Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ምክር ቤቱ የኋሊት ጉዞና ያልተሳካው ጉባዔ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የከተማም ሆነ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ሁሉ በጥንካሬው ሲጠቀስ የቆየና የአዲስ አበባ ንግድ ኅብረተሰብ ወኪል ተደርጎ የሚወሰድ ተቋም ነው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባሉት የአባላት ብዛትና በተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴዎቹም በተለየ የሚታይ ነው፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ይህ አንጋፋ ተቋም የሚታወቅባቸው መለያዎቹ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሸረሸሩ ስለመምጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ወደ አመራር ለመምጣት የሚፈልጉ ወገኖች የሚፏከቱበትም ሆኖ ስሙ በተደጋጋሚ መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከሳሽና ተከሳሽ ሆኖም ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ መጀመሩ የንግድ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ ለዚህም እንደ አንድ ማሳያ ይሆናል የተባለው ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረው የዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔዎችና በዕለቱ የተደረገው የአመራር አባላት ምርጫ ተሽሮ ድጋሚ እንዲካሄድ በፍርድ ቤት መወሰኑ ነው፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረትም በድጋሚ የሚካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያስፈጽምና ምርጫውን የሚያስደግም ባለአደራ ቦርድ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይህ ባለአደራ ቦርድ በንግድ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሁለት ወራት ሊሆነው ነው፡፡ በንግድ ሚኒስትር ዴኤታው የሚመራው ባለአደራ ቦርድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለማስፈጸምም ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቷል፡፡ የምርጫ አስተባባሪ በመሰየምም ተጠቋሚዎችን አሰባስቦ ምርጫ ለማድረግ ግን አልቻለም፡፡ ይህም የንግድ ምክር ቤቱን ክፍተት እንዳሳየ በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡

በድጋሚ እንዲካሄድ የተጠራው የንግድ ምክር ቤቱ ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ የ2005 በጀት ዓመት ሪፖርት የሚደመጥበትና ምርጫ የሚካሄድበትም ነበር፡፡ ለዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ የተዘጋጀው መርሃ ግብር ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተጀምሮ 12 ሰዓት እንደሚያልቅና ከዚያም ምሽት ላይ የሪሰብሽን ግብዣ የሚያካትት ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር የሚፈጽሙ ቢሆንም፣ የሐሙሱ ግን ከዚህ በተለየ የተጠበቀው ሳይሆን ያልተጠበቀው የታየበት ሆኗል፡፡ እንደ ሁልጊዜውም የጠቅላላ ጉባዔው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንደሚገኙ ተገልፆ ነበር፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን በይፋ የሚከፍቱት ከንቲባው ናቸው፡፡ በሐሙሱም ስብሰባ የከተማው አስተዳደር በምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ተወክሎ ነበር፡፡ አቶ አባተም በሰዓቱ ጠቅላላው ጉባዔ በሚካሄድበት የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይገኛሉ፡፡

የባለአደራ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ዓሊ ሲራጅና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊው አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ከክብር እንግዳው ከአቶ አባተ ስጦታው ጋር በመሆን የጠቅላላ ጉባዔውን መጀመር ይጠባበቃሉ፡፡

ይሁን እንጂ የዕለቱ ስብሰባ ይጀመራል በተባለበት ሰዓት ሳይጀመር ይቀራል፡፡ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ሰዓታቸውን አክብረው የተገኙ ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙ ለምን እንደማይጀመር ለማወቅ ባይችሉም፣ የንግድ ምክር ቤቱ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ከንግድ ሚኒስቴር በመወከል የባለአደራ ቦርዱ አባል የሆኑት አቶ አየነው ፈረደ ከወዲያ ወዲህ ሲመላለሱ ይታያል፡፡ በተወሰኑ ደቂቃዎች ልዩነትም ወደ ክብር እንግዶቹ እየተመላለሱ ይንሾካሾካሉ፡፡ ስብሰባው ይጀመራል ከተባለበት ሰዓት ወደ አንድ ሰዓት አካባቢ ቢዘገይም የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡

የስብሰባው አለመጀመር እንቆቅልሽ የሆነባቸው ተሰብሳቢዎችና የዕለቱ የክብር እንግዶች በትዕግሥት ከመጠበቅ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ የዕለቱ ጉባዔ እንዲካሄድበት የተመረጠው ቦታ ደግሞ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስለነበር ከቀጥር በኋላ በቆርቆሮ አዳራሹ ላይ የሚወርደውን ፀሐይ ለመቋቋም የሚጠይቀው ትዕግስት ቀላል አልነበረም፡፡ ቢሆንም ተሰብሳቢዎቹም ሆኑ እንግዶቹ የፕሮግራሙን መጀመር እየተጠባበቁ ነው፡፡

ከቆይታዎች በኋላ ከሌሎች በተለየ ፊታቸው ላይ ጭንቀት የሚታይባቸው የንግድ ምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳና ሌሎች የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች ከአቶ አየነው ፈረደ ጋር ሆነው ከተነጋገሩ በኋላ አቶ አየነው የድምፅ ማጉያውን ያዙ፡፡ ስብሰባው ሊጀመር ነው የሚል ግምት የነበራቸው ተሰብሳቢዎችም ጆሮአቸውን ሰጧቸው፡፡ አቶ አየነው ግን እንዲህ አሉ፣ ‹‹የተከበራችሁ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት አንድ ማሳሰቢያና የይቅርታ ማስታወቂያ አለን፡፡ ኮረሙ ሊሞላ የቀረው ትንሽ ነው፡፡ ከውጭም አባላት እየቡ ናቸውና በቅርቡ ይሞላል፡፡ ያቆየናችሁ ከአቅም በላይ ስለሆነብን ነው፤ ይቅርታ፡፡ ትንሽ ታገሱን፡፡›› ከዚህም በኋላ የተየ ነገር አልተፈጠረም፡፡ ከጥቂት ቆይታዎች በኋላ ምልአተ ጉባዔው ተሟልቶ ፕሮግራሙ ይጀመራል የሚለው ነገር አጠራጣሪ ሆነ፡፡ ጉባዔው ሊካሄድ የማይችል ስለመሆኑ የተረዱት የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ አባተ ስጦታው ግን ቀስ ብለው ወጡ፡፡ እየተንጠባጠበ የሚመጣ ተሰብሳቢ ቢኖርም በዕለቱ የሚፈለገውን ምልዓተ ጉባዔ መሙላት ሳይችል ቀረ፡፡

አሁን የመጨረሻው ሰዓት ነው፡፡ የባለአደራ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ዓሊ፣ አቶ ሺሰማ፣ አቶ አየነውና አቶ ጌታቸው ወደ መድረክ ወጡ፡፡ ‹‹የዕለቱ ጠቅላላ ጉባዔ በምልዓተ ጉባዔ ያለመሟላት አይካሄድም፤›› አሉ፡፡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ በድጋሚ ስብሰባው እንዲጠራ ሐሳብ ቀርቦ ቀን ተቆረጠ፡፡ ለአባላት ታድሎ የነበረው የምርጫ ካርድ ተመለሰ፡፡ ለማታ የተዘጋጀው ሪሰብሽንም ለመክሰስ ሆነ፡፡

ተለዋጭ ቀጠሮ ላይ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት አቶ ዓሊ በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ከተሰብሳቢዎች አስተያየት ተቀብለው ነበር፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ከተበተነ በኋላ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ነጋዴዎችም በዕለቱ ከተሰበሰቡት ውስጥ ንግድ ምክር ቤቱን በቅጡ የማያውቁ ጭምር እንደሆኑ ገልጸው፣ የአዲስ አበባ ነጋዴ ይህ ነው ወይ? እስከማለት ደርሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሚያውቋቸው የትላልቅ ኩባንያ ባለቤቶች በዚህ ስብሰባ የሉም፡፡ ያዩዋቸው ጥቂቶቹን ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ የንግድ ምክር ቤታቸው ዕጣ ፈንታ እንዳሰጋቸው ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የንግድ ምክር ቤቱን አካሄድ የተመለከቱ የቀድሞ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እየታየ ያለው ክፍተት ንግድ ምክር ቤቶች ቢዘጉ ይሻላል ብለው የተናገሩትን ያስታወሱም አሉ፡፡ በሰዎች ከሚፈጠረው ክፍተት ሌላ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖም አለና ይህ አዋጅ እስካልተሻሻለ ድረስ ለውጥ ሊመጣ አይችልም ብለዋል፡፡

ኮረም ለምን አልሞላም?

የአዲስ አበባ ንግድና ማኅበራት ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ከ15 ሺሕ በላይ አባላት አሉት፡፡ ባለፈው ሐሙስ ሊካሄድ ከነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተበተነው የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ በ2005 ዓ.ም. 14,987 አባላት እንደነበሩት ያሳያል፡፡

ከዚህ ውስጥ እስከ 2005 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 4,558 ዓመታዊ መዋጮዋቸውን የከፈሉ ናቸው፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ መሠረት በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመገኘትና የመምረጥ መብት ያላቸውም እነዚሁ የአባልነት መዋጮዋቸውን የከፈሉ ናቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንቡን ከማሻሻሉ ቀደም ብሎ ጠቅላላ ጉባዔው በውክልና ያካሂድ ነበር፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ሲሻሻል ግን 500+1 አባላት ከተገኙ ጉባዔውን ማካሄድ እንዲቻል ያስቀምጣል፡፡

ይህ የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ንግድ ምክር ቤቶችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ይጋጫል የሚል ጥያቄ የሚቀርብበትና ጉዳዩም ፍርድ ቤት ድረስ ያስኬደ ቢሆንም፣ የሐሙሱ ስብሰባ እንዲካሄድ የተጠራው ግን ከአጠቃላይ አባላቱ 500+1 ከተገኘ ጠቅላላ ጉባዔው ይካሄዳል በሚለው የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ መሠረት ነው፡፡

አቶ ዓሊ እንደገለጹትም ‹‹የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ምክር ቤት በሕገ ደንቡ ቢያንስ ከ500 በላይ አባላቱ መገኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ አሁን በተጨባጭ የተገኙትን አባላት ስናይ 400 አካባቢ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ቁጥር ይህንን ጉባዔ ማካሄድ ከሕግ ውጪ ነው የሚያደርገን፡፡›› አንዳንድ ተሰብሳቢዎች ግን አሁን ባለነው ለምን አይካሄድም ብለው ነበር፡፡ አቶ ዓሊ እያንዳንዱን አካሄድ በጥንቃቄ ያስኬዱ ስለነበር ባለው ተሰብሳቢ ጉባዔው ይካሄድ የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት እንደሌለው አሳወቁ፡፡ ሁሉንም ነገር በንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብና በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የሚካሄድ ነውም አሉ፡፡

15 ሺሕ አባላት 400 ብቻ አባላት ብቻ መገኘታቸውና ጉባዔ ማድረግ አለመቻሉ ምክንያት የተለየ አስተያየት እየተሰጠበት ሲሆን፣ ባለአደራ ቦርዱ ግን በኢሜልና በተለያዩ ሚዲያዎች ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ለቀጣዩ ስብሰባ ጥሪ ግን ሌሎች አማራጮችንም መጠቀም ያስፈልጋል ተብሏል፡፡  

በዕለቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በሰጡት አስተያየት፣ ምልዓተ ጉባዔ ሊሟላ ያልቻለው ያልተገባ መረጃ በመሠራጨቱ ጭምር ነው ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው አባባል ይህንን ጉባዔ እንዲካሄድ ያልፈለጉ ወገኖች የስብሰባው ቀን ተለውጧል ስለተባሉ ያልመጡ ስለመሆናቸው መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉ በዕለቱ ምልዓተ ጉባዔ ያልተሟላበት ብለው ያስቀመጡት ምክንያት ትክክለኛ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ባይቻልም፣ ያነጋገርናቸው የአንዳንድ ነባር የንግድ ምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ግን ከወ/ሮ ሙሉ የተለየ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ከንግድ ምክር ቤቱ የመራቅ አዝማሚያ እያሳዩ ያሉት ከዚህ በፊት እንጂ በዛሬ ስብሰባ ላይ አትምጡ ስለተባሉ አይደለም ይላሉ፡፡

እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች በንግድ ምክር ቤቱ አካባቢ የሚታዩ ተደጋጋሚ ፉክቻዎች አባላት ላይ እምነት ማሳጣቱን በቀዳሚነት ጠቅሰዋል፡፡ የሚታወቁና ትልልቅ የሚባሉ አንዳንድ ኩባንያዎችም ከምክር ቤቱ አባልነት እየወጡ መሆናቸውም ሌላ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በአዲሱ የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ የዘርፍና የንግድ ድርጅቶች ተጣምረው መሥራታቸውም ራሱን የቻለ ክፍተት በመፍጠሩ አባላት እንደቀድሞ ተሳትፎ እንዳያደርጉ በር ከፍቷል፡፡ ይህም ቢያንስ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንኳን ለመገኘት ባለመቻላቸው ከዓመት ዓመት የጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳታፊዎች ቁጥር ሊቀንስ ችሏል የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የንግድ ኅብረተሰቡን ወኪሎች ለመምረጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ እጁን ማስገባቱና እንደተቀጣሪ ሳይሆን እንደቀጣሪ ሆኖ እየሠራ ነው መባሉም ከአባላት ተሳትፎ ማነስ ጋር ተያይዟል፡፡

የሐሙሱ ስብሰባ ከተበተነ በኋላ አባላት ለምን አልመጡም ለሚለው ጥያቄ የተለየ አስተያየት የሰጡ አንድ አባል ደግሞ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ጠቅላላ ጉባዔዎች ጽሕፈት ቤቱ እጁን ባለማስገባቱ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከዚህ በፊት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምልዓተ ጉባዔ ለመሙላት ጣልቃ ይገቡ የነበሩ አባላት እጃቸውን እንዲሰበስቡና ባለአደራ ቦርዱም የተሳታፊ ምዝገባዎችን በጥንቃቄ በመሥራቱ ምልዓተ ጉባዔ ለመሟላት ያለመቻሉን ይገምታሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ምልዓተ ጉባዔ ሞላ የሚባለው በተገቢው መንገድ ተሠርቶ ነው የሚለውን ነገር እንዲጠራጠሩ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል፡፡

ተሰብሳቢዎቹ እነማን ነበሩ?

በሐሙሱ ስብሰባ ላይ ብልጫ ይዘው በጉባዔው ላይ ተገኝተው የነበሩት የዘርፍ አባላት ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ውስጥ የሚታወቁ የትላልቅ ኩባንያዎች መሪዎች አይታዩም፡፡ ጥቂት የባንክ፣ የኢንሹራንስና የአገልግሎት ተቋማት መሪዎች ከመታየታቸው ውጪ በትክክል የአዲስ አበባን ነጋዴ የሚወክል ስብጥር ታይቷል ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ባሉ ጠቅላላ ጉባዔዎች ላይ ይሳተፉ የነበሩ ኩባንያዎች ያለመታየትም የዘርፉ አባላት ብልጫ ያለውን ድርሻ እንዲይዙ አድርጓል፡፡ ይህ አካሄድም የንግድ ምክር ቤቱ አካሄድ ወዴት እንደሆነ እያመላከተ እንደሆነ ያሳያል የሚል አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

አንድ አባል፣ ‹‹ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት በምክር ቤቱ አመራሮች መካከል የነበረው ፍትጊያ አባላትን ያሰለቸ ይመስለኛል፤›› ብለው፣ ጽሕፈት ቤቱ ይህንን ተገንዝቦ የራሱን ሥራ ቢሠራ ይሻላል ብለዋል፡፡ ማኅበሩ እንዲፈርስ አንፈልግም ያሉት እኚሁ አባል፣ ‹‹እኛም ቀስቅሰን በቀጣዩ ጉባዔ አባላት እንዲገኙ ማድረግ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ በዕለቱ የተፈጠረው ሁኔታ ያበሳጫቸው ሌላው አባልም፣ ‹‹እባካችሁ ምክር ቤቱን እናድን፡፡ ምክር ቤቱ መፍረስ የለበትም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ባይካሄድም በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ነጥብ ይዘው በሰከነ መንፈስ አባላትን ያነጋገሩት አቶ ዓሊ፣ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣዩ ጉባዔ ላይም ኮረም ሞልቶ ጉባዔው ቢካሄድም፣ የአባላት ተሳትፎ እንዲህ መሆን እንደሌለበት ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

በፍርድ ቤት የተፈረደለት ኩባንያና ጠቅላላ ጉባዔው

ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረው ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር አባላት ምርጫ እንዲሰረዝና ባለአደራ ቦርዱ እንዲረከበው የተደረገበት ዋናው ምክንያት ኅብረት ኢንሹራንስ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የወከላቸውን አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ በመታገዳቸው ነው፡፡

ያለአግባብ አባሌ ታግዶብኛል ያለው ኅብረት ኢንሹራንስም ክስ መሥርቶ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተመረጡ ተመራጮች መሠረዛቸውን አስታውቆ ለኅብረት ኢንሹራንስ ፈርዷል፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት በባለአደራ ቦርድ የተጠራውና ሐሙስ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለዘጠነኛው ጉባዔ መታገድና ድጋሚ መጠራት ምክንያት የሆኑት የኅብረት ኢንሹራንስ ተወካይ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በሐሙሱ ስብሰባ አልተገኙም፡፡

ብዙዎችም ይመጣሉ ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ የዕለቱ ጉባዔ እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በአንድ አባል እንደቀረበውም በፍርድ ቤቱ ክርክር ባለመብት ወይም አሸናፊ የሆኑት ሰው እዚህ ካሉ አስተያየት ይሰጡ የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ አቶ ዓሊም የተባሉት ሰው መኖር አለመኖራቸውን አልጠየቁም፡፡

ሆኖም አቶ ኢየሱስ ወርቅ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለምን እንዳልተገኙ ሪፖርተር ጠይቋቸው ነበር፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በሐሙሱ ስብሰባ ላይ ያልተገኙት ጠቅላላ ጉባዔው የተጠራው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በሚያዘው መሠረት ባለመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

የጠቅላላ ጉባዔው 500+1 በሚለው መጠራት የሌለበት በመሆኑና ሕግን በማሰብ መሆኑ እንዲሁም የምልዓተ ጉባዔን ጉዳይ ሕገወጥ ነው ብለው በፍርድ ቤት ጉዳዩ እየታየ በመሆኑ መገኘት አላስፈለገኝም ብለዋል፡፡ መጀመሪያውኑ ይህ መተዳደሪያ ደንብ የተሻሻለው ምልዓተ ጉባዔ ባላሟላ ጠቅላላ ጉባዔ ነውም ብለዋል፡፡

ባለአደራ ቦርዱ ግን ይህንኑ ሐሳብ አይስማማበትም፡፡ ኮረም ለመሙላት 500+1 መሆን አለበት የሚለውን የንግድ ምክር ቤቱን ሕገ ደንብ ያልሻረ በመሆኑ፣ ጉባዔው መካሄድ ያለበት 500+1 በሚለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የተቋቋመው ባለአደራ ቦርድ ባልፈረሰው ሕገ ደንብና በስድስተኛ ጉባዔያችሁ ባፀደቃችሁት ሕገ ደንብ የቦርድ አባላቱን እንዲያስመርጥ ብቻ ስለሆነ ኃላፊነት የተሰጠው በዚሁ መሠረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዓሊ እንደተናገሩት፣ በዕለቱ የተያዘውን አጀንዳ ቋጭቶ በመረጣችሁዋቸው መሪዎች አማካይነት ቀጣይ ሥራዎች ይካሄዳሉ፡፡ ‹‹በባለአደራ ቦርዱ ሙሉ ዝግጅት አድርጎ ነበር ግን አልተሳካም፤›› በማለት ከዚህ በኋላ ምን መደረግ እንደሚገባው ተሰብሳቢውን ጠይቀዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ ተበትኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ምክር ቤቱን መልሶ ለማቋቋም ደግሞ ሁሉም ወገን መሥራት ይጠበቅበታል፤›› ብለው፣ ቀጣዩ ስብሰባ በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ ለማድረግ ሐሳብ አቅርበው ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ ሆኖም ግን የንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ ቀጣዩ ስብሰባ መጠራት ያለበት ከ15 ቀናት መሆኑን ያመለክታል፡፡

በቀጣዩ ጥሪስ ምን ያህል አባላት ይገኙ ይሆን የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሐሙሱ ስብሰባ አዲስ አበባን ሊወክሉና የሚችሉ የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት ካልተገኙ፣ ተገፋፍተው በሚመጡ አባላት ምልአተ ጉባዔው ሞላ ከተባለም ይህም ሌላ ችግር ነው የሚሉ አሉ፡፡ ብዙዎች ግን ይህ ንግድ ምክር ቤት ከተመልካቾች እጅ ወጥቶ አዳዲስ አመራሮች ሊኖሩት ይገባል የሚለው አስተያየት እየጐላ ነው፡፡ የሐሙሱ ስብሰባ ግን የንግድ ምክር ቤቱን ደረጃ ያሳየና ትዝብት ውስጥ የከተተ እንደሆነም ሁኔታውን በገለልተኝነት ያዩ ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች