Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየጎዳናዋ ሠዓሊት

የጎዳናዋ ሠዓሊት

ቀን:

መሀል ፒያሳ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕንፃ ፊት ለፊት የሚገኘውን የመንገደኞች መተላለፊያ ጥግ ይዘው የሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የሠራተኛ መውጫ ሰዓት ጠብቀው የሚነግዱ ሸቀጣ ሸቀጥ ቸርቻሪዎችና የኔ ቢጤዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በጎዳናው የሚመላለሱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ የነሱን እጥፍ ይሆናል፡፡ አካባቢውን ዘወትር ግርግር አያጣውም፡፡

በመንገደኛ መተላለፊያው ባለ አግዳሚ ድንጋይ ላይ የተቀመጠችው ሴት ግርግሩ ያወካት አትመስልም፡፡ በቀኝ እጇ በያዘችው እርሳስ በግራ እጇ ባለው ኤፎር ወረቀት ላይ በስሱ ትሥላለች፡፡ አልፎ አልፎ እርሳሱን ከወረቀቱ ታነሳና የሠራችውን በተመስጦ ትመለከታለች፡፡ አጠገቧ መሬት ላይ የዘረጋቻውን ሥዕሎች ቆም ብለው የሚቃኙ መንገደኞች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሥዕሎቿ ምስለ አካል (ፖርትሬት) ናቸው፡፡ በተለያየ ዕድሜ የሚገኙ ግለሰቦች ተሥለው ወረቀቶቹ በላስቲክ ተሸፍነዋል፡፡ የጎዳናዋ ሠዓሊት የምሥራች ነጋሽ ትባላለች፤ 35 ዓመቷ ነው፡፡

ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ከጎኗ አስቀምጣ አንዳንዴም ፎቶግራፋቸውን ተቀብላ እየተመለከተች መሣል ከጀመረች አንድ ዓመት ሊሞላት ነው፡፡ ከምትኖርበት አምስት ኪሎ ወደ ፒያሳ የምትመጣው የአምስት ዓመት ወንድ ልጇን አስተኝታ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ነው፡፡ እስከ እኩለለሊት ድንጋዩ ላይ ተቀምጣ ካስረከቧት ፎቶ የተሣለውን ሥዕል ለመውሰድ የሚመጡ እንዲሁም ከምትደረድራቸው ውስጥ መርጠው የሚገዙ ሸማቾችን ታስተናግዳለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባነጋገርናት ዕለት እንደወትሮዋ የተንቀሳቃሽ ስልኳን መብራት አብርታ ኮፍያዋ ሥር ከታዋለች፡፡ በብርሃኑ እየታገዘች የአንድ ጎልማሳ ምስለ አካል እየሠራች ነበር፡፡ የምሥራችን ያሳደጓት አክስቷ እንደነገሯት የተወለደችው አሰብ ከተማ ነው፡፡ ልጅ ሳለች ቤተሰቦቿን በሞት ስለተነጠቀች አክስቷ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ሊያሳድጓት ወሰኑ፡፡ አክስቷ ከጥቂት ዓመታት በላይ በሕይወት አልቆዩም፡፡ ሲያርፉ ሲአርኤስ ወደተባለ የዕርዳታ ድርጅት ታመራና ወላጆቻቸውን ካጡ ታዳጊዎች ጋር እንድትማር ዕድሉን ያመቻቹላታል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በጀርመን የዕርዳታ ድርጅት ትምህርት ቤት ካጠናቀቀች በኋላ ዳግማዊ ምኒልክ ገባች፡፡ ተማሪ ሳለች በምትማርበት ክፍል በእርጅና ምክንያት የተሰነጣጠቁ ክፍተቶች ያሉት ግድግዳ ላይ የምትመለከታቸውን ትርጉም የለሽ ቅርፆች በሕሊናዋ ቅርፅ ትሰጣቸዋለች፡፡ በዕረፍት ሰዓት ቅርፆቹን ሠሌዳ ላይ ታሰፍራቸዋለች፡፡ በ1992 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በማታው መርሐ ግብር ሥዕል መማር ጀመረች፡፡ ለሁለት ዓመት ተምራ ብትመረቅም ለመሣል የሚያስፈልጓትን ቁሳቁሶች የምታሟላበት ገንዘብ ስላልነበራት በሙያው መዝለቅ አልቻለችም፡፡

አክስቷ ይኖሩበት የነበረውን የቀበሌ ቤት እያከራየች መጠነኛ ገቢ ብታገኘም ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ሆነባት፡፡ ቀድሞ ይደጉማት በነበረው የዕርዳታ ድርጅት ሥር ተቀጥራ በመዋለ ሕፃናት ግድግዳና በሕፃናት መጻሕፍት ላይ ኢሉስትሬሽን (ታሪክን የሚገልጹ ሥዕሎች) ትሠራ ነበር፡፡ ሥራው ሲቋረጥ የጽዳት፣ የመስተንግዶና ሌላም ሥራዎች ስትሞካክር የሳንባ በሽታ ይዟት ከቤት ዋለች፡፡ ወዳጅ ዘመድ የሌላት የምሥራች በወቅቱ የምትመገበው እንኳን ማግኘት ተስኗት እንደተሰቃየች ታስታውሳለች፡፡ ከጊዜ በኋላ በምትኖርበት አካባቢ የተዋወቀችው ፍቅረኛዋ ያስታምማት ስለነበር አብረው ለመኖር ወሰኑ፡፡

እሷ ብታገግምም ፍቅራቸው በቶሎ ተቋጨ፡፡ በሚጋጩበት አጋጣሚ ሁሉ ይደበድባት እንደነበር ትናገራለች፡፡ ከተለያዩ በኋላ ያሳደጋት የዕርዳታ ድርጅት ተመልሳ እንዲተባበሯት ተማፀነች፡፡ ቤቷን አድሰው ጥቂት የኪስ ገንዘብ ሰጧት፡፡ ሕይወቷ በመጠኑ መስመር ሲይዝ ወደ ሥዕል ተመለሰች፡፡ ቤቷ ውስጥ ባገኘችው ቁሳቁስ ላይ ሳይቀር ትሥል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከተዋወቀችው ወጣት ጋር ፍቅር ትጀምራለች፡፡ አቅም ስላልነበራቸው በሠርግ ሳይጋቡ አብረው መኖር ይጀምራሉ፡፡

ሥዕል እንዳትሥል ተፅዕኖ ያደርግባት ስለነበር መስማማት አልቻሉም ስታረግዝ ባሕሪው ተለወጠ፤ የሚያጣላቸው ምክንያትም በዛ፡፡ ለሷና ለልጇ ምንም ዓይነት ድጋፍ ማድረግ ስላልፈለገ ጥሏት እንደሄደ ትናገራለች፡፡ እርግዝናዋ እየገፋ ሲሔድ ምንም መሥራት ስላልቻለች ቤቷ ትውላለች፡፡ ከባለቤቷ ጋር ከተለያዩ በኋላ ወደ ቤታቸው ቢመለስም ስላልተስማሙ መውለጃዋ ሲቃረብ በሕግ ጣልቃ ገብነት ተለያዩ፡፡

በዚህ ወቅት የአእምሮ መረበሽ እንዳጋጠማት ትናገራለች፡፡ ከወለደች በኋላ ልጇን ለማሳደግ ቀድሞ የሥነ ጥበብ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ ሥዕል ለመሣል የምትመርጠው የፒያሳ ጎዳና ላይ ለልመና ወጣች፡፡ ለሦስት ዓመት ያህል ሙሉ ፒያሳን እየተዘዋወረች ለምናለች፡፡ ‹‹የጎዳና ሕይወት በቀላሉ ባይገፋም ዓይኔ እያየ ልጄ በረሃብ ከሚሞት ከመለመን ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፤›› በማለት ያሳለፈችውን ታወሳለች፡፡

ቀን እየለመነች ማታ አክስቷ የተወችላት የቀበሌ ቤት ትመለሳለች፡፡ አዕምሮዋ ሲረጋጋ መንገድ ላይ በወዳደቁ ወረቀቶችና በካርቶን ቅዳጅ ላይ መሣል ጀመረች፡፡ አላፊ አግዳሚ ከበዋት ሲመለከቱና አንዳንዶች ሽጭልን ሲሏት ‹‹እግዚአብሔር የሰጠኝን ቅባ ዘይትና የምወደድን ሙያ እየሠራሁ ገንዘብ ማግኘት የሚለው ሐሳብ ብልጭ አለልኝ፤›› ትላለች፡፡ ጎዳና ላይ መሣል እንደጀመረች የሠራቻቸውን በአሥር ብር እየሸጠች ገንዘብ አጠራቅማ ለሥዕል የሚያመች ወረቀት ገዛች፡፡ በስተመጨረሻ ከዓመት በፊት ልመና አቁማ የሰዎችን ምስል እየሠራች ወደመሸጥ ገባች፡፡

አሁን አንድ ፎቶግራፍ ለመሳል 80 ብርና ሁለት ለዋሌት ሳይዝ ፎቶ 120 ብር ታስከፍላለች፡፡ አጠገቧ ተቀምጠው ለመሣል የሚፈልጉ ሰዎችን 30 ብር ታስከፍላቸዋለች፡፡ ፒያሳ የሚታየው የዕለት ከዕለት ሕይወት ለሥዕሎቿ ዋነኛ ግብዓት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ሊስትሮዎች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችና መንገደኛው ባጠቃላይ ለየምሥራች ገፀ ባሕሪያት ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ የተለያዩ አካባቢዎችን ባህላዊ አኗኗር የሚያሳዩ ሥዕሎችና አፄ ቴዎድሮስን የመሰሉ መሪዎችን ሥላ ከ25 እስከ 30 ብር ትሸጣለች፡፡

አንዳንዴ ምሽት ላይ ልጇን ወደምትሠራበት ስፍራ ትወስደዋለች፡፡ ቤት ውስጥ ብቻውን ትታው መውጣት ቢከብዳትም ተማሪ ስለሆነ ዕረፍት እንዲወስድ አስተኝታው ትወጣለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ አካባቢውን ከሚያዘወትሩ ሰዎች ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አላት፡፡ ሥዕል እየሸጠች በቀን እስከ 150 ብር ታገኛለች፡፡ ሥዕል ባይገዟትም ለማበረታታት ጥቂት ገንዘብ የሚሰጧትም አሉ፡፡ ስትለምን መንገድ ላይ ያገኟት የፖስተሪቲ የሥነ ልቦና ማዕከል ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ይሰጧታል፡፡

የምትወደውን ሙያ ቀን ከሌት ባሻት ሰዓት መሥራቷ ያስደስታታል፡፡ መተዳደሪያ ከመሆኑ  ጎን ለጎን በውስጧ ከታመቀው ስሜት እፎይታ የምታገኝበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ጥበብ ሙሉ ነፃነት ይፈልጋል፤›› የምትለው የምሥራች ድህነት፣ ጤና ማጣትና የታወከ ትዳር ከፊል ሕይወቷን እንደቀማት ትገልጻለች፡፡

‹‹ልጄ ሲማር ቀኑን እየሣልኩ አሳልፋለሁ፤ እኩለ ሌሊት ላይ ጊዜ ገድቦኝ ወደ ቤቴ መመለሴ ባይቀርም ፒያሳ እየሣልኩ ባድር ቅር አይለኝም፤›› ትላለች፡፡ በሐሴት ተሞልታ፡፡ ሠዓሊ ከእያንዳንዱ ሰው ምልከታ አሻግሮ እንደሚያይ ገልፃ፣ እሷም እይታዋንና ሐሳቧን ማካፈል በመቻሏ ግቧን እንደመታች ታምናለች፡፡ ሥዕል ተስፋ በመቁረጥ ያሳለፈችውን የሕይወቷ ክፍል እንዳሳለፋት ትናገራለች፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት በደብተሬ ጀርባ ላይ፣ ቤቴ መሬት ላይና አስፋልት ዳር ተቀምጨ ስለምንም ሥያለሁ፤›› ትላለች ሥዕል በሕይወቷ ያለውን ትልቅ ቦታ ስታስረዳ፡፡

የምሥራች ሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማና፣ ሠዓሊና ቀራፂ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኰንን ታደንቃለች፡፡ ሰፊ ሸራ ወጥራ ላንድ ስኬፕ (መልከዓምድር) የመሣልና (ዉድከት ግራፊክስ በእንጨት የመሥራት) ፍላጎት አላት፡፡ የተማረችውና የምትሠራው ሥዕል ቢሆንም ቅርፃ ቅርፅ የመሥራት ዝንባሌ አላት፡፡ አሁን በጠባብ ቤቷ ውስጥ በጭቃ ቅርፃ ቅርፅ በመሥራት ትለማመዳለች፡፡

‹‹ሕይወቴ እስከሚያልፍ ሠዓሊ ሆኜ መኖር እፈልጋለሁ፤›› የምትለዋ የምሥራች ሥራዎቿን የምታሳይበት ዓውደ ርዕይ የማዘጋጀት ምኞት አላት፡፡ ቀለም፣ ሸራና ሌሎችም ቁሳቁሶች ለማሟላት ገንዘብ እያጠራቀመች ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ ሕልሟ በሸራ ላይ መሣል ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከእንቅልፏ ስትነቃ ቡርሽ፣ ቀለምና በሸራ ላይ የተጀመረ ሥዕል አጠገቧ ሆኖ ብትመለከት ትመኛለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...