የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለ ወይኒ አሰፋ ባለፈው ሳምንት በተከናወነው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመቐለ ሴቶችን በተመለከተ ለተናገሩትና ተቃውሞ ላስከተለባቸው አነጋገራቸው ይቅርታ መጠየቃቸው ታወቀ፡፡
አቶ ተክለ ወይኒ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ ፕላኔት ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ባለፈው ዓርብ [ኅዳር 1 ቀን] የተናገርኩት ትክክል አልነበረም፡፡ የትግራይ ሴቶችን ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን መመራት ያለባቸው በስፖርቱ ባለፉ ባለሙያዎች መሆን እንደሚኖርባቸው ያስቀመጡት አቅጣጫ ላይ ለሰነዘሩት አስተያየትም አቶ ተክለ ወይኒ ይቅርታ መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
ክልሉ የምክትል ፕሬዚዳንቱን አ አስተያየቶች ተከትሎ ክልሉ በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት እንዲወዳደሩ ሰጥቷቸው የነበረውን ውክልና ሰርዟል፡፡ አቶ ተክለ ወይኒ የክልሉን ውሳኔ መቀበላቸውን በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሴቶች ላይ የተሰነዘረውን አሉታዊ አስተያየት የትግራይ ሴቶች ማኅበር (ማደአት) በመቃወም ኅዳር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አቶ ተክለወይኒ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማሳሰቡ ይታወቃል፡፡