በአዲስ አበባ ከተማ የተንሰራፋውን ሕገወጥ ንግድ ለመግታት አዳዲስ ሥልቶች እንደቀየሰና በተለይ በሰባት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በንግድ ቢሮ ላይ ባካሄደው ጥናት፣ በተለይ በሦስት ዘርፎች የሚገኙ ሰባት ችግሮችን ነቅሶ አውጥቷል፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከንግድ ቢሮ ጋር በተደረገው ውይይት የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበው መግባባት ላይ በመደረሱ፣ በሁለተኛው ሩብ ዓመት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያና ዕርምጃ ለመውሰድ ዕቅድ ወጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ ሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በመጀመርያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከቢሮው ሠራተኞች ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ይደረጋል፡፡ ከተለዩ ችግሮች መካከል የነዳጅ አቅርቦት፣ ሕገወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድና የኦዲት ግኝቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአዲስ አበበ ከተማ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ችግር መኖሩን ነዋሪዎች በተገኘው አጋጣሚ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ ንግድ ቢሮው ይህንን መሠረት በማድረግ 118 ከሚሆኑ የነዳጅ አከፋፋዮች ጋር ውይይት በማድረግ ክትትልና ቁጥጥር በማካሄድ አጥፊ ሆነው በተገኙት ላይ ደግሞ ከፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፍትሕ ቢሮና ከፍርድ ቤቶች ጋር በመተባበር አስተዳደራዊና ፍትሐዊ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
በተለይ ባለፉት 13 ዓመታት ሲስፋፉ በቆዩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ሲንሰራፋ የቆየው ሕገወጥ ንግድም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ችግር ነው፡፡ ይህንን ድርጊት ለመፍታት የንግድ ቢሮው ግብረ ኃይል አቋቁሞ በአምስት ሺሕ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ በጥፋተኞች ላይ ተገቢውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ቢሮው አሳውቋል፡፡
በከተማው ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድን መግታት ላይ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ ቢሮው ከሚመለከታቸው የፀጥታና የፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት ሥልታዊ በሆነ መደበኛ ፕሮግራም ክትትል በማድረግ ዕርምጃ ለመውሰድና በዚህ ዕርምጃ ቢሮው 15 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ለማድረግም አቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ቢሮው ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሕግ አገልግሎት በመስጠት በኦዲት ግኝት የታየ 2.7 ሚሊዮን ብር እንዲመለስ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡