Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የተነሳው እሳት በሠራተኞች ላይ ሞትና ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

  በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የተነሳው እሳት በሠራተኞች ላይ ሞትና ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

  ቀን:

  –  ሠራተኞቹ ቤተል ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ነው

  ‹‹እሳቱ በማምረቻ ፋብሪካው ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል›› ስኳር ኮርፖሬሽን

  መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት አካባቢ እስካሁን ባልታወቀ ምክንያት በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ አንድ የፋብሪካው ባለሙያ ሕይወታቸው ሲያልፍ በ16 ሠራተኞች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ታወቀ፡፡

  በአገሪቱ ካሉና ስኳር በማምረት ላይ ከሚገኙት ወንጂና መተሐራ የስኳር ፋብሪካዎች በላይ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ላይ የተነሳው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ በተለይ የፋብሪካው ሠራተኞች፣ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ወደ ዋናው ፋብሪካ እንዳይዛመት ማድረጋቸውንና ሊተርፍ መቻሉን፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዘመድኩን ተክሌ ተናግረዋል፡፡

  ባለፈው ቅዳሜ ከዋናው ፋብሪካ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘውና ፋብሪካው ስኳር እንዲያመርት ኃይል የሚሰጠው የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ ገለባ (ባጋስ) በእሳት መያያዙን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ገለባውን በማቃጠል ወደ ኃይል እንዲለወጥ የሚያደርገው ባጋስ ማሽን ሙሉ በሙሉ በቃጠሎው ከመውደሙ በስተቀር፣ በፋብሪካው ዋና ዋና ክፍሎች ላይ ሳይዛመት መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

  የፋብሪካው ሠራተኞች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ባደረጉት የማጥፋት ርብርብ እሳቱ ዋናውን ፋብሪካ እንዳይጠጋ መከላከል የተቻለ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ የድንገተኛ እሳትና አደጋ መከላከል አገልግሎት፣ እንዲሁም የመከላከያ ሔሊኮፕተር በመድረሳቸው እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን አቶ ዘመድኩን አስረድተዋል፡፡

  ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ሠራተኞቹ ባደረጉት ርብርብ እሳቱን መቆጣጠር የተቻለ ቢሆንም፣ አቶ ተስፋዬ ለሚ የተባሉ የፋብሪካው ሠራተኛ ሕይወታቸው ማለፉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 11 ሠራተኞች በቤቴል ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አምስት ሠራተኞችም የደረሰባቸው ጉዳት ቀላል ስለነበር በአካባቢው ክሊኒክ ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡

  ፋብሪካው ለጊዜው ሥራ ያቋረጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመድኩን፣ ምክንያቱ ደግሞ የኃይል ማመንጫ ማሽን በመቃጠሉ መሆኑንና እሱም ጥገናው ተጠናቅቆ በቀናት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡

  ፋብሪካው በቂ ክምችት ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመድኩን፣ ከመጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አራት ቀናት ፋብሪካው ሥራ ካቆመ በኋላ ለኅብረተሰቡ የሚደርሰው የስኳር ሥርጭት ሒደት እንዳይዛባ ከክምችት ወጥቶ እንደሚያከፋፈልም አስታውቀዋል፡፡ በፋብሪካው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ባለመድረሱ እንደተቃጠለ በማስመሰልና ምርት እንደሌለ የተሳሳተ መረጃ በመንገር የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ኅብረተሰቡ ሊያውቅ እንደሚገባና ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡

  ከአዲስ አበባ በ350 ኪሎ ሜትር ርቀት በኦሮሚያ ክልል ፊንጫ ልዩ ስሙ ለምለም በረሃ በሚባለው ሥፍራ የሚገኘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ በደርግ ዘመን ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም ማምረት የጀመረው በ1991 ዓ.ም. ነው፡፡

  ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ከኅዳር ወር 2007 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ 87,710 ቶን ስኳር ያመረተ መሆኑን፣ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ከ58 ሺሕ ቶን በላይ፣ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ደግሞ ከ55 ሺሕ ቶን በላይ ስኳር ማምረታቸው ታውቋል፡፡

  ለፋብሪካው 21,000 ሔክታር የሸንኮራ አገዳ መትከያ ማስፋፊያ ተደርጎለታል፡፡ ፋብሪካውም በተደረገለት የማስፋፊያ ሥራ የሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅሙን ከ5,000 ቶን ወደ 12,000 ቶን አሳድጓል፡፡ በዓመት 270,000 ቶን ስኳርና 20,000 ሜትር ኩብ ኢታኖል እንደሚያመርትም ታውቋል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...