Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ የፀረ ሽብርተኝነትና የፕሬስ ሕጉ እንዲሻሩ ወይም እንዲስተካከሉ እሠራለሁ አለ

መድረክ የፀረ ሽብርተኝነትና የፕሬስ ሕጉ እንዲሻሩ ወይም እንዲስተካከሉ እሠራለሁ አለ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ አንድነት መድረክ ዘንድሮ ለሚካሄደው አምስተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ መሆኑን ለማሳየት የሚረዳውን የምርጫ መወዳደሪያ ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ፡፡ የፀረ ሽብርተኝነትና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጐችን ለማሻር ወይም ለማስተካከል እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

መድረክ ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገው መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻውና ጸሐፊው አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መሠረታዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አከባበር በሚመለከት መድረክ ‹‹እንደ ፀረ ሽብርና የፕሬስ አዋጅ ያሉ ሕጎች ይሻራሉ ወይም ሕገ መንግሥቱን በማይጥስበት ደረጃ ይስተካከላሉ፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

መድረክ በማኒፌስቶው በዋነኛነት የዘረዘራቸው በርካታ ነጥቦች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም መካከል ‹‹ከአማርኛ በተጨማሪ ሰፊ ብዛት ያለው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፤›› በማለት አሁን እየተሠራበት ካለው የፌዴራሉ መንግሥት አንድ የሥራ ቋንቋ በተለየ ሁኔታ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን ለማምጣት እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡

ማኒፌስቶው ‹‹የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች ትናንሽና መለስተኛ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ልማት ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፤›› በማለት የግል ባለሀብቶችን እንደሚጋብዝ ይዘረዝራል፡፡

በመጪው ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ ከተመረጠ መድረክ አከናውናቸዋለሁ ያላቸው በርካታ ነገሮች ሲሆኑ፣ በተለይ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ ዓላማ ተግባራዊነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥም ፓርቲው ይገልጻል፡፡

ባለ 13 ገጹ የፓርቲው ማኒፌስቶ የተለያዩ አማራጭ ያላቸውን ሐሳቦችና ነጥቦችን ያካተተ ሲሆን፣ አጠቃላይ አማራጮቹም በስድስት ክፍሎች ተጠቃለው ቀርበዋል፡፡

እነዚህ ስድስት ክፍሎች በዋነኛነት የሚያተኩሩት ደግሞ አጠቃላይ ማብራሪያ፣ መሠረታዊ የፖለቲካ ዓላማዎችና አቋሞች፣ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ፣ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ፣ የውጭ ግንኙነትና የአገር ብሔራዊ ጥቅም፣ የኢኮኖሚ ልማትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ልማትን በሚመለከት ደግሞ በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ማኒፌስቶው ይገልጻል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመሬት ይዞታና የግብርና ልማት ዘርፍ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት፣ የውኃ ሀብትና የማዕድን ልማት፣ የትራንስፖርትና የመገናኛ አገልግሎቶች ልማት፣ የፋይናንስ ተቋማት ልማት፣ የከተሞችን ልማት የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አሉ የሚላቸውን ችግሮችና አማራጭ ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡

ማኒፌስቶው ሌላው በዝርዝር የዳሰሰው ደግሞ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ሲሆን፣ በዚሁም ክፍል የሥራ አጥነት፣ የድህነትና የፍልሰት ችግር፣ የትምህርት ጉዳይ፣ የጤና አገልግሎት፣ ማኅበራዊ ዋስትና እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መድረክ እንዲሁ አሉ የሚላቸውን ችግሮችና አማራጭ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡

መድረክ የማኅበራዊ ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም የሚከተል የፓርቲዎች ስብስብ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አራት ፓርቲዎችን በአባልነት አቅፏል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎችም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና) እና የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲያዊ የደቡብ ኅብረት አንድነት ናቸው፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...