Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመቄዶንያ 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ተረከበ

መቄዶንያ 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ተረከበ

ቀን:

– የ15 ሚሊዮን ብር ልገሳ ቃል ተገባለት

መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል (መቄዶንያ) ሊያስገነባ ላቀደው ሁለገብ ሕንፃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ አበረከተለት፡፡

ለግንባታው ወጪ የሚሆን ገንዘብም ለማሰባሰብ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለጋሽ ተቋማትና ግለሰቦች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

መቄዶንያ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና ዝግጅት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕንፃ ግንባታ የሚውል የ30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ሕጋዊ ካርታን የመዲናይቱ አፈጉባኤ ዶ/ር ታቦር ገብረ መድኅን ለመቄዶንያ አስረክበዋል፡፡ አፈጉባኤው እንደተናገሩትም ማዕከሉ በሚያደርጋቸው ሥራዎች ላይ የከተማው አስተዳደር ተሳታፊ ይሆናል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ልገሳ ካደረጉት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 300,000 ብር፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 100,000 ብር መስጠታቸው ታውቋል፡፡

ኮተቤ የሚገኘው ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 750 አረጋውያንን እየጦረ የሚገኝ ሲሆን፣ ሀያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ አዲስ የሚገነባው ሕንፃ ሲጠናቀቅ ለ3,000 አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን አገልግሎት ሊውልና የቅበላ አቅሙን ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳው የመቄዶንያ ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ ተናግረዋል፡፡

 ማዕከሉ ለሚያስገነባው ሕንፃ ለገቢ ማሰባሰቢያነት በዓይነት ከተደረጉ ስጦታዎች መካከል ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ኮንዶሚኒየም ቤቶችና አንድ የቤት መኪና ሲገኙበት ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካም ለቤት ግንባታው የሚያስፈልግ ሲሚንቶ ለማቅረብ ቃል ገብቷል፡፡

ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚመሩበትና በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ መሠረት ማኅበራት 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን በአገር ውስጥ ገቢ በማሰባሰብ እንዲሠሩ እንደሚያዝ ያስታወሱት፣ በመድረኩ ላይ የተገኙት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ልዑል የኋላ እንደተናገሩት፣ አብዛኛዎቹ ድርጅቶች በአዋጁ መሥራት ቢጀምሩም፣ ጥቂት የማይባሉት ግን በአገር ውስጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ከባድ መሆኑን በመግለጽ ከሥራቸው ወደ ኋላ ብለዋል፡፡ እንደ መቄዶንያ ያሉ ተቋማት ግን በአገር ውስጥ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚቻል በተግባር ማሳየታቸውን የገለጹት ‹‹በእነሱ ላይ ያለን እምነትም ከፍተኛ ነው፡፡ ትብብራችንም አብሯቸው ይዘልቃል፤›› በማለት ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጋሽ ነው፡፡ ብዙ ሰው መስጠት ቢፈልግም ችግሩ ለማን ልሰጥ?› የሚለው ጥያቄ ነው፤›› ያሉት የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፀጋዬ በርሔ፣   የከተማው አስተዳደር በለገሳቸው ቦታ ላይ ለመገንባት ያቀዱት ሕንፃ ዲዛይን መገባደዱንና ሁለገቡ ሕንፃ የስብሰባ አዳራሽ፣ መዝናኛ ሥፍራና ሌሎችም መሰል ይዘቶች ማካተቱን ተናግረዋል፡፡ ሕንፃውን ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ 300 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ለዚህም የገቢ ማሰባሰቢያ በቅርቡ እንደሚዘጋጅ አቶ ፀጋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን፣ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል ያለባቸውን ወገኖች ለመርዳት የተቋቋመ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ የተመሠረተውም ከአሜሪካ በተመለሱት አቶ ቢንያም በለጠ አማካይነት በታኅሣሥ 2002 ዓ.ም. ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...