Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ መንግሥታት ለአየር መንገዶቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

የአፍሪካ መንግሥታት ለአየር መንገዶቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ቀን:

– ኢትዮጵያ አዲስ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ልታፀድቅ ነው

የአፍሪካ መንግሥታት የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለአኅጉሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ፣ ለአየር መንገዶቻቸው አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡

መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተከፈተው 24ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባዔ የአፍሪካ መንግሥታት ለአፍሪካ አቪዬሽን ዕድገት ተጋግዘው መሥራት እንዳለባቸው፣ የአየር ትራንስፖርት ገበያቸውን ለአፍሪካ አየር መንገዶች ክፍት ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

የጉባዔው አዘጋጅ አፍሪካ አቪዬሽን ሰርቪስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኒክ ፋዱግባ የአፍሪካ መንግሥታት የኤርፖርት መሠረተ ልማት በማስፋፋት፣ ታክስ በመቀነስና የጉምሩክ አሠራሮችን በማሻሻል ለአየር መንገዶቻቸው ድጋፍ ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የአፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1988 የአፍሪካን የአየር ትራንስፖርት ገበያ ክፍት ለማድረግ የተስማሙበትን ውሳኔ እስካሁን ተግባራዊ አለማድረጋቸው እንደሚያስወቅሳቸው ጠቅሰው፣ በአፋጣኝ የአፍሪካ ገበያ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነፃ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ሚስተር ዴቪድ ካጃንጌ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፍሪካ ኅብረት ባቀረበው ጥያቄ በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ አገሮች የአየር ትራንስፖርት ገበያቸውን እ.ኤ.አ. 2017 ሙሉ በሙሉ ክፍት ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀዳሚነቱን በመውሰድ ላደረገችው ጥረት አድናቆታቸውን የገለጹት ሚስተር ካጃንጌ፣ ሌሎችም አገሮች የኢትዮጵያን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጉባዔውን በክብር እንግድነት የከፈቱት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የአቪዬሽን ዘርፍ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ 70 ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ፣ ሰባት ሚሊዮን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር  ገልጸው፣ የአፍሪካ አገሮች ለአቪዬሽን ዕድገት ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

 የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘርፉ ዕድገት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን መፍጠሩን የተናገሩት አቶ ወርቅነህ፣ በቀጣይ የዘርፉን ዕድገት የሚደግፍ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ለማፅደቅ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ሲሠራበት የቆየው ረቂቅ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጐበት በቅርቡ ለመንግሥት ቀርቦ እንደሚፀድቅ አስረድተዋል፡፡

የጉባዔው አስተናጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አገሪቱ ኢኮኖሚ በፈጣን ዕድገት ላይ መሆኑን አውስተው ገቢው ባለፉት አሥር ዓመታት ከ490 ሚሊዮን ዶላር በ500 ፐርሰንት በማደግ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት 81 አውሮፕላኖችና 84 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት ጠቁመው፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ገቢውን አሥር ቢሊዮን ዶላር፣ የአውሮፕላኖቹን ብዛት 140፣ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ደግሞ 120 ለማድረስ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተወልደ የአፍሪካ አገሮች ለአፍሪካ አየር መንገዶች የበረራ ፈቃድ በመከልከል ለውጭ አየር መንገዶች በራቸውን መክፈታቸው አግባብ እንዳልሆነ አውስተዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች ነፃና አንድ ወጥ የሆነ ገበያ መፍጠር እንደሚገባቸው፣ ተባብረው መሥራት እንጂ አንዱ አየር መንገድ ሌላውን ያጠፋል በሚል ተገቢ ያልሆነ ሥጋት ተሸብበው የመስኩን ዕድገት ወደኋላ መጐተት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 70 ዓመታት ከሌሎች አፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ተባብሮ ሲሠራ እንደኖረ፣ ወደፊትም ይህን አጠናቅሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

በጉባዔው ከተለያዩ አገሮች የመጡ 250 የኩባንያ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፣ እንደ ቦይንግና ኤርባስ ያሉ ግዙፍ አውሮፕላን አምራቾች፣ የአውሮፕላን ጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች፣ የአውሮፕላን ሞተርና መለዋወጫ አምራቾች፣ እንዲሁም አየር መንገዶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን በኤግዚቢሽኑ ላይ አስጐብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከልና የአቪዬሽን አካዳሚውን ለተሳታፊዎች አስጐብኝቷል፡፡

አየር መንገዱ በጥገና ማዕከሉ ላይ 500 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የጥገና አቅሙን ማጐልበቱን የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ዘመነ ነጋ ተናግረዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በሰባት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባ አዲስ የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋር ተመርቋል፡፡

በተመሳሳይ የአቪዬሽን አካዳሚው በ80 ሚሊዮን ዶላር መጠነ ሰፊ የሆነ የማስፋፊያ ሥራ በማካሄድ ላይ እንደሆነ የአካዳሚው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ ለጐብኝዎች ገልጸዋል፡፡ አካዳሚው ፓይለቶች፣ ቴክኒሺያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የማርኬቲንግ ባለሙያዎች የሚያሠለጥን ሲሆን፣ ሠልጣኞችን የመቀበል አቅሙን በዓመት 200 የነበረውን ወደ 1,000 አሳድጓል፡፡ በቀጣይ የመቀበል አቅሙን በዓመት 4,000 ለማድረስ በመሥራት ላይ እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱ በቅርቡ ገዝቶ የተከለው የድሪምላይነር አውሮፕላን ምሥለ በረራም ተመርቋል፡፡

  

  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...