Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ለማጋጨት ሆን ተብሎ የፈጠራ ወሬዎች እየተሠራጩ ነው››

‹‹ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ለማጋጨት ሆን ተብሎ የፈጠራ ወሬዎች እየተሠራጩ ነው››

ቀን:

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር ለማጋጨት ሆን ተብሎ የፈጠራ ወሬዎች እየተሠራጩ መሆኑን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በቅርቡ በቆሼ ስለደረሰው  አደጋና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳንና ከግብፅ ጋር ለማጋጨት  ወይም ግጭት ያለ ለማስመሰል  አንዳንድ የጥፋት ኃይሎች ሆን ብለው የፈጠራ ወሬዎች እያሠራጩ ነው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ እምነት ባለፈው ሳምንት ከደቡብ ሱዳን ተነስተው በጋምቤላ ክልል ጥቃት ያደረሱ የሙርሌ ታጣቂዎች መንግሥትን አይወክሉም፡፡ ሙርሌዎች ቀደም ሲል ከ100 በላይ ዜጎችንና በርካታ ከብቶች ዘርፈው ወስደው ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ በርካታ ሕፃናትና ከብቶች ዘርፈው፣ እንዲሁም ሰዎችን ገድለው መሰወራቸው አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተወሰዱ ሕፃናቱን በሕይወት ለማትረፍ ሲባል ኃይልን ከመጠቀም የተቆጠበ መሆኑ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ከተወሰዱት መካከል ስድስት ሕፃናትና ተዘርፈው የነበሩ 185 ከብቶች በሙሉ መመለስ እንደተቻለ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም በመንግሥት ዕቅድ ወጥቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በድንበር አካባቢ ግጭት ያለ በማስመሰል፣ ግብፅ ከኡጋንዳና ከደቡብ ሱዳን ጋር በማበር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለማድረስ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ አስመስሎ የሚነዙ ወሬዎች አሉ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ለማጋጨትና በኢትዮጵያ ሰላም እንደሌለ ለማስመሰል በጥፋት ኃይሎች ሆን ተብሎ የሚሠራጩ ወሬዎች መሆናቸውን መንግሥት እንደደረሰበት አመልክተዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን (ጁባ) የሚሠራጭ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚ መሪዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፣ ግብፅ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከደቡብ ሱዳን ተነስታ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ስምምነት ማድረጓን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በቅርቡ ቆሼ በሚባለው ሥፍራ በደረሰው የቆሻሻ የመደርመስ አደጋ ከ125 በላይ ሰዎች ለሕልፈት በመዳረጋቸው ተጠያቂው ማን ነው? ተብሎ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ በአሜሪካና በቻይናም ተመሳሳይ አደጋ እንደሚደርስ ሚኒስትሩ ጠቁመው ለአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለተመሳሳይ አደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ (በተለይ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች) ነዋሪዎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በአዲሱ የከተማው ማስተር ፕላን እንዲካተት ተደርጎ መንግሥት እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ ንፅህና ጋር በተያያዘ ለጤና የማይመቹ አካባቢዎች በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ተካተዋል፡፡ ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ ዕቅድ ወጥቶ እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቆሼ ስለደረሰው አደጋ ከጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ የአደጋው መንስዔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከቴክሳስ (አሜሪካ) ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ተቋቁሞ እንደሚጠና ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...