ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለዘንድሮው የሩሲያው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከተደረጉት ግጥሚያዎች መካከል የአፍሪካዎቹ ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካ፣ እንዲሁም የአውሮፓዎቹ ስዊድንና ጣሊያን ፍልሚያ የዓለምን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡
ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን በገዛ ሜዳዋ 2 ለ0 በመርታት ከ16 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ስታረጋግጥ፣ አራት ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳችው ጣሊያን በስዊድን በመረታት ከ60 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ሳትሆን ቀርታለች፡፡ ጣሊያን በሚላን ከስዊንድ ጋር 0 ለ0 ብትለያይም በመጀመርያው ጨዋታ 1 ለ0 መሸነፏ ነው ከዓለም ዋንጫ መድረክ ከስድስት አሠርታት ወዲህ ያራቃት፡፡ ፎቶዎቹ የድል አድራጊዎቹን ሴኔጋላውያንና የድል ተነሺዎቹ ጣሊያናውያን ሐሴት (ደስታ) እና ብካይ (ሐዘን) ያሳያሉ፡፡
ሥጋት
አመሻሽ ላይ
‹‹ደግሞ ሊያስቆዝመኝ በብቸኝነቱ
ይሄ ቀን አለፈ ሊመጣ ነው ሌቱ››
ሊነጋጋ ሲል
‹‹በእቶኑ ሊገርፈኝ በእሳት ወላፈኑ
ሌሊቱ አለፈና ይሄው መጣ ቀኑ››
ቀትር . . .
‹‹ደፈር በል ግድ የለም አንተ ቀን አትስጋ
ቋንጣ አድርገኸው ዋል ይህን ታካች ስጋ››
- ሰሎሞን ሳህለ ‹‹የልብ ማኅተም›› (2010)
*************
መንቶ
ዘፈኑ ሆነና ማሬ ማሬ ብቻ፣
ስንፈልግ ባጀነ ስኳር በዘመቻ፡፡
(ስንቅነሽ ገብሬ)
*********
የ8,000 ዓመቱ የወይን ማሰሮ
በቅርቡ ከጆርጅያ መዲና ቲብልሲ ወጣ ብሎ የተገኘው የሸክላ ማሰሮ ስብርባሪ የ8,000 ዓመታት ዕድሜ አለው፡፡ ተመራማሪዎች እንዳሉትም፣ ሸክላው ጥንታዊ የወይን አጠማመቅን የሚያሳይ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ሸክላው ከወይን ፍሬ፣ ወይን ሲጠመቅና ሰዎች ሲደንሱ የሚያሳዩ ምስሎች ተቀርጸውበታል፡፡ ሸክላው እሰካሁን በወይን አጠማመቅ ዙሪያ ከተገኙ መረጃዎች ጋር ሲነጻጸር በበርካታ ዓመታት ይቀድማል፡፡ ከዚህ በፊት ኢራን ውስጥ 7,000 ዓመታትን ያስቆጠረ ሸክላ ሲገኝ፣ ተመራማሪዎች በዓለም ታሪክ ጥንታዊውን የወይን አሠራር መግለጫ አገኘን ብለው ነበር፡፡ ሆኖም የጆርጅያው ከኢራኑ የሸከላ ማሰሮ በ1,000 ዓመት ስለሚበልጥ ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ ተመራማሪ ስቴፈን ባትዩክ እንደተናገሩት፣ ግኝቱ የወይንን ጥንታዊነት የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹ወይን በሰው ልጅ ሥልጣኔ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ለማኅበራዊ ትስስር መጠንከር፣ ለመድኃኒትነት በመዋልና በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላል፤›› ብለዋል፡፡ ጆርጅያ ውስጥ ዛሬም ወይን ለመጠመቅ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች የቀድሞዎቹን እንደሚመስሉም ተመልክቷል፡፡