የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍላተ ከተሞች ለጨረታ ባቀረባቸው ቦታዎች ከፍተኛ የመጫረቻ ዋጋ ንረት ታየ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አያትና ሰሚት አካባቢዎች ለጨረታ የቀረቡ 19 የቢዝነስ ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ20 ሺሕ እስከ 21 ሺሕ ብር ቀርቦላቸዋል፡፡ ቦሌ ቡልበላ አካባቢም ለመኖሪያ ቤት የቀረበ 163 ካሬ ሜትር ቦታ ወ/ሮ አሊቪያ ዳንኤል የተባሉ ባለሀብት 33,157 ብር በካሬ ሜትር ሲያቀርቡ፣ ከዚሁ ቦታ አጠገብ የሚገኝ ተመሳሳይ ቦታ ወ/ሮ ሰገን አድሃኖም በተባሉ ባለሀብት 31 ሺሕ ብር ቀርቦለታል፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ ወደ የረር የሚወስደው መንገድ አካባቢ አሥር ተጫራቾች ብቻ በካሬ ሜትር ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ብር ከማቅረባቸው ውጪ፣ የተቀሩት ተጫራቾች በካሬ ሜትር ከ10 ሺሕ እስከ 13 ሺሕ ብር ድረስ አቅርበዋል፡፡
ለመሬት ሊዝ ጨረታ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ መሠረተ ልማት በአግባቡ ላልተሟላላቸውና ለቢዝነስ ሥራ ተመራጭ ሳይሆኑ ለቆዩት ለእነዚህ ቦታዎች የቀረበው መጫረቻ ዋጋ እጅግ ውድ የሚባል ነው፡፡ ከዚህም በላይ የአዳዲስ መንደሮች የገበያ ዋጋን ክብረ ወሰን የሚሰብር ዋጋ በመሆኑ፣ ቀጣዩ የመሬት የሊዝ ግብይት ሌላ ገጽታ ሊይዝ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሁለቱ ክፍላተ ከተሞች 238 ቦታዎችን ለጨረታ አቅርቧል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለጨረታ የቀረቡት ቦታዎች የሚገኙት በአያት፣ በሰሚትና በቡልቡላ አካባቢዎች ነው፡፡ የቀረቡት ቦታዎች ለቢዝነስ፣ ለቅይጥና ለአፓርትመንት አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቀረቡት ቦታዎች አብዛኞቹ ከአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ ጀምሮ ወደ የረር በሚወስደው መንገድ አካባቢ ሲሆኑ፣ ቦታዎቹ ሙሉ ለሙሉ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በተለይ እነዚህ ቦታዎች የመንገድ አውታር የሌላቸው በመሆናቸው፣ ይህን ያህል ዋጋ ያወጣሉ ተብሎ ባለመገመቱ ግርምትን ፈጥሯል፡፡
ለቢዝነስ ቦታዎች በተለይም አያት አካባቢ ለሚገኙ 1,598 ካሬ ሜትር ቦታ አቶ መላው ደረሰ የተባሉ ባለሀብት 21,550 ብር በካሬ ሜትር ሲያቀርቡ፣ ከዚሁ ቦታ ጐን ለሚገኝ 1,500 ካሬ ሜትር ቦታ ወ/ሮ አለምነሽ ሳህሉ 4,728 ብር ማቅረባቸው ጉዳዩን የሚከታተሉ አስደምሟል፡፡ ሁለቱ ተጫራቾች ባቀረቡት ዋጋ መካከል ያለው ክፍተት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ቦታዎች ጐን ለጐን በመሆናቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ ዋጋ አቀራረብ አለመሆኑን ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡
ለአንድ ወር የጨረታ ሰነድ ሲሸጥ ቆይቶ መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የአቃቂ ቃሊቲ፣ የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ የቦሌ ጨረታ ተከፍቷል፡፡ ጨረታው የተከፈተው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ክበብ ሲሆን፣ የቀረበው ዋጋ ለተጫራቾች በሚነገርበት ወቅት አግራሞት የተሞላበት ጉርምርምታ ይደመጥ ነበር፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አያት አካባቢ ለሚገኘው ስፋቱ 1,200 ካሬ ሜትር ለሆነ ለቢዝነስ አገልግሎት ለሚውል ቦታ የተወዳደሩት ወ/ሮ ቤተልሔም መኩሪያ ጉዳዩ አግራሞት ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ ወ/ሮ ቤተልሔም ለዚህ ቦታ በካሬ ሜትር አምስት ሺሕ ብር በመመደብ ቢወዳደሩም፣ አንደኛ የወጣው ባለሀብት 20 ሺሕ ብር ማቅረቡ አስገርሟቸዋል፡፡
ወ/ሮ ቤተልሔም ለሪፖርተር እንደገለጹት ቦታው አያት ኮንዶሚንየምን አልፎ የሚገኝ ነው፡፡ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ የሚገነባው ሕንፃ በቶሎ ገበያ ይደራለታል የሚል እምነት ስለሌላቸው ያቀረቡት አምስት ሺሕ ብር መሆኑን ገልጸው፣ እሳቸው ካቀረቡት የበለጠ ዋጋ ለቦታው ይቀርባል ብለው ጭራሽ እንዳልገመቱ በአግራሞት ተናግረዋል፡፡