Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተር‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው››

‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው››

ቀን:

ይህ ጽሑፍ ተሐዝቦችና ማሳሰቢያ ያዘለ እንጂ ጥናታዊ ውጤትን ለሌሎች ለማካፈል ያለመ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የፌዴራል አስፈጻሚ አካል የማንቂያ ደወል እንዲሆን በማሰብ የተጻፈ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሕገ መንግሥት ያስተዋወቀችው በ1923 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሥርዓት የተደራጁ የዘመናዊ ሕጎቿን መድብላት (የፍትሐ ብሔር፣ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የንግድ፣ የባህር እንዲሁም የሥነ ሥርዓት ሕጎቿን) ያዘጋጀችው በ1950ዎቹ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የተጀመረው የሕግ ባለሙያዎችን (ጠበቆችን) የማፍራት ተግባር አነሰም በዛ፣ የጥራት ደረጃውን ጠበቀም አልጠበቀ አዳዲስ በተከፈቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ውስጥ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ‹‹ሠልጥኖ›› የሚወጣው ባለሙያ ገሚሱ በዳኝነትና በዓቃቤ ሕግነት፣ ገሚሱ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ውስጥ በአማካሪነትና ነገረ ፈጅነት፣ ጥቂቱም በሕግ ትምህርት ቤቶች መምህርነት እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሲያገለግል፤ የተቀረው በግሉ በጥብቅና ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሑፍ በግል የጥብቅናና የሕግ ማማከር ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችን ይመለከታል፡፡

ዛሬ በሠለጠነው ዓለም አብዛኛው፣ የአፍሪቃ አገሮችን ጨምሮ የሕግ ማማከርና የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጠው በተደራጀ መልኩ፣ የጥብቅና አገልግሎት ድርጅት በማቋቋም ነው፡፡ በዚህ መልኩ ተደራጅተው ከራሳቸው ግዛት አልፈው ዓለም አቀፍ የሕግ አገልግሎቶችን በመስጠት የሚታወቁ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ድንበር ዘለል የጥብቅና አገልግሎት ድርጅቶች አሉ፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች ጠንሳሽ ጥቂት ግለሰቦች ቢሆኑም፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ከአገራቸው አልፈው ለሌሎችም የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አጋዥ ኃይሎች ሆነዋል፡፡ ከተለመደው የጥብቅናና የማማከር አገልግሎት ወጣ ብለው የጥናትና የምርምር ተግባራትን በማከናወን ለሕግ አውጪው፣ ለአስፈጻሚውና ለተርጓሚው ደጋፊ ኃይሎች ሆነዋል፡፡ ብቃት ያለው የሕግ ባለሙያ ለማፍራት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ተግባራዊ የልምምድና የሥልጠና ማዕከል በመሆን ለሕግ ትምህርት ቤቶችም ተጨማሪ ኃይል ሆነዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተናጠል በሚደረግ ሩጫና መባከን ሳይሆን፣ ተመሳሳይ አስተሳሰብ፣ ዓላማና ራዕይ ያላቸው ባለሙያዎች በቅንጅት ተደራጅተው ስለሠሩ ብቻ ነው፡፡

ለንግድና ኢንቨስትመንት በተለይም ለውጭ ኢንቨስትመንት አመቺ ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከሚያግዙ በርካታ የሕግ መሠረተ ልማቶች መካከል አንዱ ለኢንቨስተሮች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕግ ማማከር አገልግሎት የሚሰጥ፣ በሥርዓት የተደራጀ የጥብቅና አገልግሎት ድርጅት መኖር ነው፡፡

በኢትዮጵያም የፌዴራሉ መንግሥት የፌዴራል ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ (አዋጅ ቁጥር 199/1992)፣ የጥብቅና ፈቃድ፣ የፈተና መመዝገቢያና የጥብቅና ድርጅት መመዝገቢያ ክፍያ (ደንብ ቁጥር 65/1992) እንዲሁም የጠበቆች የሥነ ምግባር (ደንብ ቁጥር 57/1999) ሕጎችን በነጋሪት ጋዜጦች ታትመው እንዲወጡ ካደረገ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የተጠቀሰው አዋጅ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑና የፀና የጥብቅና ፈቃድ ባላቸው ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎት ድርጅት መቋቋም እንደሚችል፣ በሕጉ የተቀመጡ መስፈርቶች ተሟልተው ሲገኙም የፍትሕ ሚኒስቴር ድርጅቱን እንደሚመዘግብና ፈቃድ እንደሚሰጥ በአንቀጽ 18 ደንግጓል፡፡ ስለሆነም ሕጉ ጠበቆችን ብቻ ሳይሆን ለጥብቅና አገልግሎት ድርጅትም ዕውቅና እንደሚሰጥ አያጠያይቅም፡፡

 ይሁን እንጂ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 18(4) ስለጥብቅና ሙያ ድርጅት ፈቃድ አሰጣጥና ተያያዥ ጉዳዮች አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣ መመርያ እንደሚወሰን ተመልክቷል፡፡ በእርግጥ ከጉዳዩ ይዘት አኳያ የማስፈጸሚያ ሕጉ ደንብ እንጂ መመርያ አይመስለንም፡፡ ያም ሆነ ይህ የፍትሕ ሚኒስቴር የማስፈጸሚያ ሕጉን ረቂቅ አዘጋጅቶ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ‹‹ለምክክር/ውይይት›› አቅርቦት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሕጉ ረቂቅ ፓርላማም ተልኮ እንደነበር ሰምተናል፡፡ የሕጉ ይዘት በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች ቢኖሩትም (ለምሳሌ የጥብቅና አገልግሎት ‹ንግድ› ወይስ የፍትሕ ሥርዓት አጋዥ ሙያ፣ የሚቋቋመው ማኅበሩ የሚኖረው ቅርፅ ወዘተ) በመነሻነት ሊያሠራ እንደሚችል ይታመናል፡፡

በየዓመቱ በአማካይ 60 ሕጎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው በሚወጡበት አገር ውስጥ ግን ይህ ሕግ ማስፈጸማያ አጥቶ ከ15 ዓመታት በላይ እንዲጠብቅ የተደረገው ምስጢሩ ምን ይሆን? ሥጋቱና ጠቀሜታው በቅጡ ተለይቶ ባለመታወቁ ይሆን? ወይስ ኃላፊነቱ የተሰጠው አስፈጻሚ አካል ‹አንገብጋቢ› ሆኖ ስላለገኘው? ወይስ በ‹እናቴ መቀነት አደናቀፈኝ› ምክንያት፡፡ ተዘንግቶ ነው? ምላሽ ይሻል፡፡

‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› የሚለው ብሂል ያለማስፈጸሚያ ተንጠልጥሎ የቆየውን አዋጅ ለመግለጽ ተስማሚ ይሆን?

ከታዛቢው

*********

በአንጋፋው ዩኒቨርሲቲ የጃጀው የስፖርት ትምህርት ክፍል

ትምህርት በሕዝብና በአገር ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ለውጥን ሊያመጣ የሚችል የዕድገትና የለውጥ ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ በዛ ዕድገት ጎዳና የሚገኙ አገሮች ያለፉበትን ሒደት ስንመለከት፣ በውስጣቸው ያላቸውን ትልቅ የተማረ የሰው ኃይል በማብቃት፣ በሙሉ ኃይሉና አቅሙ እንዲተጋና የፈጠራ አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም በማድረጋቸው የሚያመጡት ለውጥ መሆኑ ነው፡፡

አገራችንም ይህንን አቅጣጫ ለመከተል በጅማሮ ላይ ስትሆን ለዚህ ስኬታማነት በሁሉም መስክ የዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ከሚጠበቅባቸው ግምባር ቀደም ተቋማት አንዱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ይህንን ለመወጣትም አደረጃጀቱንና አሠራሩን በመፈትሽ ለለውጥ ዝግጁነቱን ማስመስከር ይኖርበታል፡፡

ለዚህ መነሻ የሆነን በዩኒቨርሲቲው ብብት ሥር ተሸጉጦ ለዘመናት በአገሪቱ ምርምርና ፈጠራ ተግባር ላይ የረባ ነገር ፈይዶ የማያውቀው የስፖርት ትምህርት ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ችግር የክህሎት ሳይሆን የዕውቀት ችግር መሆኑ እየታወቀ፣ እዚህ ግባ የሚባል ምርምር በማካሄድ የንድፈ ሐሳብና የተግባር ዕውቀት በሌላቸው ሙያተኞች የሚመራውን የስፖርት ዘርፍ ማገዝ ካለመቻሉም በላይ በአካዴሚውም ዘርፍ መምህራኖቹ ራሳቸውን በዕውቀትና ክህሎት አብቅተው በተማሪዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብዕና ሊታይባቸው አለመቻሉ ሁሌም የምናዝንበት ነው፡፡

የትምህርት ክፍሉ አብዛኛዎቹ መምህራን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ከሥራ ይልቅ በሴራ፣ ከምርምር ይልቅ በአሉባልታና እንቶፈንቶ መሆኑ ሁሌም የምናፍርበት ነው፡፡

የትምህርት ክፍሉ በብዛትና በጥራት ተፎካካሪ መምህራንን በመቅጠር በስፖርቱ ዘርፍ ተዓምር የሚፈጥሩ ሰዎችን ማውጣት ሲገባው፣ ለዓመታት ብቃት ያለው ሰው እንዳይቀጠር ከማደናቀፍ ባሻገር መምህራኑ ለእነርሱ ሎሌ የሚሆን ደካማ ሰው በማፈላለግ መመዘኛውን በልኩ ሰፍተው ብቁውን ተወዳዳሪ ያለአግባብ ከውድድር ውጪ ያደርጋሉ፡፡

አብዛኛዎቹ መምህራን በሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ዘንድ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በእነርሱ አቅም የተማሪውን ዕውቀት ከፍ ለማድረግ የማይችሉ፣ ለማሳብ የተሳናቸው ናቸው፡፡

የመምህራኑ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ለመግባባት ሰፊ ዕድል ቢሰጣቸውም እነርሱ ግን ወደ ብዙ ትንንሽነት በመከፋፈል በመገፋፋትና በመሳብ፣ አንዱ የአንዱን መንገድ በመዝጋት መሰናክል በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፡፡

ትምህርት ክፍሉ አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን የመሪነት ሚና በመጫወት የተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮችን የመዘርጋት ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ በአሥርት ዓመታት የሚያንሱት እንደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓይነቶቹ በመዳህ ዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ተቋማት የዶክትሬት ዲግሪ መርሐ ግብር ሲከፍቱ፣ እነርሱ ግን ያለቁጭትና እልህ ለአበልና ለመዝናናት በመሄድ ባገኙት ጥቅማጥቅም ይፈነድቃሉ፡፡ መቀደማቸው መንፈሳዊ ቅናት ሳያሳድርባቸው አሁን ድረስ እንዲህ ያሉ መረሐ ግብሮችን ሊከፍቱ ባለመቻላቸው፣ በአዲስ አበባና አካባቢው የምንገኝ ሙያተኞች የመማር ፍላጎታችንን፣ በትምህርት ወደ ላይ የመግፋት ጥማታችንን እሰናክለውት ይገኛሉ፡፡

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ›› ሲያስተምሩን የተጫወቱብን አልበቃ ብሎ የቅጥር ማስታወቂያ አወጣን ብለው ግልፅነት የሌለውና፣ ለእነሱ የተመቸ (ክሊክ የሆነ ሰው) ለመመደብ የሚያስችልና ለተወሰኑ ሰዎች በልክ እንዲሰፋ አድርገው ማስታወቂያውን መቅረጻቸው አስገርሞናል፡፡ ይኸውም፡-

  1. ለማስተርስ ደረጃ ያወጡት ማስታወቂያ በስፔሻላይዜሽን መሆን ሲገባው በመረብ ኳስ፣ በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በማስተማር ዘዴ ይህን ያህል ሰው ይፈለጋል ብለው አለማውጣታቸው ለተድበሰበሰ አሠራራቸው ጠቅሟቸዋል፡፡
  2. በአሁኑ ጊዜ ተቋሙ መቅጠር የሚገባው በማስተርና በፒኤችዲ ደረጃ ያሉ ሙያተኞችን መሆን ሲገባው፣ እነርሱ ግን ‹‹ክሊክ›› ለማደራጀት እንዲያመቻቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሰው እንዲሳተፍ፣ ተጨማሪ ወጪም እንዲያወጣ ማድረጋቸው ታይቷል፡፡
  3. በአሁኑ ጊዜ በስፖርት መስክ በዲፕሎማ የሚያስመርቅ ተቋም ስለመኖሩ በሚያጠራጥር ሁኔታ ውስጥ እያለን በዲፕሎማ እንቀጥራለን ብለው ማስታወቂያ ማውጣታቸው ዲፓርትመንቱን ግምት ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
  4. የጡረታ ዕድሜ ክልል ውስጥ የገቡ ሰዎችን፣ የምርምር አቅም የሌላቸውና የትኛውም ባለሙያ ሊተካቸው የሚችሉ ይልቁንም ከእነርሱም የላቀ አቅም ያለው ባለሙያ የእነዚያን ቆይታ ለማራዘም መሞከር የትምህርት ክፍሉም ሆነ የዩኒቨርሲቲውን መቅጠር እየተቻለ አሳፋሪ ገጽታ የሚያሰፋ ነው፡፡

በአጠቃላይ የምንለው ነገር ቢኖር፣ ዩኒቨርሲቲው ራሱን ለለውጥ አዘጋጅቶ ከሆነ በትምህርት ክፍሉ የማይመቹ ኃላፊዎችን ነቅሶ በማውጣት ማስተካከል እንደሚገባው እያስገነዘብን፣ ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በቸልታ የሚያልፉት ከሆነ ግን የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደርም ሆነ የአካዴሚውን ቢሮ ከተጠያቂነት አያድናቸውም፡፡

የስፖርት ትምህርት ክፍሉ በኢትዮጵያ ብቸኛ ሳይሆን ቢያንስ በምሥራቅ አፍሪካ በምርምር አርዓያ መሆን ሲገባው፣ በሚገኝበት ኋላቀር መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ቀስ በቀስ መክሰሙ አይቀርም፡፡ የዩኒቨርሲቲው ገጽታ እየጠለሸ መባባሱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ተቋም ተማሪዎች የሆንን ሰዎች የምናሳስበው ነገር ቢኖር የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል እንዲፈተሽ፣ እንዲፈተሽ፣ እንዲፈተሽ ነው፡፡

(የተቋሙ ተማሪዎች፣ ከኦሮሚያ ክልል)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...