Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያ በእሾክ የታጠረ እምቡጥ ፅጌረዳ ናት

ኢትዮጵያ በእሾክ የታጠረ እምቡጥ ፅጌረዳ ናት

ቀን:

በልዑል ዘሩ

በጽሑፌ ይህን ርዕስ ለማድረግ ሳስብ የትንታኔዬ ማጠንጠኛ አበባ ወይም እሾክ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ በምሳሌው እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያን የከበቧት ‹‹እሾኮች›› ፅጌረዳውን ከአደጋ ለመጠበቅ እንደከበቧት ያሉ እሾኮች ስለሆኑም አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ፅጌረዳ የተዋበችና የምታምረውን ‹‹የተስፋ ምድር›› አገራችንን ዙሪያዋን የከበቧትን መጥፎና አመቺ ያልሆነ ሳንካዎችን ለመተንተን በመሻት ነው፡፡ ማብራሪዬ ካላረካችሁ መልሳችሁ በዚሁ ጋዜጣ ሐሳባችሁን ብትገልጹልኝ ለውይይት በር የከፈትኩ ያህል ይሰማኛል፡፡

በምሥራቅ ያለው የሥጋት ቀጣና

ኢትዮጵያን በምሥራቅ በኩል የምታዋስነው ዋነኛዋ አገር ሶማሊያ ናት፡፡ ይህቺ አገር ለአውሮፓዊያኑ ዓይን ማረፊያ መሆን የጀመረችው ንግድን መሠረት ባደረገ ሁኔታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1840 እስከ 1886 የእንግሊዝ የምሥራቅ ህንድ ካምፓኒ (East Indian Company) ከሶማሊያ ልዩ ልዩ የጎሳ መሪዎች ጋር የንግድ ስምምነትን መሥርቷል፡፡ ጣሊያንም በዚያው ዘመን ወደ ሶማሊያ እጇን ሰድዳለች፡፡ የራሷ የአፍሪካ ኢምፓየር በማድረግ እስከ 1941 ዓ.ም. ድረስ የገዛቻት መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡

የቅኝ ገዢዎች የመቀራመትና የመለያየት ሥልት ያውም በጣሊያን መሪዎች እየተወጠነ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለመተግበር ይዶለትባት የነበረችውም ይቺው አገር ነበረች፡፡ እርግጥ ቱርክና ግብፅም በንግድ ላይ የተመሠረተ ጣልቃ ገብነት በሶማሊያ አሳይተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዲያ ከኢትዮጵያም ጋር ቢሆን የተጠናከረ ወዳጃዊ ግንኙነት ከመፈጠር ይልቅ ጽዮናውያንና የክርስቲያን ደሴት እያሉ ጠላትነትን ከሚሰብኩ ወገኖች መረጃን በመቀበል የቅራኔ አካሄድን ሲከተሉ ኖረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በአፄ ምንሊክ የተካሄደውን ወሰን የማስከበር ዘመቻ እንደ ወረራ በመቁጠር፣ ሶማሊያውያን ወገኖቻችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተወስደዋል የሚል ቅስቀሳ በቅኝ ገዢዎቻቸው ጋሻ ጃግሬነት ይነገርም ነበር፡፡

በተለይ የእንግሊዝ ሰሜን ሶማሊያ ነፃነቷን ካወጀች እ.ኤ.አ. ከ1960 በኋላ ሁሉም የቅኝ ግዛት ክልሎች የተባበረች ሶማሌ ሪፐብሊክን ሲመሠርቱ ጥያቄው በስፋት ሲቀነቀን ተስተውሏል፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ ሶማሊያን ይመሩ የነበሩት እነ አደን አብዱላህ ዶሰማንደር (ፕሬዚዳንት) እና አብዳራሺድ ዓሊ ሼርማርኬ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር የመቀራረብ አዝማሚያ ያሳዩ ቢመስሉም፣ ቅኝ ገዢዎች የፈጠሩት ጥላቻ፣ ልክ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እንደታየው ደባ የተላበሰ ነበር፡፡

ወደኋላ ላይ ሼርማርኬ ፕሬዚዳንት ሆነው ለሁለት ዓመታት አገሪቱን ከመሩ በኋላ፣ በመፈንቅለ መንግሥት በመገደላቸው እብሪተኛው ሞሐመድ ዚያድ ባሬ ሥልጣን ተቆናጠጠ፡፡ እኝህ ወታደራዊ መኮንን አገራቸውን ‹‹የሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›› ብለው በመሰየም በሶሻሊስታዊ መንፈስ (የሩሲያን ድጋፍ) አሰባስበው ኢትዮጵያን እስከ መውረር መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

የወረራው መነሻም ‹‹ታላቋ ሶማሊያን›› የመመሥረት ከንቱ ህልም በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ከደርግ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ሉዓላዊነትን ማስደፈር የማይሆንለት የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ተጋድሎ ነፃነቱን አስከብሯል፡፡ ‹‹በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና›› ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ እ.ኤ.አ. በ1991 በጎሳ በተደራጁ ሶማሊያውያን በኃይል ተገረሰሱ፡፡ ሶማሊያም ከ20 ዓመታት ለበለጠ ጊዜ መንግሥት አልባና ደሃ መባል ብቻ ሳይሆን፣ የአክራሪና የጽንፈኛ ሽብርተኛ ኃይሎች መፈንጫ ሆና ቀረች፡፡

የጎረቤት አገር ሶማሊያ ቀውስ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ለመፍጠር ሳያስችል ቆይቷል፡፡ ይልቁንም የዚያድ ባሬን ሐሳብ ከሚያራምዱ የጎሳ መሪዎች አንስቶ እስከ ግብረ ሽብር መሐንዲሶች ድረስ ኢትዮጵያን በጠላትነት ከመረፈጅ አልቦዘኑም፡፡ በዚህም የተነሳ ከአሥር ዓመት በፊት በተደረገ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት አገሪቱ በምርት ሳይሆን፣ ከ15 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎችና እሳት የሚተፉ ቅንቡላዎች (ፈንጂዎችና ተተኳሾች) ተጥለቅልቃለች፡፡ ይኼም ሌላው የቀጣናው ሥጋት ማሳያነቷ ነበር፡፡

እንደ አልቃይዳ ጥፍጥፍ የሆነው አልሸባብ ዓይነት አሸባሪዎች ከመፈጠራቸውም በፊት የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት፣ አሊተሃድና መሰል ስያሜዎችን የያዙ አሸባሪዎች በአገር ውስጥ ካሉ አንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ከ1995 ዓ.ም. የድሬዳዋ የራስ ሆቴል የፈንጂ ጥቃት አንስቶ በአዲስ አበባም በዋቢ ሸበሌና በብሉ ቶፕስ አፈንድተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 ሞምባሳ ኬንያ ፓራዳይዝ ሆቴልን ማጥቃታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዚሁ ወቅት በሥፍራው ሲበር የነበረውን የእስራኤል አውሮፕላንን ተኩሰው መሳታቸው ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1998 በናይሮቢ ኬንያ የተፈጸመ ግብረ ሽብርና የታንዛኒያው ጥቃትም የሽብር ተግባሩ ማሳያ ነበር፡፡

ከእነዚህና ከሌሎች  በርካታ የሶማሊያ የሽብር ሥጋቶች በመነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት የውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ከማረጋገጥ አንስቶ ሞቃዲሾ ድረስ በመግባት የምሥራቁን ጫፍ የነካ ጂሃዲስት ባያንኮታኩተው አመጣጡ ከባድ እንደነበር በተለይ ዛሬ ላይ ብዙ ተንታኞች እያረጋገጡት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና እንደ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድን የመሳሰሉ ሕጋዊ አካላት የሰጡትን ፈቃድ ተቀብሎ ወደ ሶማሊያ ሲዘምት፣ ተቃዋሚዎች ክፉኛ መተቸታቸው አይዘነጋም፡፡ ‹‹ሉዓላዊነት›› የሚሉ አንዳንድ ‹‹የንድፈ ሐሳብ›› ምሁራንም አንቀጾችን ለመጠቃቀስ ሞክረዋል፡፡

እውነታው ግን እንዲያውም ኢሕአዴግ ካለው የመዘናጋት ባህሪ አኳያ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ውሳኔ እጅግ ትክክል የሚባል እንደሆነ መግባባት ያስፈልጋል፡፡

ጂሃዲስቱ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ ሲያበቃ መንግሥት ‹‹በህቡዕ›› ይያዘው እንጂ በሐረርጌ ባቢሌ ገዳማት ተቃጥለው መነኮሳት እየታረዱ ነበር፡፡ በባሌ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በጅማና በሥልጤ ዞኖች ከነአልሸባብና ቦኮ ሐራም እኩል የእስልምና መንግሥት ተልዕኮን ወስዶ ውስጥ ውስጡን ሲሠራ የነበረው ኃይል እየበረታ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕገወጥ መሣሪያ የሚገኝባትን አገር እንዳሻው የሚጨፍርባትን አልሸባብ እንደምን መታገስ ይቻላል? እጅ አጣጥፎ ሞትን ከመጠበቅ ውጪስ ምን ሊመጣ ነበር?

ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ የአልቃይዳንም ሆነ የአልሸባብን አጋርነት የተመኙ፣ ‹‹ገዢው ፓርቲን ከሥልጣን ማውረድ›› በሚል ሥሌት የአገርና የሕዝብ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ የእኛ ተብዬ ኃይሎችስ አልነበሩም? በስመ ነፃ አውጪነት ተሠልፈናል እያሉ የሽብርተኞችን ተግባር የሚደግፉ ኃይሎች አልተመቻቸውም እንጂ፣ አልሸባብ ቢሆንለት እነዚህን ሁሉ አስተባብሮ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ለመበታተንና የአሸባሪዎች መፈንጫ ማድረግ ነበር ዓላማው፡፡

በሰሜን ያደፈጠው ተኩላ

ሻዕቢያ ገና ከመነሻው የኢትዮጵያ ጠላቶች ሥሪት በመሆኑ ከአብሮነት ይልቅ መነጠል፣ ከልማት ይልቅ ጥፋትና ጥላቻን መዝራት ያለመ ኃይል ነው፡፡ ምንም እንኳን በታሪክ አጋጣሚ ዛሬ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር ደርግን የመደምሰስ ስትራቴጂካዊ አጋር እንደነበር ባይካድም፣ መቼውንም ቢሆን ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ለመጉዳት መሣሪያ ሲሆን የኖረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ሻዕቢያ እያተራመሰ ከመሄድ ባለፈ በኢሕአዴግ ላይ በአንቀልባ ታዝሎ አገር ለመበዝበዝ የነበረው ህልም ሲመክን፣ ጦር ለመስበቅና ንፁኃንን ለመፍጀት ወደኋላ ያላለውም ለዚህ ነበር፡፡ ይህ አስፈሪና አደናቃፊ ኃይል በ1990 ዓ.ም. ግንቦት ወር የሞከረው ድፍረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔርና በሃይማኖት ተበታትኖ በቅድሚያ ኢሕአዴግን፣ ከዚያም የትግራይን ሕዝብ በመጨረሻም ኢትዮጵያን ገባርና ምንደኛ ለማድረግ ነበር፡፡ አይደፈሬው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ ሥልት እንዲፈታ የተደረገውን ትጥቅ መልሶ በማንገት፣ ሻዕቢያን ባይገስፀው (ሙሉ በሙሉ ያልተመታ መሆኑን ልብ ይሏል) ኖሮ ‹‹ይኼኔ ኢትዮጵያ …. ግብሩ…›› ሆኖ ነበር፡፡

ሻዕቢያ አሁንም ለኢትዮጵያ ካለመተኛቱም ባሻገር፣ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆነን እንድንኖር ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ ሻዕቢያ ከአልሸባብ ጋር የዓላማ ተጋሪ ሆኖ ከሰባት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የጥቃት ተባባሪ ሆኗል፡፡ በተለይ አልሸባብ ተቆጣጥሮት ከነበረው የባህር ዳርቻና የኤርትራ አዋሳኝነት ጋር በመጠቀም በባህርና በየብስ የጦር ልምምድን ጨምሮ ትጥቅ የማስተላለፍ እገዛ እንዳደረገ ተጠርጥሯል፡፡ ከሌብነት አስተሳሰብ በሚመነጭ የዘረፋ ተባባሪነት ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ በአስመሳይነት ‹‹ዓረባዊና እስላማዊ›› መስተጋብር የዓላማ ተጋሪ ለመሆን ሻዕቢያ ሲፍጨረጨር እንደነበርም ትልልቅ የደኅንነት መረጃዎች አውጥተውታል፡፡

ሻዕቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ነጭ ለባሾች›› ለሚላቸው ሥርዓቱን በትጥቅ ለመቀየር ለሚሹ ኃይሎች ያለው ድጋፍም በግልጽና በአደባባይ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በኃይል ለመንጠቅ የሚፈልጉ የትጥቅ ተፋላሚዎችን ማስታጠቅ ብቻ ሳይሆን የዓላማ ተጋሪነት ኅብረት የመፍጠር ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበሰ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ‹‹ከመቀየር›› ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተገኘው ሰላም ቀና ብሎ መሄድ የጀመረን ሕዝብና ገጽታን መቀየር የጀመረችውን አገር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድና ለመበታተን ታልሞ እየተሠራ ያለ ነው፡፡

ኢሕአዴግ እያሠራ ባለው ሥራ ሕዝብ ካላረካ፣ የአገርን ጥቅምና ፍላጎት ከጎዳ፣ እንዲሁም የሕዝቡን አንድነት አጠናክሮ መቀጠል ካልቻለ ከሥልጣን መውረድ እንዳለበት ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን መቼም ቢሆን ተመልሰን ወደ ግጭት፣ ጦርነትና ትርምስ ልንሄድ አንችልም፣ አይገባም፡፡ ሕዝቡ ማጣጣም የጀመረውን ልማትና ሰላም የሚያደፈርስበትን ኃይል ሊቀበልና ሊያስተናግድ አይችልም፡፡ በዛሬው ዓለም እንዲህ ያለውን አፍራሽ መንገድ የመረጡ የዚህ አገር ዜጎች መንገዳቸው ስህተት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከአገር አጥፊው ሻዕቢያ ጋር ያላቸው ጥምረት አዋርዷቸዋል፡፡ ደጋፊ አልባ እንደሚያደርጋቸውም ጥርጥር የለውም፡፡

በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው ባሻገር መልሰው በቢዝነስ ዘርፍ እየተሰማሩ ነው፡፡ በየዩኒቨርሲቲው መግባታቸውም ይታወቃል፡፡ ይህ በጎ ተግባር እንደ ሕዝብ ጥቅም ሲታይ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሻዕቢያ ተንኮልና መሰሪ ባህሪ አኳያ ለጥፋት መንገዱ የሚመቹ ግለሰቦችና የመረጃ ሰዎችን አለማስገባቱን አለመጠርጠር ተላላነት ነው፡፡ የአገራችን የፀጥታና የደኅንነት ኃይል መቀናጀትና ጥንካሬ መኖሩ እንጂ፣ በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ላይ ለሚነሱ የጥቃት ሥጋቶች የሚጠረጠረው ሻዕቢያና ሻዕቢያ ብቻ ሆነዋል፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹የግንቦቱን ምርጫ በጦርነት እናሟሽሸዋለን›› የሚሉ ታጣቂዎች ከወደ ሰሜን እየተናገሩ ነው፡፡ ይህ ድርጊት አሁን ባለው ሁኔታ የአንበሳን አፍንጫ የምታሸተው ሚዳቋ ዓይነት ተረት ቢሆንም መንገዳችንን ሊያስተጓጉል አይችልም ማለት አይቻልም፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ያልተገባ ሥራ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ለዘብተኛና ‹‹በራሱ ይንኮታኮት›› የሚል ቢመስልም በጥንቃቄ መጤን ያለበት ነው፡፡ ሻዕቢያ ለሶማሊያ ሰላም ማጣት፣ ለደቡብ ሱዳን ግጭት መባባስ፣ ለናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አንዳንድ አገሮች (ኡጋንዳ፣ ሱዳንና ግብፅ) ያለመፈረምና ማንገራገር፣ ወዘተ ሁሉ አስተዋጽኦ አልነበረውም ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡

ባለፈው ዓመት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሕገወጥነት ስም ከሳዑዲ ዓረቢያ እየተለቀሙ በእንግልት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጊዜ በመልክ፣ በሥነ ልቦናም ሆነ በቋንቋ ከአገሬው ሰዎች ጋር የሚመሳሰሉት ኤርትራውያን ያን ያህል መፈናቀልና መፍለስ ያልደረሰባቸው መሆኑ ሲታይ፣ ኢሳያስና ጀሌዎቹ የሚሄዱበትን የተንኮል መንገድ ርቀት ማጤን ይረዳል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያውያንን በጦር መውጋት እንደማይሳካ ሲያውቀው፣ በተለያዩ ‹‹ገለልተኛ›› በሚመስሉ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ሕዝቦች እርስ በርስ የሚያባላው ማን ነው? በሃይማኖትና በአመለካከት ያለን ልዩነት እንደ ውቅያኖስ እንዲሰፋ በማድረግ አገራዊ አንድነት እየመነመነ እንዲሄድ አላደረገም? ዛሬ በቀናት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚጎበኙዋቸው ድረ ገጾች የማን ናቸው? (እኛም እየተባበርነው ይኼኛው ጥፋት ይበልጥ የተሳካለት ይመስለኛል)

የምዕራባዊ አቅጣጫው ጉርብትና ሰላም ነውን?

ኢትዮጵያን በምዕራብና በምዕራባዊ ደቡብ በኩል የሚያዋስኑ አገሮች ቢያንስ ሦስት ሆነዋል፡፡ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ከፊል ኬንያ፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ አገሮች ጋር እንደ መንግሥት የጎላ ፀብና አለመግባባት የለም፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩም የተበላሸባት የታሪክ አጋጣሚ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ወደፊት እያደጉ የሚሄዱና በተጠናከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙንት ካልተያዙ የመበላሸት ዕድል ያላቸው ሥጋቶች መኖራቸውን ግን መዘንጋት አይገባም፡፡

አንደኛው ከሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር ጋር በተያያዘ 11.3 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ግጭት ነው፡፡ ይህ የሕዝብ አደጋ በጥቂት ስግብግብ የሥልጣን ጥመኞች መዘዝ የተፈጠረ ሲሆን፣ መሠረታዊው ችግር ዘረኝነትና ጠባብነት ነው፡፡ ዓለም አንድ መንደር ለመሆን ሲጣጣር ቢያንስ አገሮችም ብቸኛው አማራጭ ውህደትና ትብብር ነው ብለው እየዘመሩ፣ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ግን ከሱዳን መገንጠላቸው አንሶ ዲንቃና ኑዌር ብለው መገነጣጠልን ይሻሉ፡፡

‹‹ይኼ ታዲያ ለኢትዮጵያ ምን ሥጋት ይሆናል? ለምን አይባሉም?›› የሚሉ የዋሃን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እውነቱ ግን አሁን ባለችው ዓለም በየትኛውም አገር ግጭትና አለመግባባት ሲነሳ ጥፋቱ በቀጣና ደረጃ ሥጋት የሚፈጥር እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ የነ ኢራቅና አፍጋኒስታን ከአገር አልፎ የመላው መካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ሥጋት የሆነው በጊዜ በትብብር ባለመፈታቱ ነው፡፡

በምዕራብ አፍሪካ ናይጄሪያ ውስጥ የታየው የቦኮ ሐራም አዝማሚያ ቻድንም ወደ ጦርነት አስገብቷል፡፡ አሁንም ርብርብ ካልተደረገበት ቀጣናው አልፎ እንደሚሄድ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በዩክሬን መዘዝ የታንክ ሸራውን እየገፈፈ ያለው አገር እየተበራከተ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት፣ ሩሲያና አሜሪካ ብቻ ሳይሆኑ እነቻይናም በቅርብ ርቀት ለማየት የሚሹት አጀንዳ ሆኖ መሰንበቱን አይተናል፡፡ የደቡብ ሱዳናውያን ግጭት ለእኛ ደግሞ ከእዚህም የቀረበ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ጋምቤላ ክልል ያለው አኝዋክ ማኅበረሰብ ከፊል ወገኖቹ ደቡብ ሱዳን የሪክ ማቻር ‹‹ተከታዮች ናችሁ›› በሚል ከፍተኛ ጥቃትና ስደት እየደረሰባቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ሳል ቫኪር የኢትዮጵያን ለዘመናት የዘለቀ የደቡብ ሱዳንን ድጋፍ በመዘንጋት ከነኡጋንዳና ኬንያ የበለጠ አይደለም ወደ ማለት ማፈግፈጋቸው ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የኢጋድ አስገዳጅ ሁኔታ ይዟቸው እንጂ፣ ኢትዮጵያ ከሽምግልና እንድትወጣ ፍላጎታቸውን በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹ አይዘነጋም፡፡

ከዚህም በላይ ግብፅን የመሳሰሉ ከኢትዮጵያ ጋር እምብዛም ወዳጅነት የሌላቸው አገሮች በደቡብ ሱዳን እያሳዩ ያሉት ጥምረት የሥጋት ምንጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር በተያያዘ፣ የግብፅና የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ትብብር መጀመር፣ በቅርቡም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚሆን ሰፊ መሬት ላይ የመስኖና የኃይል ማመንጫ ሥራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ በጎ ነው ብሎ መውሰድ ያዳግታል፡፡ በድምሩ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ በእጅ እንደተያዘ እንቁላል በአግባቡ ካልተጠበቀ አደጋው ቀላለ አይሆንም፡፡

የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የቅርብ ጊዜ ‹‹ወዳጅነት›› መልካም የሚባል ነው፡፡ በተለይ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ መስማማትና መግባባት እየተፈጠረ ይመስላል፡፡ ሱዳን ግን በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ሽብርተኝነትን በይፋ ከማያጋልጡ መንግሥታት ተርታ የሚሠለፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በእስራኤልም ሆነ በአሜሪካ የአየር ጥቃት ደርሶበት የነበረ ‹‹የነውጠኛና የለዘብተኛ ቅልቅል ባህሪ›› ያለው መንግሥት ነው የሚሉ ታዛቢዎች አሉ፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፕሬዚዳንት አል በሽር ከኢትዮጵያውያን መሪዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ በኢትዮጵያ ሐዘንም ሆነ ደስታ የሚያደርጉት ተሳትፎ አለ፡፡ ሻዕቢያንም እኩል የሚያስተናግዱ መሆናቸው ግን በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ከግብፅ ጋር ለረዥም ዘመን ከነበራቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጋብቻ አኳያም ሱዳን ሙሉ በሙሉ አጋርና ታማኝ ወዳጅ ነው ብሎ መደምደም የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ክስረትን ያስከትላል፡፡ አንዱ ማሳያ ‹‹የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ የስምምነት ማዕቀፍ›› መፈረም አይደለም እንደ ጋራ ሰነድ ሲጠቅሱ አለመታየታቸው ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በወዳጆች መሀል ብቻ የተከከበች አይደለችም፡፡ አጎራባቾቿን ለመጠምዘዝ የሚችሉ ሀብትና አቅም ያላቸው ባላንጣዎችም አሉባት፡፡ ከሁሉ በላይ በፍጥነት ማደግም ሆነ ኃይል የመሆን ጥረቷ እንቅልፍ የሚነሳቸው አይኖሩም ማለት ያዳግታል፡፡ ስለዚህ ምንጊዜም ቢሆን ይኼን ተገንዝቦ ዘርፈ በዙ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ በብሔር ስም የሚቀነቀን ጠባብነት፣ በሃይማኖት ጭቆና መዘዝ የሚቦካና የሚጋገር የመበታተን አደጋ እየታረመ፣ ኅብረ ብሔራዊ ዴሞከራሲያዊ አንድነት በብሔራዊ መግባባት ታግዞ ካልተገነባ መጪው ጊዜ ፈተና የሞላበት መሆኑ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...