመንግሥቱ ወርቁ በመቀጠል ተሳትፎውን እውን ያደረጉ መሆናቸውን ተከትሎ በእሳቸው ላይ የተንጠለጠለው ተስፋ ሩቅ የሚያስጉዝ መስሎ ነበር፡፡ ይሁንና በዓለም ዋንጫው ማጣሪያና አፍሪካ ውስጥ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የቻን ውድድር ብሔራዊ ቡድኑ ያሳየው ደካማ አቋም ከግምት ገብቶ በአሠልጣኙ የተለኮሰውን የማነቃቂያ ችቦ የበለጠ እንዲያበራ በማሰብ በከፍተኛ የደመወዝ መጠን አዲስ የውጭ አገር አሠልጣኝ ሊቀመጥበት ግድ ሆነ፡፡
ከዚህ ቀደም በዓለም የወጣቶች የዓለም ዋንጫ ታሪክ ሠሪ የነበሩትን ፈረንሣዊውን አሠልጣኝ ዲያጎ ጋርዚያቶን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ አሠልጣኞች በተፎካከሩበት የዋሊያዎቹን የአሠልጣኝነት መንበርን የመቆናጠጥ ፉክክር ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ አሸናፊ ሆነው ተቀመጡበት፡፡ ሚያዝያ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. የፖርቱጋላዊው ቅጥር ይፋ ሆነ፡፡ በአሠልጣኝነት ሹም ሽረቱና ምርጫም ላይ በርካታ አስተያየቶች ቢሰጡም የፌዴሬሽኑን ውሳኔ በፀጋ ተቀብሎ ስኬቱንም ሆነ ውድቀቱን በጊዜ ሒደት ለመገምገም በሚል ብዙኃኑ የስፖርት ቤተሰብ በዝምታ ቆየ፡፡
አንድ ዓመት ሊሞላቸው የወር ዕድሜ የቀራቸው ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ በሕዝቡ ምልከታ ሊመዘኑ የሚገባቸው ወሳኝ ወቅት ላይ ደረሱ፡፡ እስካሁን ወደ ስድስት ሚሊዮን ብር የደመወዝ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው የሚነገርላቸው አሠልጣኝ ባሬቶ፣ አገሪቱን በእግር ኳሱ ዓለም ስኬታማ ለማድረግ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግና በርካታ መሠረታዊ ሥራዎች መከናወን እንደሚገባቸው ቢገልጹም፣ ብዙኃኑ የእግር ኳሱ ቤተሰብ በሰፊ ሀብትና በተጨዋቾች ስብስብ አሠልጣኝ ሰውነት የተጓዙበትን ርቀት መጓዝ ባቃታቸው ማሪያኖ ባሬቶ ላይ ጣታቸውን መቀሰር ጀምረዋል፡፡ በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በለጋ ወጣቶችና ልምድ ባላካበቱ ወጣቶች በተገነባው የሱዳን ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ መሸነፉና ከማጣሪያው ውጪ መሆኑ በአሠልጣኙ ላይ የነበረው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ መረጋጋት የተሳነው የሚመስለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት አሠልጣኙን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ የተነጋገረበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጾ፣ በአፈጻጸም ሪፖርቶችና ሙያዊ ግምገማዎች ላይ በመመሥረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሚከተለውን አቅጣጫ በተመለከተ ተገቢ መረጃዎችን እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል፡፡
በአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎችና የእግር ኳሱ ቤተሰቦች ሙያዊው ግምገማ በአሠልጣኙ ላይ ብቻ መተግበር እንደሌለበት፣ ራሱ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ያከናወነው ጠንካራና ደካማ ጎን፣ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ በተለያየ ደረጃ የተዋቀሩ ንኡሳን ኮሚቴዎች ማለትም የውድድርና ሥነ ሥርዓት፣ የዳኞች፣ ብሔራዊ ቴክኒክ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴዎችና በዋናነት የእግር ኳሱ ሞተር ተብሎ የሚጠራው ቴክኒክ ዲፓርትመንት ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በግምገማው ሊያይ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡
ከነዚህ አስተያየት ሰጭዎች ውስጥ የቀድሞ ኤሌክትሪክ ክለብ ቡድን መሪ አቶ ገበየሁ ተወልደ መድኅን፣ ‹‹የምናወራው የአገሪቱን እግር ኳስ ለመለወጥ ከሆነ አሠልጣኝ መቀያየር ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔው ለቦታው የሚታጩ አመራሮች የተቋሙን ኃላፊነት ሲረከቡ አብሮ ተጠያቂነት ሊካተት ይገባዋል፡፡ ይኼ ባልሆነበት ግን አሠልጣኝ ማሪያኖ ቀርቶ አሁን በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በማሠልጠን ላይ የሚገኙ አሠልጣኞች ዕድሉ ቢሰጣቸው በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የሚፈለገው ለውጥ እንደማይመጣ በእርግጠኝነት መናገር ይችላል፤›› በማለት በፌዴሬሽኑ ሥር ሰዶ ያለው ችግር ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የውጤቱን ቀውስ ተከትሎ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉና ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮችም ይህንኑ ሲያጠናክሩ፣ ‹‹በእርግጥ አሁን ላለው እግር ኳስ አሠልጣኝ ብቻውን ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ከየአቅጣጫው የተቃውሞ መአት እየዘነበባቸው የሚገኙት ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ብቃት እንዳላቸው በፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት ተረጋግጦ ነው ቅጥር የፈጸሙት፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ አሠልጣኙ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ባከናወኑት ጨዋታ ዓይነትና መጠን ምን ዓይነት ጠንካራና ደካማ ጎን እንደነበራቸው ተገምግመው አያውቁም፡፡ ይኼው አካል የአሠልጣኙን ገፀ ሰብ (ፕሮፋይል) መርምሮ ለዚህ ኃላፊነት ያበቃ በመሆኑ ምክንያት ያደረጓቸውን ጨዋታዎች አሠልጣኙ ባሉበት ገምግሞ አያውቅም፡፡ ይኼ ተደጋግሞ ሲነገር የቆየ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱ አባላት ዛሬ በሠሩት ሥራ ሊጠየቁ ካልቻሉ ነገ ሌላ አሠልጣኝ ይምጣ ቢባል ተመሳሳይ የቃላት ጨዋታን ላለመጠቀማቸው ምንም ዓይነት ዋስትና ስለሌለ፤ እንደ አሠልጣኙ ሁሉ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው አቅምና ብቃትም መገምገምና መታየት ይገባዋል፤›› ይላሉ፡፡
በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ አሠልጣኙ በወቅቱና በጊዜው ቢቻል ያደረጓቸውን ሁሉንም ጨዋታ ካልተቻለ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ያደረጓቸውን ወሳኝ ጨዋታዎች መገምገም ይገባ እንደነበር ገልጸው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሠልጣኙን በተመለከተ ይፋ ስላደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ይዘት ግን የሚያክሉት የተለየ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አሠልጣኝ ማሪያ ባሬቶ እንደተባለው በየጨዋታው ተገምግመው ቢሆን ኖሮ ለውሳኔው መጓተት ወይም መዘግየት ችግር ውስጥ ባልተገባ ነበር የሚል የግል አመለካከት እንዳላቸው ግን አልሸሸጉም፡፡
ከፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ይልቅ ጉዳዩን በዝርዝር ያስረዳሉ በሚል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝን ነው፡፡ ሆኖም ኃላፊው ፌዴሬሸኑ አዲስ እየተከተለ ባለው አሠራር መረጃዎች በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ካልሆነ በሚል ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሠራሩን እንዲፈትሽ ከሚተችባቸው ነጥቦች ውስጥ ጽሕፈት ቤቱና የቴክኒክ ዲፓርትመንቱ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀርበው ደግሞ ቅዳሜ መጋቢት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) የካሜሮን አቻቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳሉ፡፡ ጨዋታው በኮንጎ ብራዛቢል አስተናጋጅነት ለሚከናወነው መላው አፍሪካ ጨዋታዎቸ ማጣሪያ ሲሆን፣ ለዚሁ ተብሎ ሉሲዎቹም ዝግጅት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ይሁንና የሉሲዎቹ አሠልጣኝ በኃይሏ ዘለቀ የዋና አሠልጣኝነት ኃላፊነቱን ከተረከቡ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸውና የኮንትራት ጊዜያቸውን በተመለከተ ግን ይህን አስተያየት እስከሰጡበት ድረስ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ እንደ አሠራር ግን ይህ ኃላፊነት በዋናነት የጽሕፈት ቤቱ መሆኑ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ሳይቀር የሚያምኑበት ነው፡፡ ሆኖም ግን ፌዴሬሽኑ ለአሠልጣኟ የሦስት ወር ኮንትራትና በወር 50,000 ብር ለመቅጠር ሐሳብ እንዳለው የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሠልጣኟ በዋና አሠልጣኝነት የሚያቆያቸው ኮንትራት ሳይፈጸምላቸው መቆየቱን አምነው፣ ጉዳዩ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀርቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ያገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይም የፌዴሬሽኑን ጽሕፈት ቤት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ስለአገሪቱ እግር ኳስ የውጤት ቀውስ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ለቡድኑ ውጤት ችግሩ እሳቸው ብቻ እንዳልሆኑ የሚገልጹት ዋና አሠልጣኙ፣ ‹‹እኔን ጨምሮ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው አገሪቱ ትልቅ ሕዝብ የሚኖርባት አገር ነች፡፡ የትልቅነቱን ያህል እግር ኳሱ ላይ የተሠራ ሥራ የለም፡፡ እንመልከት፤ በአገሪቱ ከትልልቆቹ ቡድኖች ጀምሮ እስከታችኞቹ ድረስ በረኞችን ጨምሮ ለጨዋታ ዕድል የሚሰጠው ለውጪ ተጨዋቾች ነው፡፡ በዚህ ላይ እኔ ወጣት ናቸው ብዬ የምመርጣቸው ተጨዋቾች ብዙዎቹ በክለቦቻቸው ተጠባባቂ ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ተብሎ ነው የአገሪቱ እግር ኳስ እንዲያድግ የሚጠበቀው፤›› በማለት በእሳቸውና በተጨዋቾቹ ላይ እየተደመጠ ያለውን ትችት ይቃወማሉ፡፡
መፍትሔው ለሚለው አሠልጣኙ፣ ‹‹ብሔራዊ ቡድን ወጣቱም ሆነ ዋናው ቡድን ኢንተርናሽናል ልምድ እንዲያገኝ ተደጋጋሚ የወዳጅነት ጨዋታዎች ያስፈልጉታል፤›› ብለው፣ ‹‹ለመሆኑ በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተብለው ያየናቸው ታዳጊዎች በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነገር አለ? የለም፤›› ይላሉ፡፡
የአገሪቱ ተጨዋቾች አንድ ተጨዋች ሊያሟላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ተብለው የሚታወቁ ነገሮችን ያሟሉ እንዳልሆኑና ያንን ጭምር ለማምጣት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ የሚያሠለጥኗቸውን ተጨዋቾች ራሳቸው አሠልጣኙ እንዳልመረጧቸው የሚናገሩ አሉ ለሚለው አሠልጣኙ፣ ‹‹ውሸት ነው›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር ነገር መናገር አልፈለጉም፡፡
አሠልጣኙ ሌላው ከሚወቀሱባቸው ምክንያቶች ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኃላፊነት ያስቀመጣቸውን እንደ ቴክኒክ ዲፓርትመንትና ቴክኒክ ኮሚቴ በመሳሰሉት ንኡስ ኮሚቴ ውስጥ ለሚሠሩ ሙያተኞች ክብር የላቸውም የሚለው ይጠቀሳል፡፡ አሠልጣኙ ግን እሳቸውና እየተጠቀሱ ያሉት ሙያተኞች የሥራ ድርሻ የተለያየ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ክብር›› ስለሚገባው ግን በተለይ በቴክኒክ ዲፓርትመንት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ቀርበው ስለዚህ ጉዳይ አውርተዋቸው እንደማያውቁ ነው ያስረዱት፡፡
ይህንኑ የአሠልጣኙን አስተያየት ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች የሚጋሩት አሉ፡፡ እነዚሁ አካላት የእግር ኳስ ሙያ 80 በመቶው የሜዳ ተግባር ሲሆን፣ በፌዴሬሽኑ በተለይም በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ሥራዎች ወረቀት ላይ ካልሆነ መሬት ወርደው በተግባር እንደማይታይ ትዝብታቸውን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን ጉዳይ በተመለከተ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው አሠልጣኙ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ገምግሞ ሪፖርት እንዲያቀርብ መመሪያ እንደተሰጠው ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ታማኝ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡