Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለግንባታዎች የወጣው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰርኩላር እንዲነሳ ተደረገ

ለግንባታዎች የወጣው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰርኩላር እንዲነሳ ተደረገ

ቀን:

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተቋቋመው ዴሊቨሪ ዩኒት ማናቸውም ግንባታዎች ከመካሄዳቸው በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲያካሂዱ አስገዳጅ ሆኖ መደንገጉ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት ሆኗል የሚል አቋም በመያዙ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል ፕሮጀክቶች ከመካሄዳቸው በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የማካሄድ ጉዳይ አስገዳጅ ስለመሆኑ ያስተላለፈውን ሰርኩላር አነሳ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ ‹‹የመንግሥትም ሆነ የግል የልማት ፕሮጀክቶች በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሥርዓት ማለፍ እንደሚገባቸው የተላለፈ ሰርኩላር ስለማንሳት›› በሚል ርዕስ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ለከተማው ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹በከተማችን በተለያዩ ዘርፎች እየተተገበሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ለከተማው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና የተተገበሩትና ወደፊትም የሚተገበሩት የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃን በማገናዘብ፣ ከአካባቢ ጋርም ተጣጥመው መሥራታቸው ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጉልህነትና ዘላቂነት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል ይሁንታ የሚያሰጣቸው ወይም ክልከላ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች ዝርዝር በደብዳቤ ቁጥር አ.አ./ብዕ/03/307 በተጻፈ ሰርኩላር መሠረት አገልግሎቱ በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ሆኖም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊና መልካም አስተዳደር ዴሊቨሪ ዩኒት አማካይነት በግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል ያሉ ችግሮችን ለመለየት በተካሄደው ጥናት፣ ከላይ በሰርኩላር የወረደው አሠራር ችግር ሆኖ መገኘቱ ተረጋግጧል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መነሻ በአዲስ አበባ የተቋቋመው ዴሊቨሪ ዩኒት ከ55 የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል የአካባቢ ተስማሚነት የሚያስፈልጋቸውንና በዚሁ ሥርዓት ማለፍ የሚገባቸውን ልማቶች የመለየት፣ የከተማው ፕላን ኮሚሽን ካዘጋጀው የመሬት አጠቃቀም ጥናት ጋር የተገናዘበ ልማት እንዲከናወን በታቀደው መሠረት የመፍትሔ ሐሳብ ጥናቱ ተከናውኖ እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሕግጋቱ መሠረት የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቱን የመስጠት ሒደቱን እንዲያስቀጥል ሲሉ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህ ደብዳቤ በግልባጭ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ ለኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ለፕላን ኮሚሽንና ለከንቲባው ዴሊቨሪ ዩኒት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተልኳል፡፡

በቅርቡ እንደ አዲስ የተቋቋመው የመሠረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን (የቀድሞው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን) በበኩሉ፣ ሰርኩላር ስለመነሳቱ የሚገልጸውን ደብዳቤ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ለሚገኙ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤቶች ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. አሰራጭቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሠረተ ልማት ቅንጅት፣ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አለቃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል የተሰራጨው ሰርኩላር ለሁሉም ዓይነት ግንባታዎች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ያስፈልጋል የሚል ነበር፡፡ ይህ አሠራር ከፍተኛ መጉላላትና የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠሩ፣ መኖሪያ ቤትን ለመሳሰሉ ግንባታዎች ጥናቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማካሄድን አስቀርቷል፡፡

‹‹አሁንም ቢሆን ግን አካባቢን ሊበክሉ ለሚችሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ለውኃ ማጠራቀሚያ፣ ከ500 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ የሚገነቡ መጋዘኖች፣ ለነዳጅ ማደያ፣ ለፋብሪካና ሆስፒታልን ለመሳሰሉ ግንባታዎች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ይጠየቃል፤›› ሲሉ አቶ መለስ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን አዲስ የሚካሄዱ ግንባታዎች በሙሉ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲያካሂዱ በፌዴራል ደረጃ ኅዳር 24 ቀን 1995 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 299 ወጥቷል፡፡ ቀደም ብለው የተካሄዱ ግንባታዎች ደግሞ በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመከላከል በዚሁ ወቅት የብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300 ወጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም ከእነዚህ አዋጆች በመነሳት ደንብና መመርያዎች አውጥቶ ከመሥራቱም ባሻገር፣ የከተማው መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ለባለሥልጣኑ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት አውቀው ተባባሪ እንዲሆኑ ሰርኩላር ተላልፏል፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ የከተማው ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አዲስ ለሚገነቡ ሁሉም ግንባታዎች የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይሁንታ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዱኛ ወንድሙ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ ‹‹ትኩረት የተሰጠው የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታትተ ብቻ ነው፡፡ በወቅቱ የተነሳ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት በሁሉም ክፍለ ከተማ አውርደን ነበር፡፡ ነገር ግን ችግሩ እየተነሳ በመሆኑ መንግሥት ሰርኩላሩን አንስቷል፤›› ብለዋል፡፡

ያም ሆኖ ግን የከተማው ፕላን ኮሚሽንና አካባቢ ጥበቃን ጨምሮ አራት መሥሪያ ቤቶች ሕግጋቱን በመመርመርና በማጥናት የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ችግሮችን ለመፍታት የዴሊቨሪ ዩኒት ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ዴሊቨሪ ዩኒት የሚመሩት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆኑ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር ደግሞ ሦስት ዘርፎች ተቋቁመዋል፡፡

የመጀመርያው ዘርፍ የማኅበራዊና መልካም አስተዳደር ዴሊቨሪ ዩኒት ሲሆን፣ ዩኒቱን አቶ ሙክታር ከድር ይመሩታል፡፡ ሁለተኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ሲሆን፣ ዘርፉን አቶ ሱፊያን አህመድ ይመሩታል፡፡ ሦስተኛው የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ሲሆን ዘርፉን አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ይመሩታል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃም የዴሊቨሪ ዩኒት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደሚመሩት ታውቋል፡፡

ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀረበ ሪፖርት ዴሊቨሪ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ‹‹ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በሚያስችል መንገድ የማቀድ፣ የመምራትና የመከታተል አሠራር ማዕቀፍ ሲሆን፣ ይህም የመሪዎችን ራዕይና ግብ ውጤታማና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስፈጸም ያስችላል፤›› ሲል አዲስ የመጣውን አሠራር ይገልጸዋል፡፡ ይህ የዴሊቨሪ ጽንሰ ሐሳብ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ በሚል ምክንያት ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሲደረጉ የቆዩትን (ቢፒአር፣ ባላንስድ ስኮር ካርድ፣ ካይዘን) ጽንሰ ሐሳቦች የሚተካ ሳይሆን ጎን ለጎን የሚካሄድ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...