– ለ18 ወራት በእስር ቆይተው በብቃት በመከላከላቸው ነፃ ወጥተዋል
የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ፋይናንሱን ከሚያመጡ ድርጅቶች ለመግዛት ባወጣው ዓለም አቀፍ የትራንስፎርመሮች ጨረታ ምክንያት፣ በሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው ለ18 ወራት ባደረጉት ክርክር በነፃ የተሰናበቱት ሁለት ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎችና ሦስት ኃላፊዎች በሹመት ወደ ሥራቸው ተመለሱ፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሰብሳቢ የሆኑበት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት ቦርድ መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ መሆናቸው በፍርድ ቤት ለተረጋገጠላቸው አምስት የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችን ሾሟል፡፡
ቦርዱ አቶ መስፍን ብርሃኔን የአገልግሎቱን ዘርፍ ማኔጅመንት ኮንትራት ወስዶ እያስተዳደረ የሚገኘው የህንድ ኩባንያ ወኪል ሚስተር ከህሬ ኩማር በመቀጠል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ አቶ ሽፈራው ተሊላ ደግሞ በኢንጂነር አዜብ አስናቀ የሚመራው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ ሚሊዮን ማቱሳላን ደግሞ የግዥ፣ የሎጂስቲክስና የመጋዘን ዳይሬክተር፣ አቶ ዳንኤል ገብረ ሥላሴ የአስተዳደርና ሎጂስቲክ ኦፊሰር፣ አቶ ሰመረ አሳቤ ደግሞ የማሠራጫ፣ የፕላንና ዲዛይን ባለሙያ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ቦርዱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሹመት የሰጣቸው ኃላፊዎች በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ለ18 ወራት ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የቆዩ ቢሆንም፣ ባቀረቡት የሰነድና የሰዎች ማስረጃዎች የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዳልፈጸሙ በመረጋገጡ፣ እንዲሁም ከመታሰራቸው በፊት በነበሩበት ኃላፊነት በሥራቸው ከፍተኛ ለውጥ ያመጡ መሆናቸው ከግምት ውስጥ ገብቶ ሊሾሙ መቻላቸውን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊና የቦርድ አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ በተለይ በኃይል ሥርጭት ዘርፍ ማኔጅመንቱን እንዲያስተዳድር በተሰጠው የህንድ ኩባንያ አማካይነት ከፍተኛ ለውጥ ታመጣለች የተባለ ቢሆንም፣ እንኳን ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ በነበረበት እንኳን ማስቀጠል አለመቻሉን የገለጹት የቦርድ አባሉ፣ የህንዱ ኩባንያ የኮንትራቱን ጊዜ ሊጨርስ ከስድስት ወራት ያልበለጠ ጊዜ እንደቀረው ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እነዚህን ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ቦርዱ መሾሙ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለሹመት የበቁት ኃላፊዎች ሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. የተዘጋጀ ክስ የቀረበባቸው ቢሆንም፣ በተጠረጠሩበት ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ (በወቅቱ መጠሪያ) 3,520 የማሠራጫ ትራንስፎርመሮች ግዢ ለመፈጸም ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው፣ ጉድላክ ስቲል ሊሚትድ የሚባል የህንድ ኩባንያ ሲሆን፣ ከነወለዱ በ17,695,686 ዶላር ለማቅረብ መስማማቱን ክሱ ያስረዳ ነበር፡፡ ኩባንያው ግን የትራንስፎርመሮቹን ፋይናንስ ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ፣ ኮብራ ኢንስታሌሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የግዢውን ፋይናንስ እንዲያቀርብለት ውል እንዲሻሻልለት ጥያቄ ያቀርባል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ተስማምቶ ውሉን አሻሽሏል፡፡ ጉድላክ ትራንስፎርመሮቹን ሲያቀርብ ኮብራ ኢንስታሌሽን ደግሞ የግዢውን ፋይናንስ ለማቅረብ የሦስትዮሽ ውል ተፈራርመዋል፡፡ ሁሉንም የስምምነት ፊርማዎች በኮርፖሬሽኑ በኩል የተፈራረሙት የቀድሞው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበ መሆናቸውን ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
ጉድላክ የተባለው ኩባንያ ትራንስፎርመሮቹን የሚያቀርበው ናሽናል ኤሌክትሪክ ኢኪዩፕመንት ኮርፖሬሽን ከሚባል ሌላው የህንድ ኩባንያ በመሆኑ ምክንያት፣ የኮርፖሬሽኑ የሕግ ባለሙያ ጉድላክ ቀስ እያለ ከስምምነቱ ሊወጣ ይችላል በሚል ሥጋት ‹‹ጉድላክ ከውሉ እንዳይወጣ›› የሚል የማሳሰቢያ ደብዳቤ መጻፋቸውንም የክስ ቻርጁ ይገልጻል፡፡ ጉድላክ ጨረታውን ሲያሸንፍ የወሰዳቸውን ግዴታዎችና መብቶች ለኮብራ በማስተላለፍ እንደተፈራው ከሦስትዮሽ ውሉ ይወጣል፡፡ አሁን ለሹመት የበቁት ኃላፊዎች በወቅቱ በነበራቸው የሥራ ኃላፊነት መሠረት፣ ዋናው ተጫራች ከሦስትዮሽ ውሉ መውጣቱን እያወቁ ከሌላው የህንድ ኩባንያ (ኮብራ) ተቀባይነት እንዲያገኝ ማረጋገጫ ሰጥተዋል የሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር፡፡ ጉድላክ ውሉን በማፍረሱ ኮርፖሬሽኑ ሊያገኝ የሚችለውን 1,487,776 ዶላር እንዲያጣ በማድረግ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተመሠረተባቸውን ክስ፣ አምስቱም ተሿሚዎች በብቃትና አስተማማኝ በሆነ ማስረጃ ማስተባበል በመቻላቸው ነፃ መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከተሿሚዎቹ ጋር አብረው ተከሰው የነበሩ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች አቶ አሸናፊ ዮሐንስ (በሌሉበት)፣ አቶ ፋሪስ አደም፣ አቶ ብሩክ ተገኝና አቶ ጌታቸው አዳነ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው ለሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ለውሳኔ ተቀጥረዋል፡፡