በአዲስ መልኩ ብቅ ብለው የነበሩት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) በአንድ ወቅት የአገሪቱ የስፖርት ቤተሰብ መነጋገሪያ ነበሩ፡፡ በብቃታቸው በአፍሪካ ዋንጫ በተከታታይ መሳተፍ የቻሉት ሉሲዎቹ ዛሬ ላይ ግን የወትሮው ዓይነት ትኩረት ያገኙ አይመስልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ያስመዘገቡት ውጤትና አነሳሳቸው ላይ የነበረው ውጤታማነት ከመሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነው፡፡
ይህም ሆኖ በኮንጎ ብራዛቪል አስተናጋጅነት በመጪው ጳጉሜን ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ማጣሪያ ከአናብስቱ ካሜሮናውያን ጋር ተፋጠዋል፡፡ ጨዋታው በዕድሳት ምክንያት ከሁለት ወር በላይ ከማንኛውም እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴዎች ዝግ ሆኖ በቆየው በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዳሜ መጋቢ 12፣ 2007 ዓ.ም. ይደረጋል፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች በደርሶ መልሱ ጨዋታ አሸናፊው ለመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አላፊ ይሆናል፡፡
የሉሲዎቹ ዋና አሠልጣኝ በኃይሏ ዘለቀ የተጋጣሚያቸውን ቡድን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል መረዳት የሚያስችል የቪዲዮ መረጃ ደርሷቸው ቡድናቸውን እንዳዘጋጁ ይናገራሉ፡፡ 26 ተጨዋቾችን በኢትዮጵያ ሆቴል አሰባስበው ከሁለት ሳምንት በላይ ዝግጅት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ዋና አሠልጣኙ፤ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ቡድኑ የታቀፉት ሁሉም ተጨዋቾች እስከመልሱ ጨዋታ ድረስ እንደማይቀነሱ ሆኖም ወደ ካሜሮን የሚጓዙት ግን 20 ወይም 23 ተጨዋቾች ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ያስረዱት፡፡
አሠልጣኟ ይህን አስተያየት እስከሰጡበት ድረስ ቡድናቸው ጨዋታውን በሚያደርግበት የአዲስ አበባ ስታዲየም ዝግጅት ያደረገው ለአምስት ቀን ብቻ ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት በመድንና በመከላከያ ሜዳዎች ጠንካራ ዝግጅት ማድረጉን ግን አልሸሸጉም፡፡ የሉሲዎቹ ተጋጣሚ የካሜሮን ቡድን በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ የላከው መግለጫ ያመለክታል፡፡ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ የሚዳኙት ዳኞች አራቱም ከግብፅ ሲሆኑ፣ የጨዋታው ታዛቢ ዳኛ ደግሞ ከኬንያ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡