የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በመጤ አረም መወረሩን የፓርኩ ኃላፊ አቶ ሽፈራው መንግሥቴ ይናገራሉ፡፡ ይህም ከሰው ሠራሽ ችግሮች ጋር ተዳምሮ የፓርኩን ህልውና እየተፈታተነ ነው፡፡
አቶ ሽፈራው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮሶፊሶ ፓርቴንየምና ሪቨር ቫይን በመባል በሚጠሩት መጤ አረሞች ፓርኩ በመጥለቅለቅ ላይ ሲሆን፣ በነፋስና በእንስሳት ዓይነ ምድር አማካይነት በፍጥነት እየተዛመተም ነው፡፡
አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ተከስቶ በነበረው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በውስጡ የነበሩት የዱር እንስሳትም ተሰደው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ከዚያ ድርቅ ቢያገግምም ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለስ ግን አልቻለም፡፡
በፓርኩ ባደረግነው ቅኝትም አፈር ብቻ ይታይባቸው የነበሩ ሥፍራዎች ሳር ለብሰው ቢታዩም፣ ብቅ ብቅ ያለው ሳር በፍየሎች፣ በግመሎች እንዲሁም ለቤት ክዳን በሚያጭዱ ሰዎች ሽሚያ እየጠፋ ነው፡፡ የፓርኩ መለያ የሆነው ሳርና እዚህም እዚያም እያገገሙ ያሉት ግራሮችም በሰዎች እየተመለመሉ ነው፡፡
ከፓርኩ ተሰደው የነበሩ አዕዋፋት መመለሳቸውን በማገገም ላይ ባሉት ግራሮች በርካታ አዳዲስ የወፍ ጎጆዎች ተቀልሰው መታየታቸው ያረጋግጣል፡፡ በፓርኩ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲገባ ለወትሮው ከርከሮና አጋዘን በብዛት ሲያቋርጡ ይታይ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ፍየሎችና በርቀት ደግሞ ጠባቂዎቻቸው ከፓርኩ ጠባቂዎች ለመሸሽ ሲያቋርጡ ይታያሉ፡፡ ከድርቁና ከሽሚያው የተረፈው የፓርኩ መለያ ሰንበሌጥ ዛሬ ቁመቱ አጥሮ የግጦሽ ሜዳ መስሎ ይታያል፡፡
የፓርኩ ኃላፊ እንደሚሉት፣ አረሙ የተለያየ ባህሪ ሲኖረው፣ የሚያደርሰውም ውድመት ፈጣን ነው፡፡ በፓርኩ በዋናነት ለሳላ ምግብ የሆነውን ሳር እያጠፋም ይገኛል፡፡ ሐረግ መሳዩ አረም ያገገሙት ዛፎች ላይ በመጠምጠምና ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ምንም ብርሃንና አየር እንዳያገኙ በማድረግ በስብሰው እንዲወድቁ እያደረገ ነው፡፡ ሥራቸው ረዣዥም የሆኑት አረሞች ደግሞ በበቀሉበት አካባቢ ውኃን ከምድር በመምጠጥና አጠገባቸው ያለውን ተክል ውኃ በማሳጣት እንደሚያደርቁት፣ ለፓርኩ መሠረት የሆኑት የግጦሽና ትልልቅ የግራር ዛፎች በእነዚህ መጤ አረሞች በመጥፋት ላይ መሆናቸውንና የዱር እንስሳቱ ምግብና መጠለያ ማጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አረሙ ከፓርኩ ከ80 ሔክታር በላይ ደን አጥቅቷል፡፡ በጥናት ባይረጋገጥም በተለምዶ ሳር የሚበቅልባቸው ቦታዎች ቀንሰዋል፡፡ የበቀሉትም የቀጨጩና ለአንድ ወቅት ብቻ የሚቆዩ መሆናቸውን ፓርኩን ተዘዋውረን በተመለከትንበት ወቅት ባለሙያዎች አስረድተውናል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ድርቁ ከተከሰተ በኋላ እየባሰበት መጥቷል፡፡ ከበላይ አካል የሚሰጠው ትኩረት ደካማ በመሆኑ ከዚህ ሊደርስ መቻሉን በመጠቆም፣ ችግሩ ከእሳቸውና ከሠራተኞቻቸው በላይ እንደሆነ አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡
ፓርኩ ከተጋረጡበት በርካታ አደጋዎች አንዱ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ያለው ችግር ሲሆን፣ ይኼንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ያለው ጂአይዜድ፣ የፓርኩ ጠባቂዎች ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ሰሞኑን በፓርኩ ውስጥ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት ሚስተር ፓትሪክ ዱርሶስካ ከአገር ሽማግሌዎቹ ፊት በርከክ በማለት ከፓርኩ ጠባቂዎች ጋር ተባብረው በመሥራት ፓርኩን እንዲታደጉ ተማጽነዋል፡፡
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በፓርኩ ላይ ባደረግነው ጉብኝት ሳላዎችን ለማየት በረዣዥም ሣር የተሸፈነውን የፓርኩን ክፍል ማጋመስ የግድ ነበር፡፡ በቡድን ተሰብስበው የተቀመጡ ሳላዎችን ማየትም ያጓጓ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ ተመናምኗል፡፡ አካባቢውን ቀድሞ ለሚያውቀው ሰው ዛሬ ላይ ያለበት ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ከነበሩት የዱር እንስሳት ተርፎ በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮች የቤት እንሰሳዎች ይመግብ የነበረው ፓርክ እየተራቆተ ነው፡፡
የፓርኩ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ስለደረሰው ድርቅ ሲገልጹ፣ በፓርኩ ውስጥ ሣር የሚበቅልባቸው ቦታዎች በማይታወቅ መጤ አረም እየተሞሉ ነው፡፡ አገር በቀል ዕፅዋትም እየጠፉ ዘራቸውም እየተመናመነ ነው፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ውዝግብ በከፊል ቢፈታም ችግሩ ግን አለ፡፡
አዋሽ ፓርክ ከአዲስ አበባ 215 ኪሎ ሜትር ርቆ በምሥራቁ የአገራችን ክፍል የሚገኝ ሲሆን፣ የተቋቋመው 1958 ዓ.ም. ነው፡፡ በወቅቱ ስፋቱ 756 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የነበረ ሲሆን፣ በ1961 ዓ.ም. ሲከለል፣ አሁን ያለውን 591 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይዞ ቀርቷል፡፡
ፓርኩ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎችም ያዋስኑታል፡፡ ዝቅተኛ የሙቀት መጠኑ 26 ዲግሪ ሲንቲግሬድ ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 42 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይለካል፡፡ በዓመት በአማካይ እስከ 620 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ዝናብ ያገኝ ነበር፡፡ በውስጡም 81 አጥቢ እንስሳት 435 የወፍ ዓይነት 43 ሬፕታይልስና ከ400 በላይ የዕፅዋት ዓይነቶች ይዟል፡፡ በተለይ የቱሪስት ቀልብ የሚስበው የፓርኩ መለያ አርማ የሆነው ሳላህ፣ በብዛት ይኖርበታል፡፡ የአዋሽ ፏፏቴ፣ የተፈጥሮ ፍልውኃ፣ እዋሽ ጐርጅ፣ ረዣዥም ሳሮች፣ ከ20 የሚበልጡ የተፈጥሮ መስህቦችን ይዟል ቢባልም፣ ዛሬ ላይ ሁኔታዎች ተቀያይረዋል፡፡ የአዋሽ ፓርክ እየተመናመነ ነው፡፡
ፓርኩ በሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ ሲሄዱ አዋሽ ከተማ ለመድረስ 16 ኪሎ ሜትር ሲቀርዎት በስተቀኝ አዋሽ ፓርክን ያገኛሉ፡፡ ይህ ግቢ ብዛት ያላቸው ሳላዎችን ጨምሮ ሌሎች እንስሳት የሚገኙበት ነው፡፡ በስተግራ በኩል ደግሞ ከዋናው መንገድ 30 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ፍልውኃና የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ያሉበትን የፓርኩን ክፍል ያገኛሉ፡፡
በአካባቢው የአርብቶ አደሮች በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ፣ በአዋሽ ፓርክ አስተዳደር ያለው የመንግሥት ኃላፊነትና የሙያ ግዴታ፣ ተከስቶ የነበረው ድርቅ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ፣ አረሙ፣ በፓርኩ ውስጥ አዲስ የተዘረጋው የባቡር መስመር፣ የአዋሽ ወንዝ መበከል፣ በዱር እንስሳቱ ላይ የሚደርሰው ችግር፤ ፓርኩ ከቱሪዝም የሚያስገኘውን ጥቅም አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መቼ፣ እንዴት፣ ተፈትተው አዋሽ ፓርክ የቀድሞውን ግርማ ሞገስ ያገኝ ይሆን? የሚለውና ከዚህ ቀደም ይነሳ የነበረውን ጥያቄ አሁንም ኅብረተሰቡ እያነሳው ነው፡፡