አንድ ዓመት ሊሞላቸው የወር ዕድሜ የቀራቸው ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ በብሔራዊ ቡድኑ የነበራቸውን ኃላፊነት ይዘው ‹‹ይቀጥሉ›› ወይስ ‹‹አይቀጥሉ›› የሚለውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነገ በስቲያ (መጋቢት 11፣ 2007 ዓ.ም.) በሚያደርገው ስብሰባ ውሳኔ እንደሚሰጥ ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ከዋሊያዎቹ ጋር በነበራቸው የዋና አሰሠልጣኝነት ቆይታ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው፣ ሆኖም ክፍያው አሠልጣኙ እንዲያስመዘግቡ ከሚጠበቀው ውጤት ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ ምክንያት የእግር ኳስ ቤተሰቡ የተቃውሞ ድምፁን ማሰማት ከጀመረ መሰነባበቱ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ከዚሁ ሁኔታ በመነሳት ለአገሪቱ የስፖርት ሚዲያ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ‹‹በብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ዙሪያ የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስተላለፈውም ሆነ የተደረገ ስብሰባ የለም፡፡ ሆኖም ሪፖርቶችን መሠረት ያደረገ ሙያዊ ግምገማ ተደርጎ ተገቢውን መረጃ ወደፊት እሰጣለሁ፤›› ማለቱም ይታወሳል፡፡
የአሠልጣኙን ገፀ ሰብ (ፕሮፋይል) አጣርቶና መርምሮ ለፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅርቦ ቅጥሩ እንዲፈጸም በዋናነት የሚጠቀሰው የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ከሳምንት በፊት ተሰብስቦ አሠልጣኙ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ላይ መድረሱ ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡