Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መስክ ለውጦችን ያመላከተው የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት በርካታ ጉድለቶች እንዳሉ...

በመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መስክ ለውጦችን ያመላከተው የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት በርካታ ጉድለቶች እንዳሉ ጠቆመ

ቀን:

በለጋሾችና በኢትዮጵያ መንግሥት በሚመደብ በጀት ሲተገበሩ በቆዩት የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ በየጊዜው ለውጦች ቢመዘገቡም፣ በርካታ ጉድለቶች እንደሚታዩ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት አመላከተ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ረገድ አፋርና ሶማሌ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

በጤና፣ በትምህርት፣ በመጠጥ ውኃ፣ በሳኒቴሽንና በሌሎችም የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች መስክ ሲካሄዱ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ከማክሰኞ ኅዳር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ መገምገም በጀመረው የጋራ መድረክ ወቅት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባቀረበው የዳሰሳ ጥናት ውጤት መሠረት፣ በአገሪቱ የተሻሻለ ንፁህ የመጠጥ ውኃ የሚያገኘው ሕዝብ ቁጥር 65 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 57 በመቶው የገጠሩ ነዋሪ ሲሆን፣ ከከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ግን 97 በመቶው የንፁህ ውኃ አቅርቦት ያገኛል ተብሏል፡፡

በአገሪቱ የሥነ ሕዝብና የጤና አገልግሎቶች ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ ከፍተኛ ጉድለት የታየበት የግልና የአካባቢ ንፅህና ወይም የሳኒቴሽን አቅርቦት ነው፡፡ በኤጀንሲው ጥናት መሠረት የአገሪቱ የሳኒቴሽን ሽፋን ስድስት በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በየሜዳው የሚፀዳዳው ሕዝብ ብዛት 32 በመቶ ሲሆን፣ የተሻሻሉ የሳኒቴሽን አቅርቦቶች ጉድለት 53 በመቶ ደርሷል፡፡ እንደ መፀዳጃ ቤት ያሉ አገልግሎቶችን በጋራ የሚጠቀመው ሕዝብ ብዛት ዘጠኝ በመቶ እንደሆነ የሚያሳየው ጥናት፣ በገጠር ደረጃ የተሻሻለ አቅርቦት ማግኘት ያልቻለው ሕዝብ 56 በመቶ እንዲሁም በከተማ ደረጃም 43 በመቶ እንደሚሸፍን አመላክቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጤና ረገድ የሕፃናት ሞት እየቀነሰ በመምጣት በሕይወት ከሚወለዱና ከአምስት ዓመታቸው በፊት ለሞት ከሚዳረጉ 1,000 ሕፃናት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚሞቱት ቁጥራቸው 67 እንደሆነ፣ ይህም ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት ከተመዘገበው የ88 ሕፃናት ሞት ቁጥር አንፃር መቀነሱን አሳይቷል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት በተደረገው ጥናት መሠረት የሟች ሕፃናት ቁጥር 166 እንደነበር የኤጀንሲው የጥናት ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይሁንና በጤና ባለሙያዎች ታግዘው የሚለወዱ እናቶች ቁጥር 28 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ያሳየው ይኸው ጥናት፣ 42 በመቶው የወሊድ አገልግሎት በልምድ አዋላጆች እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

የልምድም የሕክምናም አገልግሎት ሳያገኙ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 15 በመቶ ሲሆን፣ በሐኪሞች ዕገዛ የሚለወዱ እናቶች ብዛት ስድስት በመቶ፣ በነርሶች ወይም በአዋላጅ ነርሶች ታግዘው የሚወልዱት እናቶች ቁጥር 20 በመቶ ሆኗል፡፡ በጤና ተቋማት ከሚወለዱ እናቶች ዝቅተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡት ክልሎች አፋርና ሶማሌ ሲሆኑ፣ 15 እና 18 በመቶ እንደ ቅደም ተከተላቸው አስመዝግበዋል፡፡ 

በትምህርት ረገድም በአገሪቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከሚያጠናቅቁ ወንዶችና ልጃገረዶች መካከል ዝቅተኛውን ውጤት ያሳዩት የአፋርና የሶማሌ ክልሎች፣ እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት አሳይቷል፡፡ በአፋር ክልል የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የቻሉት 19.13 በመቶ፣ በሶማሌ 26.82 በመቶ ሲሆኑ፣ በድሬዳዋ ደግሞ 38.36 በመቶ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ አካባቢዎች ልዩ እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ደረጃ ማለትም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ባለው ዕርከን ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሁሉም ተማሪዎች፣ ወደ ሚቀጥለው የክፍል ደረጃ ለማለፍ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ማቀዱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለመጪዎቹ ሦስት ቀናት የሚገመገመው የአገሪቱ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ስለታዩ መሻሻሎችና ችግሮች የሚመክረው የጋራ መድረክ፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ትኩረት የሚደረግባቸውን አቅጣጫዎችም ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም ባንክን ጨምሮ በርካታ መንግሥታት ድጋፍ የሚሰጡበት የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መንግሥት ከሚያራምዳቸው ትልልቅ ፕሮግራሞች መካከል እንደሚመደብ ለጋዜጠኞች ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ፣ በቅርቡ ለዚሁ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከዓለም ባንክ ጋር የ600 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል፡፡ መንግሥትም ከራሱ በጀት ይህንን ያህል ገንዘብ ለፕሮግራሞቹ በመመደብ እንደሚሠራ የጠቆሙት አቶ አድማሱ፣ በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር በኩል ከግምጃ ቤት የሚወጣ ገንዘብ በመሆኑ በበጀት አጠቃቀምና ትግብራ ላይ የሚፈጸም የሙስና ተግባር እምባዛም መሆኑንና ለጋሾቹ በውጤት ላይ ተመሥርተው ፋይናንስ የሚለቁ በመሆናቸውም ጭምር፣ የበጀት ፍሰቱን ተዓማኒ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...